ሰዎች ከቁጥጥራቸው ውጭ በሆነ ሁኔታ ሰውነታቸው እንዲንቀጠቀጥ የሚያደርገው የፓርኪንሰን ሕመም ስርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል።
ፓርኪንሰን ፔሸንት ሳፖርት ኦርጋናይዜሽን የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ለ35 ሐኪሞች በባሕር ዳር ከተማ ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስለ ፓርኪንሰን ሕመም ከሰሞኑ የሁለት ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷል።
ስልጠናውን የሰጡት በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነርቭ ክፍል ኃላፊ እና የነርቭ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ማቲያስ አዱኛ እንደገለጹት የፓርኪንሰን በሽታ ውስብስብ እና አልፎ አልፎም በቅጡ መረዳት የሚያዳግት ሕመም ነው። በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎችን ለችግር ያበቃ በሽታም ነው።
ዶ/ር ማቲያስ እንዳሉት የፓርኪንሰን በሽታ የነርቭ ሥርዓት እንቅስቃሴ መዛባት ሲሆን ቀስ በቀስም ሥር እየሰደደ እና እየተባባሰ የሚሄድ በተለይም የአካል እንቅስቃሴን የሚቆጣጠረውን የአንጎል ክፍል የሚያጠቃ እና ከነርቭ ሥርዓት መታወክ ጋራ የተዛመደ የጤና ችግር ነው።
በሀገሪቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ ስለፓርኪንሰን በሽታ ያለውን የግንዛቤ እጥረት እና በሕክምና ተቋማት ካለው የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች በመነሳት የፓርኪንሰን ፔሸንት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ (ፓፔሳኦኢ) በጎ አድራጎት ድርጅት በ2004 ዓ.ም በአንዲት የፓርኪንሰን በሽታ ተጠቂ ሰው ተመሠረተ።
የድርጅቱ አስተባባሪ የአብሥራ ዘላለም እንደገለጹት በኢትዮጵያ ስለፓርኪንሰን በሽታ በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ እንዲሁም የአዕምሮ እና የነርቭ ጤና ሐኪሞች በቂ ባለመሆናቸው ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ እንኳ በምርመራ የሚረጋገጠው በሽታው ከጀመራቸው ከሦስት እና ከአራት ዓመት በኋላ ነው። ይህም በሽታው በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ በመሆኑ ሕክምናውን አስቸጋሪ ያደርገዋል። በመሆኑም ሥልጠናው ለጠቅላላ ሐኪምች መሰጠቱ ሕመሙን በጊዜ ተረድተው በሚገባው ልክ ሕሙማንን ለማገዝ ያስችላቸዋል።
የፓርኪንሰን በሽታ አንዴ ከጀመረ በኋላ እስከ ሕይዎት ፍጻሜ አብሮ የሚኖር በመሆኑ ስር ሳይሰድ በጊዜ በሽታው ተለይቶ ሕክምና መጀመር ይገባል።
የፓርኪንሰን በሽታ የእጅ ወይም የእግር መንቀጥቀጥ፣ የጡንቻ መጠንከር (እንደፈለጉ ማንቀሳቀስ አለመቻል)፣ የሰውነት እንቅስቃሴ መቀነስ፣ በጊዜ ሂደትም ለመናገር መቸገር፣ ድባቴ እና የእንቅልፍ ማጣት እንዲሁም የማስታወስ ችሎታን ያዳክማል። በተጨማሪም የሰውነት ሚዛንን በማሳት መውደቅን ያመጣል፡፡
የፓርኪንሰን በሽታ መንስኤዎች በውል ባይታወቁም የሚከሰተውም ዶፓሚን የሚያመርቱ ሕዋሳት ሲያንሱ ወይም ሲያረጁ ነው። ዶፓሚን ሰውነታችን የእንቅስቃሴ ቅንጅት እንዲኖረው የሚያደርግ ኒውሮ ትራንስሚተር (የነርቭ ሕዋሳት መልዕክት አስተላላፊ) ነው።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

