በቱርክ ኢስታንቡል የነበሩ ባለትዳሮች በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ ፍቺ ሲፈጽሙ ባልየው የነበሯቸውን ሁለት ድመቶች የማሳደግ ኃላፊነቱን ለሚስቱ ማስተላለፉን እና ማሳዳጊያ አበል በየሦስት ወሩ 240 ዶላር ለመክፈል ግዴታ መግባቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::
ድረ ገጹ እንዳስነበበው ለፍርድ ቤት ባቀረቡት ማመልከቻ አለመጣጠም እና የጋብቻቸው መሰረት መበላሸቱን ጠቅሰዋል:: በዚህም አንዳቸውም ከሌላው ምንም ዓይነት ካሳ ወይም የገንዘብ ድጋፍ አለመጠየቃቸው ነው በፍቺ ውላቸው ላይ የሰፈረው:: ይሁን እንጂ ለየት ያለ አንድ ፍሬ ነገር ሰፍሯል “ባልየው የሁለቱን ድመቶቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነት ለሚስቱ እንደሚያስተላልፍ እና ማሳደጊያ ገንዘብ መክፈል አለበት::” የሚል በፍቺ ስምምነታቸው መሰረትም ልክ እንደ ልጆች ማሳደጊያ ድጋፍ ባል በየሦስት ወሩ 240 ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል:: ባል የሚከፍለው የድመቶች ማሳደጊያ በየጊዜው ከሚኖረው የዋጋ መጨመር ጋር የዶላር ከምንዛሬ መዋዠቅ እንደሚሰላም ነው የሰፈረው::
ሁለቱ የጋራ “ሀብት” የሆኑት ድመቶችም በቀድሞዋ ሚስት ዘንድ ማንኛውም አስፈላጊ ሁኔታ ማለትም ምግብ፣ መኝታ እና የፅዳት እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሚቆዩ በፍቺ ስምምነት ውላቸው ሰፍሯል::
በቱርክ በፍቺ ስምምነት ውል ላይ የሰፈረ አዲስ ዓይነት የማሳደጊያ አበል ክፍያ መሆኑን ያስነበበው ድረ ገጹ ፍቺ ከተፈፀመ በኋላ ለቤት እንስሳት የገንዘብ ድጋፍ መደረግ እንደሚኖርበት ያመላከተ ፋናወጊ መሆኑም ነው የተሰመረበት- በድረ ገጹ:::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


