ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መልካም ጅምር

0
34

የትኛውንም ዓይነት ቋንቋ መማር እና ማስተማር ጥቅም እንጂ አንዳችም ጉዳት የለውም:: ቋንቋ ለየትኛውም ሰው ሆነ ማኅበረሰብ የመገናኛ መሣሪያው ነው፤ ይህንን መሣሪያ ለግንኙነት መጠቀም ብልህነትም አዋቂነትም ነው፡፡

በተለምዶ ሲባል የምንሰማውቋንቋ ወንዝ ያሻግራልብሂል ዝም ብሎ አባባል ብቻ አይደለም፡፡ ቋንቋ ሀሳብን ለመረዳት እና ለማስረዳት፣ ርስ በርስ ለመረዳዳት እንዲሁም ችግርን ለመፍታት ትልቅ ሚና አለው፡፡

ማንኛውንም ቋንቋ መማሩ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ስንል በአብነት ከሚጠቀሱ ቋንቋዎቻችን አንዱ  ግዕዝ ነው:: ግዕዝ  ለዘመናዊው ዕውቀት መነሻ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ በውስጡም ሰፊ የዕውቀት፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ የታሪክ እና የሳይንሳዊ እንዲሁም የመድሃኒት  ዕውቀቶችን አካቶ የያዘ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ ቅርስ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ሕፃናት ከተወለዱበት ዕለት ጀምሮ ቋንቋን የማወቅ ችሎታ አላቸው:: ችሎታ ብቻ ሳይሆን መብትም አላቸው:: ሕፃናት ቋንቋን የማወቅ መብት የሚኖራቸው ሲያድጉ በዚያ ቋንቋ ስለሚጠቀሙበት ነው:: ሕፃናት በሕፃንነት ማወቅ የሚጀምሩትን ቋንቋ ካደጉ በኋላ ከቋንቋው ተናጋሪዎች በመስማት እና ለመናገር በመሞከር ይበልጥ ያበለፅጉታል:: ሕፃናት ቋንቋን ይበልጥ መልመድ የሚችሉት በተወለዱ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ነው:: ለዚህም በተለይም በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካቶ መሰጠቱ ቋንቋውን ይበልጥ እንዲያውቁት እና እንዲጎለብት ያደርገዋል፡፡

ለግዕዝ የተሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያ ጥንታዊነት እንዲሁም ታሪካዊ ሀገርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረውን ቅቡልነት በእጅጉ የሚያሳድግ ነው፡፡ በግዕዝ ቋንቋ ተቀርጾ የሚገኝ ዕውቀት ሰፊ እና ጥልቅ በመሆኑ በዓለም ላይ የሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ግዕዝን ዋና የትኩረት አቅጣጫቸው አድርገዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድ የመንፈሳዊ እና የታሪካዊ ቅርስ ምስጢር የሚገለጥበትን ግዕዝ ከዘመናዊ ትምህርት

ጋር አቀናጅቶ እንዲማር መደረጉ በጥልቀት ለመማር እና ለመመራመር በር የሚከፍት ነው፡፡ ለግዕዝ የተሰጠው ትኩረት የበለጠ እንዲሰፋ ለማድረግም የሁሉም ርብርብ ወሳኝ ነው፡፡

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ለግዕዝ የሰጠችው ትኩረት መልካም ነው፡፡ ግዕዝ በጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች ከመሰጠት አልፎ በአማራ ክልል በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ መሰጠት መጀመሩ የቋንቋዉን ጠቀሜታ ከመረዳት የመነጨ መሆኑን ያሳያል፡፡

ግዕዝ ከሃይማኖት ቋንቋነት በላይ መሆኑን መገንዘብም ለግዕዝ ትንሳኤ መሠረት ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ጥበብ፣ ፍልስፍና፣ ምስጢር የሰፈረው እና ተደብቆ የሚገኘው በግዕዝ ቋንቋ በተጻፉ ሰነዶች ላይ በመሆኑ ቋንቋውን ከብሔር እና ከሃይማኖት ባሻገር አስቦ መማር የሀገርን የማደግ ምስጢር ማወቅ እንዲሁም ዕድገት እንደማፋጠን ነው፡፡ እናም ቋንቋውን በትምህርትነት መስጠቱ በስፋት ሊተገበር የሚገባው መልካም ርምጃ ነው፡፡

 

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here