ስጋት ላይ የወደቀዉ የክልሉ የእግር ኳስ ስፖርት

0
52

በሀገሪቱ ትልቁ የሊግ እርከን ከአማራ ክልል ፋሲል እና ባሕር ዳር ከነማ እየተሳተፉ ይገኛሉ:: ደብረብርሃን ከተማ እና ደሴ ከተማ ደግሞ በሀገሪቱ ሁለተኛው የሊግ እርከን እየተፎካከሩ ይገኛሉ:: በአንደኛ ሊግ ግን አንድም የአማራ ክልል ክለብ እየተሳተፈ አይደለም:: የተቋረጠው የአማራ ሊግ ውድድርም ቢሆን እስካሁን አልተጀመረም:: አንድ ወቅት በሁሉም የሊግ እርከኖች ላይ በጠንካራ ተፎካካሪነታቸው ይታወቁ የነበሩት የክልሉ ክለቦች ዛሬ ቁጥራቸው ከማነሱም በላይ የፉክክር አቅማቸው በእጅጉ ተዳክሟል።

የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው 2017 ዓ.ም የክልሉን ክለቦች በየደረጃቸው መድቦ ውድድሮችን ለማስጀመር አቅዶ የነበረ ቢሆንም በሀገራዊ ጉዳዮች እና በክልሉ ሰላም መደፍረስ ምክንያት ውድድሮቹን ሳያካሂድ ቀርቷል። በርካታ ክለቦች በተለይም በአንደኛ ሊግ የሚሳተፉ አብዛኞቹ ክለቦች ከበጀት እጥረት ጋር በተያያዘ ለውድድር ዝግጁ እንዳልነበሩም የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ኀላፊ አቶ ብርሃኔ ጌትነት ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል::

የአንደኛ ሊግ ክለቦች የሚገኙባቸው ወረዳዎች በፀጥታ ችግር የተጎዱ እና የገንዘብ እጥረት ያለባቸው በመሆኑ ውድድር ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ላይ አይደሉም:: የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአንደኛ ሊግ ክለቦች ውድድሩን እንዳያቋረጡ እና የነበራቸውን ሀገር አቀፍ ውክልናን እንዳያጡ ውድድሮቹ እንዲራዘሙላቸው ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱ አይዘነጋም:: የክልሉ እግር ኳስ አጠቃላይ ተሳትፎ በሦስቱም የሊግ እርከኖች ላይ በእጅጉ ቀንሷል። በፕሪሚየር ሊጉ ከባሕር ዳር ከነማ እና ፋሲል ከነማ በስተቀር ሌላ ክለብ ማፍራት አልተቻለም:: ሁለቱ ክለቦችም ቢሆኑ ከዚህ ቀደም ያሳዩት የነበረውን የዋንጫ ተፎካካሪነት እና አህጉራዊ ውድድር ተሳትፎ መድገም ተስኗቸዋል::

ታዲያ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? አንድ ወቅት ጥሩ ይንቀሳቀስ የነበረው የክልሉ እግር ኳስ ዛሬ ለምን ስጋት ላይ ወደቀ የችግሮቹ ስር መሰረት የት ላይ ነው? ክለቦቹ የሚተዳደሩት ከከተማው አስተዳደር በሚመደብላቸው በጀት ብቻ በመሆኑ በዚህ አሰራር ለከፋ ችግር እንደተዳረጉ አቶ ብርሃኔ ጌትነት ተናግረዋል። ክለቦቹ ከመንግሥት በጀት ውጪ ሌሎች የገቢ ምንጮችን ለመፍጠር አልሰሩም ነው- ያሉት ጽ/ኀላፊው::

በከፍተኛ ሊጉ እና በአንደኛ ሊግ የክልሉ ክለቦች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ቀንሷል:: በፊት በየምድቡ ከሁለት እና ሦስት ክለቦች በማያንስ ቁጥር ይወከል የነበረው አማራ ክልል ዛሬ አንድ ክለብ እንኳን ማግኘት ከባድ እየሆነ መጥቷል:: በርካታ ክለቦች ወይ ፈርሰዋል አልያም ከውድድሩ ራሳቸውን አግልለዋል:: ለክለቦች የደም ስር እና ለተተኪ ተጫዋቾች መፈልፈያ ምንጭ የነበረው የአማራ ሊግም (የክልሉ ሊግ) ውድድር ከ2015 ዓ.ም ወዲህ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።

የፀጥታ ስጋት ባለበት ሁኔታ ተጫዋቾችን፣ አሰልጣኞችን እና ደጋፊዎችን ይዞ መንቀሳቀስ የማይታሰብ ነው:: በርካታ ተጫዋቾች በተለይ በታችኛው ሊግ እርከን ላይ የነበሩ በፀጥታው ስጋት እና ውድድር ባለመኖሩ ምክንያት ክለቦቻቸውን ጥለው ወደ ሌሎች ክልሎች ለመሄድ ተገደዋል:: እናም የክልሉ ሊግ (አማራ ሊግ) መቋረጥ እግር ኳሱ  የሚቆፈርለትን መቃብር እያፋጠነው ይገኛል:: የበርካታ ክለቦች አመራሮች በፖለቲካዊ ውሳኔ የሚሾሙ እንጂ ለእግር ኳስ ሙያዊ እውቀት እና ልምድ ያላቸው አይደሉም:: እነዚህ አመራሮች ታዲያ የክለቦችን የረጅም ጊዜ ህልውና ከማረጋገጥ ይልቅ በየዓመቱ የአጭር ጊዜ ውጤት ላይ ብቻ ያተኩራሉ::

ይህም የክለቦችን ውድቀት የሚያፋጥነው ሌላኛው ምክንያት ነው:: የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን በአግባቡ ከማስኬድ እና አዲስ መዋቅር ከመዘርጋት አንፃር ያላቸው ሚናም እጅግ ደካማ ነው። የእግር ኳስ ክለቦች መዳከም እና መጥፋት ጉዳቱ በሜዳ ውጤት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም:: የሚያስከትለው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከዚህም የከፋ ነው:: እግር ኳስ ወጣቶች ከአልባሌ ስፍራ እና ከሱስ የሚርቁበት፣ ጉልበታቸውን እና ጊዜያቸውን በበጎ ነገር ላይ የሚያውሉበት ትልቅ መሳሪያ ነው::

የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2018 ዓ.ም ውድድሮችን ለማስጀመር የተለያዩ አማራጮችን እያጤነ መሆኑን የጽ/ኀላፊው አቶ ብርሃኔ ጌትነት ተናግረዋል:: ውድድሩን በማዕከል ከማድረግ ይልቅ በየቀጠናው (ለምሳሌ ምስራቅ አማራ፣ ወሎ፣ ጎጃም እና ጎንደር) በማካሄድ የፀጥታ ስጋትን ለመቀነስ እና የክለቦችን የጉዞ ወጪ ለመቆጠብ ታስቧል ብለዋል። ፌዴሬሽኑ ክለቦች ከየአካባቢው መስተዳድር በጀት እንዲያገኙ እና ውድድር እንዲጀምሩ ለማስቻል ጥረት እያደረገ ነው። በአሁኑ ወቅት የትኞቹ ክለቦች በጀት እንዳላቸው እና እንደሌላቸው ለማወቅ የማጣራት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ አቶ ብርሃኔ ነግረውናል::

ፌዴሬሽኑ ለክለቦች የስልጠና እና ሌሎች የቴክኒክ ድጋፎችን በማድረግ ከጎናቸው እንደሚቆም ገልጿል። በተለይም ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድጉ ለሚጠበቁት እንደ ደሴ ከተማ ላሉ ክለቦች ልዩ ክትትል እና ድጋፍ እናደርጋለን  ብለዋል- ኀላፊው። ለፈረሱ እና ለተዳከሙ ክለቦችም የማንሰራሪያ በጀት በመመደብ ወደ ውድድር እንዲመለሱ ማድረግ ሌላኛው መፍትሄ ነው:: የክለብ አወቃቀርን መቀየር ክለቦች ከመንግሥት ጥገኝነት ወጥተው ሕዝባዊ ማድረግ እንደሚገባም አቶ ብርሃኔ ጌትነት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር  8  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here