ኢንስቲትዩቱ የጤና ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው

0
11

የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልሉን የጤና ተቋማት ቤተ ሙከራዎች (ላብራቶሪዎች) አቅም በመገንባት ጥራት ያለው፣ ተደራሽ እና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በማቅረብ  የክልሉን ማሕበረሰብ የጤና ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል::

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንደገለጹት የቤተ ሙከራ አገልግሎቶች የሁሉም ጤና ሥርዓቶች አስፈላጊ እና መሠረታዊ ነገሮች ናቸው:: በበሽታ ምልክቶች ብቻ ተመርኩዞ ሕክምና መስጠት ታማሚዎችን ለከፋ ጉዳት ስለሚዳርግ ናሙናዎችን ወስዶ በቤተ ሙከራ ምርመራ ማድረግ ግዴታ ነው:: ለዚህ ደግሞ ቤተ ሙከራዎችን ጥራታቸውን ተቆጣጥሮ  የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግም ተገቢ ነው::

እንደ አቶ በላይ ገለጻ ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ዋና ዓላማዎች መካከል አንዱ በክልሉ የቤተ ሙከራ አቅም ግንባታ በማጠናከር የበሽታ ልየታ፣ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ እንዲሁም የሕክምና አገልግሎቱ እንዲሻሻል ማስቻል ነው:: ይህ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ያሉ የጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ የላብራሪ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል፤ ይህ ተግባርም እየተገበረ ይገኛል ነው ያሉት::

በተጨማሪም በክልሉ የጤና ተቋማት ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በማሰልጠን፣ የቤተ ሙከራ  አገልግሎት የትግበራ መመሪያዎችን  በማዘጋጀት፣ ከጤና ጣቢያ እስከ ክልል የሪፈራል ላብራቶሪ ምርመራ በመዘርጋት፣ የጥራት ቁጥጥር ማዕከላትን በማቋቋም፣ የላብራቶሪ አቅምን ለማጎልበት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል::

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ስሜነህ አያሌው በበኩላቸው የክልሉ የሕክምና ላብራቶሪ አገልግሎት ተደራሽነን ለማስፋፋት እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ደግሞ የጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን የጤና ተቋማትን በማስተሳሰር በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ነው የጠቆሙት:: በተሠራው መልካም ተግባርም የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለተከታታይ አምስት ዓመታት በISO-15189 መስፈርት ተመዝኖ የሙሉ ዕውቅና ዋንጫ አግኝቷል፤ አገልግሎቱን የበለጠ በማሳደግ በአዲሱ መስፈርት ISO-15-2022 መሠረትም በቅርቡ ተመዝኖ ዕውቅና አግኝቷል::

እነዚህ ውጤቶች ቢገኙም የሕክምና ግብአት አቅርቦት ችግር፣ በየደረጃው የሚታየው የሰው ኃይል እጥረት፣ የረጅ ድርጅቶች ተሳትፎ እየቀነሰ መምጣት እና የክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ችግር በአገልግሎቱ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው፤ ችግሩን ለመፍታትም የባለድርሻ አካላትን  ትኩረት እንደሚፈልግ አቶ ስሜነህ ተናግረዋል::

4ኛው ክልላዊ የሕክምና ላብራቶሪ ፌስቲቫል ጠንካራ የላብራቶሪ ስርዓት ጥራት ላለው የጤና አገልግሎት በሚል መሪ ሐሳብ በባሕር ዳር ከተማ ከሰሞኑ ተካሂዷል፤ በክልሉ የሚገኙ የግል ሆስፒታሎችን ጨምሮ ዐሥራ ስምንት የሕክምና ተቋማት በዓለም አቀፉ የላብራቶሪ የጥራት መስፈርት ተመዝነው ዕውቅና አግኝተዋል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here