የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ ሰዎች የሚያስተላልፏቸው ይዘቶችን ከስሜት ጋር ማያያዝ በጣም የተለመደ ስልት ሆኗል፡፡ ሰው ለስሜት ካለው ስሱነት የተነሳ ምርት እና አገልግሎት ለማስተዋወቅና ለመሸጥ የሚፈልጉ ሰዎች ስሜትን እንደ ስልት ይጠቀማሉ፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ በብዛት የሚሸጡ፣ የሚታዩ፣ የሚደመጡ ይዘቶች ስሜት ኮርኳሪ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ ስሜትን ቆንጠጥ አድርገው መያዛቸው እውነት ቢሆንም እንኳን በሰዎች ላይ የሚፈጥሩት ተጽእኖም የሚካድ አይደለም፡፡
ይህን የማሻሻጥ ዘዴ የስነ ልቦና ምሁራን ትራውማ ማርኬቲንግ (በሰቀቀን ግብይት) ብለው ይጠሩታል፡፡ ሰዎች የግል አሰቃቂ ገጠመኞቻቸውን ወይም ከባድ የሕይወት ውጣ ውረዶቻቸውን ለግብይት የሚጠቀሙባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ አውድ ይህ ዘመን የትኩረት ዘመን ነው፡፡ ትኩረት ደግሞ ገበያ ነው፤ እድል ነው፤ ሀብት ነው፡፡ መታየት እንጀራ ነው፡፡ አላግባብ መታየትም ደግሞ ኪሳራ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አሰቃቂ ገጠመኝን ለግብይት የሚጠቀሙ ይዘት ፈጣሪዎች ግንኙነትን ይገነባሉ፡፡ እውነተኛነትን ይፈጥራሉ፡፡ መፍትሄን ይሰጣሉ፡፡
ሰዎች ሰው እንዲረዳቸው እና እንዲታዩ ይፈልጋሉ፡፡ የግል ስቃያቸውን ማካፈል ደግሞ ወዲያውኑ ወደዚህ የቅርብ ግንኙነት ያደርሳቸዋል፡፡ በቀላሉ ትኩረት ያገኛሉ፤ ይታመናሉ፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ተጋላጭነት እና እምነት የተሳሰሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ አንድ ሰው የሕይወቱን በጣም አስቸጋሪ እና ምስጢራዊ ክፍል ሲያጋራ የራሱን መከላከያ ምሽግ ያፈርሳል፡፡ እርቃኑን አደባባይ የቆመ ስለሚመስል ይታመናል፡፡ ሰዎች በግልጽነቱ ይወዱታል፡፡ ባህል እና እሴት ጠባቂዎች ደግሞ ተው የሚል ሙግት ያቀርቡበታል፡፡ ቢሆንም ብዙኀኑ ወደውታልና ጉዞውን ይቀጥላል፡፡
ይህ ድርጊት ደንበኞች ወይም ተከታዮች ወዲያውኑ የሚያወራቸው ወይም መረጃ የሚያጋራቸው ሰው እውነተኛ እንደሆነ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡ ሰው ራሱን ሲያጋልጥ ለማዳመጥ እና ለመረዳት ፈቃደኞች ይሆናሉ፡፡
ለምሳሌ አንድ ፖድካስት አቅራቢ “እኔም የአልኮል ሱሰኛ ነበርሁ” ወይም “ከዚህ በፊት የገንዘብ ችግር ነበረብኝ” የሚል ታሪክ ሲናገር ወዲያውኑ ተመሳሳይ ችግር ካለባቸው ሰዎች ጋር ጥልቅ የስሜት ግንኙነት ይፈጥራል፡፡
ከአድማጭ ተመልካች ጋር የጋራ እውነታ ያለው ሰው የችግር ታሪክን ሲገልጽ ሰዎች ተመሳሳይ ልምድ እንዳላቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ የዚህ ችግር ተጠቂ እኔ ብቻ አይደለሁም በሚል አቻ ያገኛሉ፡፡ ሰዎች የሚመለከቱት ምስል ወይም የሚያደምጡት ይዘት ይለውጠኛል፣ ይጠቅመኛል፣ የእኔም ጉዳይ ነው ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡ ተመሳሳይ ክንፍ ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ እንደሚባለው ሁሉ፤ ተመሳሳይ ችግር እና ስቃይ ያለባቸው ሰዎች ከስቃይ ሙጫ ትስስርን ያጠናክራሉ፡፡
የአሸናፊ ሰዎች ታሪክ ብዙ ጊዜ ለግብይት ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይዘት የሚያቀርበው ሰው ያለፈበትን ችግር ወይም አሰቃቂ ገጠመኝ ያጋልጣል፡፡ በማጋለጡ የገበያ አማራጩን ያሰፋል፡፡ ከስሬ፣ አጋሬ ጥሎኝ ሄዶ፣ ታምሜ ነበር፣ ሱሰኛ ነበርሁ የሚሉ ይዘቶች ወደ ታዳሚ ሲደርሱ ቀልብን የመግዛት እድል አላቸው፡፡
በመቀጠልም እነዚህ ሰዎች የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት የተጠቀሙበትን ስልት፣ ምርት፣ ወይም ኮርስ ያስተዋውቃሉ፡፡ የእነሱ ታሪክ አሁን የሚሸጠው ነገር ለምን ልክ እንደሆነ እና ለእነሱም እንደሚሰራ እንደ ማረጋገጫ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ታሪካቸው፣ ህመማቸው፣ ስቃያቸው ምርት እና አገልግሎት ማሻሻጫ ሆኖ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡
ለምሳሌ አንድ ይዘት ፈጣሪ “ክብደቴን ለመቀነስ ሞክሬ ከብዶኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህንን ቴክኒክ ተጠቀምሁ፡፡ አሁን ደግሞ ይሄንን ኮርስ ብትገዙኝ እንደ እኔ ትለወጣላችሁ!” ብሎ ያስተዋውቃል፡፡
ይህ ሒደት በታዳሚ ዘንድ ተስፋን የሚፈጥር ነው፡፡ የመለወጥ ገጠመኝን መስማት ለተመልካቾች “እሱ/ሷ ከቻለ/ች እኔም እችላለሁ” የሚል የመቻል ተስፋ ይሰጣል፡፡
ይህ ስሜታዊ ምላሽ የግብይት መልእክቱን በስሜት እንዲሳብ ያደርገዋል፡፡ በዲጂታል ዓለም ውስጥ የግል ታሪኮች ስሜትን የሚነኩ ከሆኑ ትኩረትን በፍጥነት ይስባሉ፡፡ ከተራ ታሪክ በተሻለ የማይረሱ ይሆናሉ፡፡ ለማድመጥ የሚያስገድዱ ሆነው በማይረሳ ትውስታ ማህደር ውስጥ ይታተማሉ፡፡
አርተር ሆርን ማኒፑሌሽን በሚለው መጽሐፉ ሰዎችን የመዘወር እና የመቆጣጠር ስውር ሳይኮሎጂን በተመለከተ አብራርቷል፡፡ ማኒፑሌሽን (መዘወር) ሰዎችን የመጉዳት ፍላጎት ባይኖረውም እንኳን ራስን ለመጥቀም ሲል ሰዎችን ይጠቀማል ይላል፡፡ በዚህም መዘወር በጨዋነት ሲገለጽ ተጽእኖ ፈጣሪነት ነው ብሏል፡፡
ስሜታዊ ተጋላጭነትን ያሳዩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ተብለው ይታያሉ፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ኢጎን (ኩራት እና ክብርን) የሚተው እና እውነተኛ ግንኙነትን የሚሹ ሰዎችን ያደንቃሉ፡፡ ተጽዕኖ (Influence) የሚያገኙ ሰዎች ብዙዎች የማያደርጉትን የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የማህበረሰብ እሴት እና ሞራልን የመጣስ ችግር ውስጥ ሊገቡም ይችላሉ፡፡ ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገኝ ባለመሆኑ ምን ባደርግ ወይም ራሴን እንዴት ባጋልጥ ነው ሰዎች የሚከተሉኝ ወይም ብዙ ተመልካች የማገኘው የሚለውን በሚገባ የሚያጠኑ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ የሚመጡ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተሰላ ዘዴን የሚጠቀሙ እንጂ በደመ ነፍስ የሚያደርጉ አይደሉም፡፡
ይህ ዓይነቱ ግብይት በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎች በአጭር ጊዜ የሕዝብ ቀልብ አግኝተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከስነ ምግባር አኳያ አደገኛ ድንበር የሚጥስ ነው፡፡
አርተር ሆርን እንደሚለው ተጽእኖ ፈጣሪዎች ሰዎችን መበዝበዛቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጋልጡት ከተመልካች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ሳይሆን ራሳቸውን ለመጠቀም ነው፡፡ የግል ስቃይን ማጋራት ከሌሎች ጋር የመገናኛ መንገድ መስሎ ይጀመራል፡፡
በስውር ግን ዓላማው ለፈጣን ትርፍ ሲባል የሌሎች ሰዎች ጥልቅ ስሜቶች ላይ መጫወት ስለሚሆን ወደ ብዝበዛ ይለወጣል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሐሰት ተስፋ ለአድማጭ ተመልካች ሊቀርብ ይችላል፡፡ ታሪኩን በማጋነን ወይም በማጭበርበር፣ ቀላል መፍትሔዎችን ቃል በመግባት፤ የሌሎችን የሕይወት ፈተና ለንግድ ዓላማ መጠቀም ሊኖር ይችላል፡፡
ሰዎች የግል ገጠመኞቻቸውን ለግብይት የሚጠቀሙት እውነተኛ መስሎ በመታየት፣ ስሜታዊ ግንኙነትን በመፍጠር እና ራሳቸውን ለሌሎች እንደ መፍትሄ መንገድ በማቅረብ ነው፡፡ አሰቃቂ ገጠመኝን ለግብይት የሚጠቀሙት ተጽዕኖ በሚፈጥሩባቸው ዘዴዎች ነው፡፡ የግል ታሪኮችን በመናገር ብራንድ (ስም) ለመገንባት በሥነ ምግባር አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ነው፡፡ አሰቃቂ ገጠመኞችን ወይም ተጋላጭነትን ለግብይት ዓላማ መጠቀም ስነ ልቦናዊ ዘዴዎች ናቸው፡፡
አርተር ሆርን የሰዎችን ችግር እና ተጋላጭነት በመጠቀም ግብይት የሚፈጽምባቸው ዘዴዎችን አስቀምጧል፡፡ በዚህም ማስታወቂያዎች ቀዳሚዎች ናቸው፡፡ የአንድን ምርት ወይም አገልግሎት አዎንታዎ ጎን በማጋነን የሰዎችን ምርጫ የመጫን እና የመዘወር አቅም እንዳላቸው ይገልጻል፡፡
ቀጥሎ የሚመጣው የጦነት ስትራቴጂ ነው፡፡ አርተር እንደሚለው የጦር መሪዎች ጠላትን ለማታለል የማይገመቱ ዘዴዎችን እና ፕሮፓጋንዳን ይጠቀማሉ፡፡ ሦስተኛው የሙያተኛው ዓለም ነው፡፡ በአንድ ኩባንያ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ፍላጎት ሁልጊዜም መሪ መሆን ነው፡፡ ነገር ግን ፉክክር እና ትብብርን የሚያስተናግዱበት መንገድ ብዝበዛ ያለበት መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ አለቆች የበላይ እና የበታች ሰራተኞችን የሚይዙበትን መንገድ ጤናማ እንዳልሆነ አርተር ጽፏል፡፡
አራተኛው አርተር የሚያስቀምጠው የብዝበዛ ስልት ሰዎች ከሰዎች ባላቸው ግንኙነት ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ አንዱ ወድቆ ሌላው የሚቀጥልበት ዓለም ውስጥ የሰዎች ግንኙነት ጤና የራቀው ይሆናል፡፡ በፍቅር፣ በወዳጅነት፣ በጓደኝነት እና በቤተሰብ ግንኑነቶች ሰዎች ለሰዎች መጠቀሚያ ይሆናሉ፡፡
ወላጆች የልጆችን ባህሪ በቅጣት ወይም በሽልማት ስም ይበዘብዛሉ፡፡ ምንም እንኳን ወላጆች የልጆችን ባህሪ ለመግራት ብለው ቢያደርጉትም በውጤቱ ብዝበዛ ይሆናል፡፡ በፍቅር ግንኙነት አንዱ ሌላውን ይጎዳል፡፡ አንዱ ሌላውን መጠቀሚያ ያደርጋል፡፡ በፍቅር ወርቅ ሰጥቶ አፈር የሚቀበል ሰው አለ፡፡
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


