ዘንድሮስ ይሳካላቸዉ ይሆን?

0
233

አዲሱ የወንዶች ከፍተኛ ሊግ የውድድር ዓመት ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በጂማ እና በሀዋሳ ከተሞች ተጀምሯል፡፡ ምድብ “ሀ” በሀዋሳ እየተደረገ ሲሆን ምድብ “ለ” ደግሞ በጅማ ነው እየተከናወነ ያለው፡፡ 20 ክለቦች በሚሳተፉበት በዚህ መድረክ ደሴ ከተማ እና ደብረብርሃን ከተማ ከአማራ ክልል እየተሳተፉ የሚገኙ ክለቦች ናቸው፡፡

 

አምና የምድብ ሁለት ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ደሴ ከነማ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ዓመቱን የጨረሰው፡፡ አስደናቂ የውድድር ዓመት ባሳለፈበት የ2017 ዓ.ም ክለቡ በሁሉም የሜዳ ክልል የተዋጣለት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ቡድኑ ጠንካራ የኋላ ክፍል የነበረው ሲሆን በሊጉ አነስተኛ ግቦች የተቆጠሩበት ቀዳሚው ክለብ ነበር፡፡ የፊት መስመሩም ቢሆን በርካታ ግቦችን ካስቆጠሩ ቡድኖች መካከል አንዱ እንደነበር ቁጥራዊ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ክለቡ አምና የነበረውን ክፍተት በመሙላት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ በክረምቱ የዝውውር ወቅት በንቃት ተሳትፏል፡፡ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ በፕሪሚየር ሊጉ የሚያሳተፈውን ውጤት ይዞ ለመጨረስ ጠንካራ ዝግጅት አድርጎ የውድድር ዓመቱን ጀምሯል። ክለቡ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን በመቅጠር፣ 12 አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል እና የነባር ተጫዋቾችን ውል በማደስ በደብረዘይት ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በማድረግ ነው ወደ ጅማ ያቀናው፡፡ የክለቡ ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ተስፋ ለአሚኮ ስፖርት ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት ክለቡ የ2017 የውድድር ዓመት እንዳበቃ በቀጥታ ወደ ዝግጅት መግባታቸውን አስታውሷል፡፡ “ለ2018 የውድድር ዓመት የተሻለ ቡድን ለመገንባት ዝግጅታችንን ቀደም ብለን ነው የጀመርነው” ብሏል።

ባለፈው ዓመት በአራት ጨዋታዎች ብቻ ተሸንፎ ሊጉን በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ደሴ ከተማ  ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እቅድ ይዟዋል፡፡  “በከፍተኛ ሊግ ስኬት ነው የሚባለው ወደ ፕሪሚየር ሊግ ስታድግ ብቻ ነው” በማለት የዘንድሮው  እቅዳቸው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደግ መሆኑን የክለቡ ቴክኒካል ዳይሬክተር ተናግሯል።

ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ክለቡ በአጨዋወት ስልቱም  ለውጥ ማድረጉን ቴክኒካል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። “ደሴ ከተማ በደንብ ከኳስ ጋር የተዋሀደ፣ በኳስ ቁጥጥር የሚያምን፣ ማራኪ የአጨዋወት ዘይቤ የሚከተል ቡድን መሆኑን ያስረዳው አቶ አብርሃም ሊጉ የሚፈልገውን ጉልበት እና ፍጥነት ለማስተካከል ብዙ ሥራዎችን ሠርተዋል። በቀጣይ እቅዳቸውን ለማሳካት የደጋፊዎች  እገዛ እንደሚያስፈልጋቸውም የክለቡ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ተናግረዋል፡፡

ደብረ ብርሃን ከነማ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ለበርካታ ዓመታት የቆየ ክለብ ነው፡፡ ቡድኑ ባለፈው ዓመት በ33 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዞ መጨረሱ አይዘነጋም፡፡ ከተቆጠረበት ግብ የበለጠ ግብ አለማስቆጠሩ በሁሉም የሜዳ ክፍል ደካማ እንደነበር ቁጥሮች ያመለክታሉ፡፡ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ኃይለየሱስ ጋሻው ከአሚኮ ስፖርት ጋር ባደረጉት ቆይታ ክለቡ ካለፈው ዓመት ስህተቶች በመማር እና የተሻለ የተጫዋቾች ስብስብ በመገንባት ፕሪምየር ሊጉን የመቀላቀል እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ክለብ ባለፈው የውድድር ዘመን በምድቡ አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ምንም እንኳ ውጤቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ከፉክክሩ ግን በጊዜ መሰናበቱ በደጋፊዎች እና በክለቡ አመራሮች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ አልፏል። ይህንን ታሪክ ለመቀየር ዘንድሮ ቆርጦ መነሳቱን  አሰልጣኝ ኃይለየሱስ ይናገራል። ‹‹ደብረ ብርሃን ከተማ እግር ኳስ ክለብ ካለፈው ዓመት የተሻለ አቅም ይዞ ለመቅረብ እና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ነው እየሰራን ያለነው›› ያሉት አሰልጣኙ  “የቡድን ግንባታው ሂደት ላይ ትኩረት አድርገን ነው ዓመቱን የጀመርነው” ብለዋል። የተጫዋቾቹ ተነሳሽነት ጥሩ መሆኑን አሰልጣኝ ኃይለየሱሱ ተናግሯል፡፡

ይሁን እነጂ ልክ እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም ክለቡ በቂ የዝግጅት ጊዜ እንዳላገኘ አሰልጣኝ ኃይለየሱስ ሳይጠቅሱ አላለፉም። ‹‹በዘንድሮው ዓመት የዝግጅት ጊዜያችን አጭር ቢሆንም በተቻለን አቅም ግን ያለውን ጊዜ አጣበን ውጤት ለማምጣት እየሰራን ነው›› ብለዋል። የዝግጅት ጊዜው ያጠረው ችግሩ ከክለቡ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ አስተዳደራዊ ጉዳዮች የተነሳ መሆኑን ጠቁመዋል።  የደብረ ብርሃን ከተማ ክለብ ባለፈው ዓመት ያጠናቀቀበት ደረጃ እና ዘንድሮ የተደለደለበት ምድብ ሲታይ ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠብቀው አያጠያይቅም። አሰልጣኝ ኃይለየሱስም ይህንን በሚገባ የተረዱ ይመስላል። ዘንድሮ ከዛ በተሻለ ውጤት ለማምጣት የተሻለ ሥራ እየሠራን ነው ያሉትም ለዚህ ነው፡፡

የዘንድሮው ምድብ ጠንካራ መሆኑን የጠቀሱት አሰልጣኙ ‹‹በእኛ ምድብ ያሉ ቡድኖች ተፎካካሪ ናቸው፤ ደስ የሚል ምድብ ነው ያለው›› በማለት ለፈተናው ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል። ለዚህም ተገቢውን ዝግጅት አድርገው የውድድር ዓመቱን ጀምረዋል፡፡ ሁለቱ የአማራ ክልል ክለቦች በመጀመሪያ ሳምንት የከፍተኛ ሊግ ውድድር እርስ በእርስ የተገናኙ ሲሆን ደሴ ከተማ ሁለት ለባዶ አሸንፏል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here