የተባባሰዉ የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት

0
11

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት (Russia–Ukraine War) በዓለም ላይ እየተካሄደ ከሚገኙ ጦርነቶች በአውዳሚነቱ ይጠቀሳል። ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከእስያ እስከ አሜሪካ ከፍተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተፅእኖ ያደረሰ ጦርነት ነው።

ዩክሬን እና ሩሲያ በቅድመ ታሪክ አንድ  ሀገር ነበሩ። እ.አ.አ በ1991 ሶቪዬት ሕብረት ስትፈራርስ ነበር ዩክሬን ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን ያወጀችው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም የነበረ ቢሆንም ሩሲያ እ.አ.አ በ2014 ክሪሚያን ወደ ግዛቷ ስትቀላቅል ውጥረት ተፈጠረ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ወደ ለየለት ውጥረት ተሸጋገረ። ሳይውል ሳያድርም የተፈራው ጦርነት ጀመረ።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላዲሚር ፑቲን ዩክሬን ከኔቶ ለመቀላቀል የምታደርገው ጥረት እና በጦር መሣሪያ መደራጀቷ ለሩሲያ ሉዓላዊነት ያሰጋል በሚል ነጋሪት ጎስመው ጦርነት አውጀው መዋጋት ከጀመሩ አራት ዓመታት ሊቆጠሩ ጥቂት ወራት ቀርተዋል። እ.አ.አ የካቲት 24/2022  ነበር ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጦርነት ዘመቻን የጀመረችው። በሳምንታት  ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ጦርነትም አድማሱን አስፍቶ ቀጥሏል፤ የዜጎች ሰቆቃ እና ቁሳዊ ውድመቱም እንዲሁ። ሁለቱም ሀገራት ‘ተኝተው የሰቀሉት ቆመው ለማውረድ ይችግራል’ የሚባለው አባባል ደርሶባቸዋል።

የዓለም ታሪክ እንደሚያስረዳው አንዲት ሀገር በጦርነት አሸናፊ ብትሆንም ብዙ መስዋዕትነትን ያስከፍላታል። አልያም ደግሞ ሀገርን ከባድ ውጥንቅጥ ውስጥ ካስገባ እና ምትክ የለሹን የሰውልጅ ሕይወት ከቀጠፈ ማግስት በጠረጴዛ ዙሪያ እልባት ያገኛል።

ጦርነት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይዎት እንደ ደረቅ ቅጠል የሚረግፍበት ከመሆኑ ባለፈ የሀገርን ጥሪት ያወድማል። አይረሴ ጠባሳዎችን እንደ ሕዝብ ማድረሱም አይቀርም። ታዲያ ይህ ሁሉ ውድመት የሚታወቀው ጦርነቱ ሲቋጭ ነው። የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ግን ገና አልተቋጨም:: መልኩን እየቀያየረ ተባብሶ ቀጥሏል። ሁለቱም ሀገራት አሉኝ የሚሏቸውን አውዳሚ የጦር መሣሪያዎች በመወራወር ውደመቱ እየከፋ ነው።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የጦርነቱን ሪፖርት በማጠናቀር የሚታወቀው ራሽያ ማተርስ ኦርጋናይዜሽን (russiamatters.org) እንዳስታወቀው ሩሲያ 790 ሺህ ወታደሮቿ ሙት እና ቁስለኛ ሆነዋል:: 50 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ የገቡበት አይታወቅም:: ከዩክሬን በኩል ደግሞ 400 ሺህ  ወታደሮች የሞት እና የመቁሰል አደጋ አጋጥሟቸዋል:: 35 ሺህ የሚሆኑትም የት እንደገቡ ሳይታወቅ ቀርቷል:: የንጹኃን ሞትም  ከሁለቱም በኩል ወደ 15 ሺህ ተጠግቷል::

ግሎባል ኮንፍሊክት ትራከር (www.global-conflict-tracker.org) ላይ ያገኘነው መረጃ ደግሞ ዩክሬን በጦርነቱ ወደ 407 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እርዳታ  ያገኘች ሲሆን ከዚህ ውስጥ  ከ118 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከአሜሪካ የተሰጠ ነው። ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የሀገር ውስጥ መፈናቀል አጋጥሟቸዋል::  ስድስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ደግሞ ከዩክሬን ተሰደዋል። 12 ነጥብ ሰባት  ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ከሩሲያ በኩል 5ሺህ ዜጎች የሀገር ውስጥ መፈናቀል ደርሶባቸዋል:: 800ሺህ ዜጎቿ ደግሞ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ አለመረጋጋት ሀገራቸውን ጥለው ወደ ሌላ ሀገራት ተሰደዋል:: የራሽያ ማተርስ ኦርጋናይዜሽን መረጃ እንደሚያትተው ዩክሬናዊያን በመጋቢት እ.አ.አ 2024 በሩሲያ ኢነርጅ ኃይል ላይ ባደረሰችው ጉዳት 60 ቢሊዮን ሩብል ወይም 714 ሚሊዮን ዶላር ጉዳት ደርሶባታል:: በዩክሬን በኩል ሩሲያ ባደረሰችባት ድብደባ 60 በመቶ የሚሆነው የዩክሬን የጋዝ ማምረቻ ወድሟል:: የዩክሬን የኢኮኖሚ እድገት ከዜሮ በታች 22 ነጥብ ስድስት በመቶ ደርሷል::

ብዙ የዓለም ሀገራት በተለይም ምዕራባዊያን  የሩሲያን ድርጊት አጥብቀው ተችተዋል። ሩሲያ ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሳለች በሚል ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባታል:: የዩክሬንን ሉዓላዊነት ደፍራለች በሚልም ምዕራባዊያን ሩሲያን ከሚቆጣጠሩት የዓለም ገበያ ለማስወጣት ሞክረዋል:: በሩሲያዊያን ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠሩ የማዕቀብ መዓት አውርደውባቸዋል::

ታዲያ ይህ ሁሉ ነገር ሩሲያን ያወጀችውን ዘመቻ እንድታቆም አላደረጓትም:: አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገሮች ዩክሬንን  በጦር መሣሪያ እና በኢኮኖሚ ድጋፍ እያደረጉላት፣ ሩሲያን ደግሞ በየጊዜው የኢኮኖሚ ማዕቀብ እየጣሉባት ወደ አራተኛው የጦርነት ዓመታቸው እየተቃረቡ ነው።

የቅርብ ጊዜዎቹ የአሜሪካ ማዕቀቦች የሩሲያን ሁለት ትላልቅ የነዳጅ ኩባንያዎችን እና ስርጭቶቻቸውን የሚያደናቅፉ ናቸው:: የሩሲያን የጦር ፋይናንስ (ሉኮይል) ለማደናቀፍ የታቀዱ አዳዲስ የአሜሪካ ማዕቀቦችን ተከትሎ ድርጅቱ ዓለም አቀፍ ንብረቶቹን እንደሚሸጥ ተናግሯል:: ሉኮይል በአፍሪካ፣ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ (ብሎምበርግ) ዙሪያ ንግዶች አሉት።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን እንደሚያስቆሙት በተደጋጋሚ ቃል መግባታቸው ይታወሳል። ቃል ከመግባት ባለፈም ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በአሜሪካዋ አላስካ ግዛት ተገናኝተው መክረዋል። ይህም የጦርነቱን ፍጻሜ ያበስራል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር፤ አልተሳካም እንጅ:: ዩክሬን ክሬሚያን እንደ ሩሲያ ግዛት ዕውቅና መስጠትን ጨምሮ ዩክሬን ስምምነት እንድታደርግ አሜሪካ ጫና አድርጋለች። ይሁን እንጂ ጠብ የሚል ውጤት ሳይገኝበት ጦርነቱ ተባብሶ ቀጥሏል::

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ጦርነቱ በአብዛኛው በደቡብ እና በምሥራቅ ዩክሬን ክልሎች ውስጥ ቀጥሏል። ባሳለፍነው ዓመት የሩሲያ ጦር ኃይሎች የሚቆጣጠሩትን ግዛት ቀስ በቀስ በማስፋፋት በተለይም በዩክሬን ምሥራቃዊ ክፍል በቅርብ ጊዜ በኪየቭ እና በሌሎች ከተሞች የአየር ድብደባውን ቀጥለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን አሜሪካ ሠራሹን ቶማሃውክ የተባለውን የረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ የጦር መሣሪያ መፈለጓ የተሰማውም ከሰሞኑ ነው። ሆኖም አሜሪካን እና ሩሲያን ግጭት ውስጥ ሊያስገባ ስለሚችል ትራምፕ ሚሳኤሉን ከመስጠት ይልቅ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱን ባለበት አቁመው በንግግር መፍትሔ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ቶማሃውክ በከፍተኛ ፍጥነት የሚመወነጨፍ አውዳሚ የጦር መሣሪያ ነው። ከመሬት በ10 ሜትር ከፍታ ርቀት ስለሚጓዝ በቀላሉ ማክሸፍ አይቻልም። ሚሳኤሉ ዒላማ በመምታትም ይታወቃል። አቅጣጫን የመከተል ብቃቱ አስተማማኝ ነው። ቶማሃውክ በሺዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን ይይዛል። እንዲህ ያሉ የጦር መሣሪያዎች ደግሞ ለዩክሬን መልሶ ማጥቃት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

በተያያዘም የዩክሬንን የቶማሃውክ ሚሳኤል ይሰጠኝ ጥያቄን ተከትሎ ሩሲያ በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀስ ቡሬቬስኒክ የተባለ ክሩዝ ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን የሀገሪቷ ከፍተኛ ጄነራል ከሰሞኑ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። ሚሳኤሉ ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ ኪሎሜትር ድረስ እንደሚጓዝ እና በሩሲያ የትኛውም ክፍል ለማረፍ እንደሚችል እንዲሁም አሜሪካ ድረስ ያሉ ዒላማዎችን የመምታት አቅም እንዳለው ታውቋል። ሚሳኤሉ ከመሬት ከ50 ሜትር እስከ 100 ሜትር ከፍታ ድረስ ዝቅ ብሎ መብረር ይችላል። ለአየር መከላከያ ሥርዓቶች ቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑም ይነገርለታል።

በሌላ በኩል የአውሮፓ ምክር ቤት የዩክሬንን ከ2026 እስከ 2027 አስቸኳይ የገንዘብ ፍላጎቶችን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን ለምክክርም ያመቸው ዘንድ ለምክርቤቱ አባል ሀገራት ጥሪ አቅርቧል::

የሁለቱን ሀገራት ጦርነት  ዘርፈ ብዙ ዓለም አቀፍ ጫናን አስከትሏል። ለኑሮ ውድነቱ መንስኤ ስለመሆኑም ነው የሚነገረው። ለአብነትም ከሰሞኑ በተናጠል የትራምፕ አስተዳደር በሩሲያ የኃይል አቅርቦት (ኢነርጂ) ላይ የጣለውን አዲስ ማዕቀብ ተከትሎ የዓለም የነዳጅ ዋጋ አምስት በመቶ ጨምሯል። የሕንድ ማጣሪያዎች የአሜሪካን ማዕቀብ ተከትሎ ወደሀገር ውስጥ የሚገቡ የሩሲያ የዘይት ምርቶችን ለመቀነስ ማቀዳቸውን ስማቸው ያልተጠቀሰ የኢንዱስትሪ ምንጮችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here