የዓሣ ሃብታችን ሲቃኝ

0
83

በሀገራችን 200 ያህል የዓሳ ዝርያዎች ይገኛሉ:: አማራ ክልል ደግሞ የአብዛኛዎቹ የዓሳ ዝርያዎች መገኛ ነው፤ ከአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው በሀገራችን ከሚገኙት የዓሳ ዝርያዎች ውስጥ 18ቱ በአማራ ክልል ብቻ ይገኛሉ::

ክልሉ ያለውም የኣሳ ሀብት መሠረት በማድረግ ታዲያ ለበርካቶች የሥራ ዕድልን የፈጠረ ዘርፍ ሆኗል ፤ ባሕር ዳር ከተማም በዓሳ ሀብት ከሚታወቁት መካከል አንዷ ናት:: ወ/ሮ ዓለምናት ሙጨ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ ሽንብጥ ቀበሌ ነዋሪ እና ዓሳ በማዘጋጀት እና በመሸጥ ከተደራጁ 46 ሴቶች ውስጥ እንዷ ናቸው::

በማሕበሩ የሥራ ቦታ ተገኝተን እንደታዘብነው የማሕበሩ አባላት (ሁሉም ሴቶች መሆናቸውን ልብ ይሏል) ጠዋት በመገኘት አስጋሪዎች የሚያመጡትን ዓሳ አጥበው በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች እና ድርጅቶች ያስረክባሉ::

ጣና ሐይቅ እና ዓሳ የኑሮ መሠረታችን ነው፤ የሚሉት ወ/ሮ ዓለምናት ሴቶቹ በአንድ ቀን ከ30 ኪሎ ያላነሰ ዓሳ አዘጋጅተው ለተጠቃሚው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፤ እርሳቸው እንደሚሉት በተለይም ቀይ (አምባዛ)፣ ነጭ እና ቀረሶ የሚባሉት የዓሳ ዝርያዎች በገበያው በጣም ተፈላጊ ምርቶች ናቸው::

ሌላዋ የማህበሩ አባል ወ/ሮ ዘውዴ አላምረው 2016 ዓ.ም የተመሰረተው ማህበራቸው  በጋራ የሚሠሩበት አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል:: በሥራው 4 ልጆችን ያስተዳድሩበታል:: ማህበራቸው ከአስጋሪዎች በመረከብ በማጠብ እና በማዘጋጀት ለተመጋቢም ለሆቴሎችም ምርቱን በጥራት ያቀርባሉ ምርቱ ከወቅት ወቅት ቢለያይም ምርቱ ሲቀንስ ደግሞ በጣም እንደሚያሳስባቸው ነው የሚገልፁት::

በአማራ ክልል እንስሳት እና  ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ የዓሳ ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ አበበ ፈንታሁን  ክልሉ የበርካታ ኃይቆች፣ ወንዞች፣ የአርሶ አደር ኩሬዎች እና ግድቦች ባለቤት መሆኑን ያነሳሉ፤ ከፍተኛ የዓሳ ምርት የሚመረትበትም ነው:: እንደ ባሙያው ማብራሪያ በክልሉ 312 ሺህ ሄክታር በሚሸፍን የውኃ መሬት ላይ የዓሳ ማስገር ሥራ ይከናወናል፤ ከዚህም 38 ሺህ 372 ቶን የዓሳ ምርት ይመረትበታል::

በክልሉ ዓሳ በሁለት ዓይነት መንገድ ይመረታል፤ የመጀመሪያው በተፈጥሮ የውኃ አካላት ላይ እና ሁለተኛው ደግሞ በሰው ሠራሽ ኩሬ እና ግድቦች ላይ ነው::

አቶ አበበ እንዳሉት በተፈጥሮ የውኃ አካላት ላይ የሚመረተው ዘላቂ እንዲሆን የዓሳ አስተዳደር ፖሊሲዎች እንዲወጡ (ዘርፉን በፖሊሲ ለማጠናከር)፣ በአዋጅ እና በደንብ እንዲመራ እንዲሁም አስጋሪዎች ትክክለኛ የማስገሪያ መሣሪያ እንዲጠቀሙ ለማድረግ እየተሠራ ነው::

የውኃ አማራጭ ያላቸው አርሶ አደሮች ደግሞ በሰው ሠራሽ መንገድ ኩሬ በማዘጋጀት ለምግብነት እንዲጠቀሙ በትኩረት እየተሠራ ነው፤ ለአብነትም በኩታ ገጠም (በክላስተር) በአንድ ወረዳ 40 አርሶ አደሮች ኩሬ እንዲያዘጋጁ በማድረግ ለዚያ አካባቢ ተስማሚ የዓሳ ጫጩት እንዲጨምር፣ አምርተውም ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሠራቱን አንስተዋል:: ከአንድ ሺህ 500 በላይ አርሶ አደሮች የኩሬ ግብርና እየተገበሩ ይገኛሉም ብለዋል::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የዓሳ ምርቱን ለማሳደግ ባለፈው በጀት ዓመት (2017 ዓ.ም) ከ775 ሺህ በላይ የዓሳ ጫጩት ተባዝቶ ተሰራጭቷል:: በዚህ ዓመት ደግሞ 280 ሺህ የዓሳ ጫጩት ወደ ግድቦች፣ ኃይቆች እና የአርሶ አደር ኩሬዎች ይሰራጫል:: ዘርን ውጤታማ ለማድረግም የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ እንዲገቡ እየተሠራ ይገኛል::

ባሙያው አክለውም የጣና ሐይቅን ጨምሮ በክልሉ ያለውን የዓሳ ሃብት ዘላቂ ለማድረግ በሁሉም አካባቢዎች በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል::

በዘርፉ የዓሳ ማስገር ዝግ ወቅት የሚባል አለ፤ ይህ ወቅት ወላድ ዓሳዎች ለምግብነት እንዳይውሉ  ለማድረግ ይረዳል::

አንዲት ወላድ ዓሳ በእርባታ ወቅት ገበያ ላይ ብትውል በትንሹ 500 ጫጩቶችን /እንቁላል/ በአፏ ውስጥ ትይዛለች፤ ይህ ደግሞ ምርት እንዲቀንስ ያደርጋል:: ይህን ወቅት መሠረት በማድግ እና በጥናት ተመሥርቶ መፍትሔ ለመስጠት አዋጅ መውጣቱንም ባሙያው አስታውሰዋል::

ጣና ሐይቅ ከግንቦት 15 እስከ ሐምሌ 15 ቀን ሙሉ ለሙሉ ከማስገር ዝግ ይደረጋል፤ ይህ ወቅት ይላሉ ባለሙያው አቶ አበበ ቀረሶ የሚባለው የዓሳ ዝርያ የሚራባበት ነው:: በተመሳሳይ ከሐምሌ ወር መጀመሪያ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ደግሞ የጣና ገባር ወንዞች ከማስገር ዝግ ይደረጋሉ፤ በዚህ ወቅት ነጭ ዓሳዎች ወደ ወንዞች ተጉዘው እርባታ የሚያካሂዱበት ነው::

ምርቱ ዘላቂ እንዲሆን ታዲያ አንዱ መፍትሔ እና ትኩረት ተደርጎ የሚሠራበት ዝግ ወቅትን ማክበር ላይ ነው፤ ይህን ለማስፈፀም በየቀበሌው የዓሳ አስተዳደር ግብረ ኃይል ተቋቁሟል:: ግብረ ኃይሉ ግንዛቤ ተፈጥሮለት ወደ ሥራ መግባቱን በማንሳት ግረ ኃይሉ ደግሞ ለአስጋሪው በማስገንዘብ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል::

ሁለተኛው የመፍትሔ ተግባር ደግሞ የጫጩት ቁጥር እንዲጨምር ነው:: ለአብነትም ባለፈው ክረምት 325 ሺህ የዓሳ ጫጩት ከባሕር ዳር እና ሌሎች የውኃ ውስጥ ምርምር ማዕከላት ወደ ጣና የመልቀቅ ሥራ ተሠርቷል::

በሌላ በኩል የጣና ኃይቅ የዓሳ ሃብት እየተመናነ ይገኛል የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ይሰማል፤ ባለሙያው አቶ አበበ ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም:: ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ የአስጋሪ ቁጥር መጨመሩን ነው::

አቶ አበበ እንደሚሉት በጣና ኃይቅ በጊዜያዊ እና ቋሚ ከስድስት ሺህ 900 በላይ የዓሳ አስጋሪዎች ይገኛሉ፤ ምርቱ ሲከፋፈል ታዲያ ቀነሰ ሊባል እንደሚችል ነው የገለጹት:: ባለፈው በጀት ዓመትም (በ2017 ዓ.ም) ከ25 ሺህ ቶን በላይ ዓሳ ከጣና ኃይቅ ማምረት ተችሏል ነው ያሉት::

ምርቱ ወደ ማዕከላዊ ገበያ (አዲስ አበባን ጨምሮ) እና ከሃገር ውጭ ደግሞ ሱዳን ድረስ ለሽያጭ እንደሚቀርብ በማንሳት የዓሳ ምርት የገበያ ችግር የለበትም ብለዋል:: ለበርካቶችም የሥራ ዕድል የፈጠረ ዘርፍ መሆኑን አንስተዋል::

አስጋሪው ያሰግራል፣ በመሃል የተደራጁ ፕሮሰስ የሚያደርጉ እና ከነሱ ተረክበው ደግሞ የሚሸጡ አካላት ሰፊ ሰዎች (የሥራ ዕድል) የፈጠረ እና ሰፊ ምርት ያለበት ክልል አንደሆነም ገልፀዋል::

የገበያ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናር የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው፤ ለምሳሌ በብዛት ዓሳ የሚመረትበትን ተከዜ በሰፊው በማስተዋወቅ አዲስ አበባ ድረስ ምርቱን ተረካቢ ማግኘት መቻሉን ነው የገለፁት::

የተፈጥሮ የውኃ አካላትን በአግባቡ መምራት፣ ግድቦችን ለይቶ የዓሳ ጫጩት ማሰራጨት የዚህ በጀት ዓመት ትኩረቶች ናቸው፤ ለማሳያም 43 ግድቦች ተለይተው ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ ስለመገባቱ ባሙያው አንስተዋል::

ከተፈጥሮ ውኃ አካላት የራቁ አርሶ አደሮችም በኩሬ እንዲያለሙ የማድረግ በመጨረሻም ምርቱ በጥራት ወደ ገበያ እንዲቀርብ የአሳ ድህረ ምርት አያያዝ እና አጠቃቀም ላይ ሥራዎችን መሥራት ሱቆች፣ መጋዘኖች፣ የፕሮሰስ ሼዶችን የመሥጠት ተግባር እንደተቋም እየተሠራ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት::

 

መረጃ

በሀገራችን የዓሣ ጫጩት ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም የአቅርቦት እጥረት መኖሩ ይነገራል፤ ችግሩን ለመፍታት ታዲያ በ10 ዓመቱ የግብርና መሪ ዕቅድ ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ የዓሳ ዘርን በአስተማማኝ መጠን ለማቅረብ በየዓመቱ 658 ሚሊዮን የዓሳ ጫጩት የሚያመርቱ የዓሳ ጫጩት ማስፈልፈያና ማሰራጫ ማዕከላት ይቋቋማሉ ተብሏል፡፡

ማዕከላቱ እንደ አስፋላጊነቱ ሦስት የዓሳ ዝርያዎችን (ቀረሶ፣ አምባዛ እና ቤዞ) ያመርታሉ፡፡ የግሉ ዘርፉ የዓሳ ጫጩት ማምረት ላይ እንዲሳተፍ አስፈላጊው ድጋፍ እና እገዛም ይደረጋል፡፡

መረጃው  – የግብርና ሚኒስቴር 10 የዓመት ዕቅድ ነው

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here