ከሁለት ዓመታት በላይ በሰላም እጦት ውስጥ የሚገኘው የአማራ ክልል ችግሩ የትምህርት ዘርፉን እየፈተነው ነው:: በእነዚህ ሁለት ዓመታት ሰባት ሚሊዮን ያህል ተማሪዎች ከትምህርት ርቀዋል፤ መምህራን በነጻነት እንዳያስተምሩ ሆነዋል:: ከሁለት ሺህ በላይ የትምህርት ተቋማት ደግሞ ለጉዳት ተዳርገዋል::
ባለፉት ዓመታት በትምህርት ሥራው ላይ ያጋጠመው መስተጓጎል እንዲያበቃ፣ በ2018 የትምህርት ዘመንም በእነዚያ ዓመታት የታጣውን የትምህርት ሥራ ውጤት ለማካካስ ወደ ሥራ ተገብቷል:: ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን ተማሪዎች በዓመቱ ተመዝግበው እንደሚማሩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል:: የተማሪ ምዝገባውም ነሐሴ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ቢጀመርም በተቀመጠው የምዝገባ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አልተቻለም፤ እስከ መጀመሪያው ሩብ ዓመት ጊዜ ድረስም የተማሪ ምዝገባው አልተጠናቀቀም::
በክልሉ የሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች ትምህርት የጀመሩት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲያጠናቅቁ፣ ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማብቃት ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ:: ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎንም ወደ ትምህርት ያልመጡ ተማሪዎችን ለመመለስ ትኩረት አድርገዋል::
ትምህርት ቤቶች ነፃ የመማር ማስተማር ሥራ የሚካሄድባቸው፣ ህፃናት በነፃነት ዕውቀት የሚቀስሙባቸው፣ ተተኪ ትውልድ የሚፈጠርባቸው፣ ሀገርን የሚረከብ በዕውቀት የዳበረ ትውልድ የሚፈራባቸው ተቋማት መሆናቸውን በማሳት ሐሳባቸውን ያጋሩን የሰሜን ሜጫ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተዋቸው በቀለ ናቸው:: የትምህርትን ጥራት፣ ሽፋን እና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑም አስታውቀዋል::
ኃላፊው እንዳሉት ወላጆች ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል:: የትምህርት ባለሙያውም የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለበት:: ከዚህ ባሻገር የትምህርት ተቋማትን በግብዓት እና በትምህርት ቁሳቁስ የማበልጸግ ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን ነው የጠቆሙት::
ባለፉት ሁለት ዓመታት በትምህርት እንቅስቃሴው ዝቅተኛ አፈጻጸም ያስመዘገበው የምዕራብ ጎጃም ዞን አንዱ ነው፤ የ2018 የትምህርት ዘመንን ደግሞ ማካካሻ ለማድረግ ዕቅድ ይዟል:: እንደ ዞኑ ትምህርት መምሪያ መረጃ በዞኑ በሚገኙ 600 ትምህርት ቤቶች 426 ሺህ 29 ተማሪዎች በትምህርት ዘመኑ ይማራሉ ተብሎ ይጠበቃል::
ይሁን እንጂ እስከ ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 89 ሺህ 738 ተማሪዎች ብቻ በትምህርት ላይ እንደሚገኙ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ የስጋት ደሴ አስታውቀዋል::
በዞኑ አሁንም ድረስ 336 ሺህ 229 ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መሄድ እንደናፈቁ ናቸው:: በመሆኑም ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን መመለስ የቀጣይ ትኩረት መሆኑን አቶ የስጋት ገልጸዋል:: ተማሪዎችን ከመመዝገብ በተጨማሪ ኅብረተሰቡን፣ አጋር እና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ጉዳት የደረሰባቸውን 161 ትምህርት ቤቶች መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል::
በተመሳሳይ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና ቁልፍ ሥራዎች ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ በደጀን ከተማ አካሂዷል:: የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ጌታሁን ፈንቴ እንዳስታወቁት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ተገቢው መግባባት ቀድሞ ቢፈጠርም የሚፈለገው ውጤቱ አልተገኘም::
በትምህርት ዘመኑ 790 ሺህ 474 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ ቢያዝም ውይይቱ እስከተካሄደበት ጊዜ ድረስ ማሳካት የተቻለው ግን 140 ሺህ 129 ተማሪዎችን ብቻ ነው:: ይህም የዕቅዱ 17 ነጥብ 7 በመቶ ያህል ብቻ ነው::
አሁንም ከ659 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቶቻቸው ጋር አልተገናኙም፤ የጸጥታ ችግሩ 824 ትምህርት ቤቶች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዳይመለሱ ማድረጉም ተጠቁሟል::
ወደ ትምህርት ገበታ ያልተመለሱ ተማሪዎችን መመለስ እና ያልተከፈቱ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ መሥራት የቀጣይ ትኩረት መሆኑንም መምሪያ ኃላፊው አስታውቀዋል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን ከደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ወልዲያ ከተማ አስተዳደር የትምህርት አመራሮች ጋር ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ገምግሟል:: በዚህ ወቅት የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ መኳንንት አደመ ትምህርት የለማ የሰው ኃይል በማፍራት እንደ ሀገር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል::
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክልሉ ትምህርት እየተፈተነ መሆኑን አስታውቀዋል:: ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባለው የክልሉ የሰላም እጦት ምክንያት ከስድስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ጠቁመዋል:: በዘርፉ ላይ የደረሰው ችግር የትምህርት ጥራት እና ተወዳዳሪነት ችግር ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል ብለዋል::
ችግሩ አሁንም ድረስ መፍትሔ ሳያገኝ ቀጥሏል፤ በርካታ ታማሪዎችም ከትምህርት ገበታ እንደራቁ ነው:: ለአብነትም በዚህ ዓመት መዝግቦ ለማስተማር ከታቀደው የተማሪ ቁጥር ውስጥ በሩብ ዓመቱ ማሳካት የተቻለው ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ተማሪዎችን ብቻ ነው:: ይህም የዕቅዱን 52 በመቶ እንደ ማለት ነው:: በክልሉ በትምህርት ዘመኑ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር በዕቅድ መያዙን ልብ ይሏል::
ቀሪ 42 ከመቶ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ አሁንም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ምትል ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል:: ሁሉም ተማሪዎች እንዲመዘገቡ ከማድረግ በተጨማሪ የተመዘገቡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል::
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ ተዘግተው በከረሙ ትምህርት ቤቶች የተፋጠነ የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን አስታውቀዋል:: ይህም የባከነውን የታዳጊዎች ዕድሜ የሚያካክስ እንደሆነ ነው የጠቀሙት:: ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ አንዱ መፍትሔ መሆኑንም አስታውቀዋል:: በወቅታዊ የሰላም መደፍረሱ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቀው ትምህርት በትውልድ ቅብብሎሹ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳርፍ የትምህርት አይነቶች ወደ አምስት ዝቅ እንዲሉ መደረጉንም ተናግረዋል::
ሕዝቡ ትምህርትን አጀንዳ እንዲያደርግ የተሠራው ሥራ መልካም ውጤት ማስገኘቱን የጠቆሙት ዶክተር ሙሉነሽ በቀጣይም ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሁሉም በጋራ እንዲሠራ ጠይቀዋል::
ግዕዝ በአማርኛ
ከግእዝ የተወሰዱ የአማርኛ ቃላት
መንፈስ
ድምጽ
መክሊት
አራዊት
መቅሰፍት
ቀቢጸ ተስፋ
አእምሮ
ጉባኤ
ምንጭ፡- አልፋ ግእዝ
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


