ብራዚሊያዊው የ2018 እ.አ.አ ስሪት የሆነ ተሽከርካሪውን ከከተማ ራቅ ካለ ገጠራማ ቀጣና አውጥቶ ከመድን ካሳ ለማግኘት ሆን ብሎ በእሳት ማያያዙ በማስረጃ መረጋገጡን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት አስነብቧል::
በጥቅምት ወር መግቢያ ወደ ቀጣናው የፖሊስ ጽ/ቤት ጐራ ያለ አንድ ሰው የታጠቁ ሰዎች አስገድደው ወስደው “ላፓ” በተሰኘው ስፍራ አስቁመው ሊገድሉት እንደነበር እና ተሽከርካሪውን በእሳት ማቃጠላቸውን ሪፖርት ያደርጋል:: ግለሰቡ ተሽከርካሪውን ሲያቃጥሏት እሱንም እሳት ሲለበልበው ባሰማው ጩኽት አልፎ ሂያጅ መንገደኞች ደርሰው እንዳተረፉት ነው በሪፖርቱ ያስታወቀው- ለፖሊስ::
አቤቱታውን የሰሙት ፖሊሶችም “የጥቃቱ አድራሾች ምክንያታቸው ምንድን ነው? ምን ይመስልሃል?” ሲሉ ላቀረቡለት ጥያቄ መነሻቸው ምን እንደሆነ እንደማያውቅ አስረድቷል::
ፖሊስም የደረሰውን አቤቱታ ይዞ መርማሪ ቡድን አዋቅሮ ተሽከርካሪዋ “በእሳት ተያያዘች” ወደ ተባለበት ስፍራ ያመራል:: በቦታው እንደደረሱ በተወሰነ ዙሪያ ቀጣና አሰሳ ሲያደርጉ የእንቅስቃሴ መቅረጫ ቪዲዮ ካሜራ (ሲሲቲቪ)መኖሩን ይደርሱበታል::
የቡድን አባላቱ ጊዜ አላጠፉም፤ የተቀረፀውን ምስል ወደ ኋላ አጠንጥ ነው በጥንቃቄ መመልከት ሲጀምሩ- ያዩትን ማመን ያቅታቸዋል::
“ፖርሽ” የተሰኘውን ዘመናዊ ተሽከርካሪ ሲሾፍር የነበረው ሰው ተክለሰውነት እና የለበሰው ልብስ ሳይቀር እሳት ካያያዘው ሰው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ደረሰበት- ቡድኑ::
ቡድኑ በዚህ አላቆመም “ለምን?” የሚል ጥያቄ አነሱ:: በገዛ እጁ የራሱን ተሽከርካሪ በእሳት ለማቃጠል መነሻው ምን ይሆን? ምርመራውን ቀጠሉ::
በመጨረሻም “ጂግሎቦ” ከተሰኘ ድርጅት ባገኙት መረጃ ተሽከርካሪው ከተገዛበት 2018 እ.አ.አ ጀምሮ ያልተከፈለ የግብር እዳ አለበት::
ግለሰቡ የግብር እዳ ያለበትን ተሽከርካሪ መሸጥ ስለማይችል በማቃጠል ከመድን በሚያገኘው ካሳ ለማካካስ ነበር ህልሙ- “አተርፍ ባይ…” ሆነ እንጂ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


