በሩብ ዓመቱ ከ21 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠበሰበ

0
104

በአንደኛው ሩብ ዓመት ከ21 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሰቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል። በቢሮው የግብር ትምህርት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ እንደተናገሩት እስከ ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ከ21 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠብስቧል።

ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው መግለጻቸውን ከቢሮው የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለዚህም ውጤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሠራቱ እና በዘመናዊ (በኤሌክትሮኒክስ) የታክስ አስተዳደር ሥርዓት የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ባሉበት ሆነው እንዲከፍሉ መደረጉ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

ቢሮው ብልሹ አሠራሮችን ለማስተካከልና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን ያነሱት አቶ ታዘባቸው የሥነ – ምግባር ጉድለት በታየባቸው 58 ባለሙያዎች ላይ የተለያየ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል።

የደረሰኝ መሰወር፣ የግብር ማጭበርበር፣ የንግድ እንቅስቃሴ አለመረጋጋት እና የመሳሰሉ ተግዳሮቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሰብ ዐቅዶ እየሠራ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here