የሜዳዉ አናብስት የበጎ ሥራ አርአያዎች

0
65

በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚገኙ አፍሪካውያን ኮከቦች በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ የገቡት በእግር ኳስ ብቃታቸው ብቻ አይደለም:: ይልቁንም  ስማቸው ከፍ ብሎ የሚጠራው ከሜዳ ውጪ በሚያከናውኑት በጎ ሥራ ጭምር እንጂ:: እነዚህ አፍሪካዊ የእግር ኳስ ተጫዋቾች  በተለያዩ የበጎ አድራጎት  ሥራዎች በመሳተፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ቀይረዋል፤ እየቀየሩም ይገኛሉ::

ታዲያ  መልካም ልብ ያላቸው እነዚህ ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ ክህሎታቸው  በዓለም መድረክ  ከፍ እንዳደረጋቸው ሁሉ ከሜዳ ውጪ የሚሰሩት በጎ ሥራም በህዝባቸው ልብ ውስጥ የዘላለም ዙፋን አሰጥቷቸዋል፤ ዝናን፣ መልካም ስምን እና ሀብትን ለማኅበረሰብ ለውጥ በምን መንገድ መጠቀም  እንደሚቻል በተግባር እያሳዩ መሆናቸውን የጎል ዶት ኮም መረጃ ያስነብበናል:: የኮትዲቫራዊውን ዲዲየር ድሮግባ ስብዕና ለመረዳት በሀገሩ የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት በእግር ኳስ ያከሸፈበትን ታሪክ ማንበብ በቂ ነው:: ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ድሮግባ ከጨዋታው በኋላ ከብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ጋር በመሆን በካሜራ ፊት ተንበርክኮ ያስተላለፈው የሰላም ጥሪ ተዋጊዎቹ ለአንድ ሳምንት ያህል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ምክንያት እንደነበር አይዘነጋም::

የድሮግባ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ተቋማዊ ቅርፅ የያዙት እ.ኤ.አ. በ2007 ባቋቋመው “የዲዲየር ድሮግባ ፋውንዴሽን” አማካኝነት መሆኑን የአፍሪካ ዶት ኮም መረጃ ያመለክታል:: ድሮግባ ከፔፕሲ ኩባንያ ባገኘው ሦስት ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ በአቢጃን ከተማ ዘመናዊ ሆስፒታል አስገንብቷል:: ይህ ሆስፒታል በእናቱ ስም የተሰየመ ሲሆን በተለይ በእናቶች እና ህፃናት ጤና ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል:: በተጨማሪም ተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎቶችን በማዘጋጀት በገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች አገልግሎት ይሰጣል::

“ትምህርት የድህነትን ሰንሰለት ለመስበር ቁልፍ ነው” በሚል እምነት በርካታ ትምህርት ቤቶችንም  አስገንብቷል። ለአብነትም በኮትዲቫር  ገጠራማ  አካባቢዎች የዲጂታል የመማሪያ ክፍሎችን በማዘጋጀት ህፃናት ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ  እያደረገ ይገኛል:: የድሮግባ ህይወት አንድ ግለሰብ በቁርጠኝነት እና በሀገር ፍቅር ከተነሳ ከፖለቲከኞች በላይ ለሀገሩ ሰላም እና እድገት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችል ያስተምራል ሲል አፍሪካ ዶት ኮም አስነብቧል::

በአንፊልድ በደጋፊዎች ዘንድ “የግብጽ ንጉሥ” ተብሎ የሚዘመርለት  ሙሀመድ ሳላህ የልብ ምቱ የሚጨምረው የትውልድ መንደሩን ስም ”ናግሪግን” ሲሰማ ነው::  የመንደሩ ነዋሪዎች ንጉሣችን ሳይሆን “የደስታችን  ምክንያት” ሲሉ  ይጠሩታል:: ለትውልድ መንደሩ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና የፍሳሽ ማስወገጃ አገልግሎት ለማዳረስ 450 ሺህ ዶላር የሚያወጣ መሬት ገዝቶ ለፕሮጀክቱ አስረክቧል:: በተጨማሪም የሴቶች ትምህርት ቤት የወጣቶች ማዕከል እና የአምቡላንስ ማዕከል እንዲገነባ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል:: ሆስፒታል እንዲገነባ እና የህክምና አገልግሎት እንዲሻሻል ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል:: በካይሮ ለሚገኘው የብሔራዊ ካንሰር ተቋም  ሦስት ሚሊዮን ዶላር በመለገስ በሽብር ጥቃት የወደመውን ህንጻ መልሶ እንዲገነባ አድርጓል::

በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ለትውልድ መንደሩ በብዙ ሺህ ቶን የሚቆጠር ምግብ፣ የኦክስጅን ሲሊንደሮች እና አምቡላንሶችን በመለገስ የበርካቶችን ህይወት ታድጓል:: በእሳት አደጋ ለወደመው የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን መልሶ ግንባታ ሦስት ሚሊዮን የግብጽ ፓውንድ መለገሱ የእርሱን መልካምነት ያሳያል:: የሳላህ ታሪክ “መነሻህን አትርሳ” የሚለውን የሀገራችንን ብሄል በተግባር ያሳያል:: ስኬት፣ የመጣህበትን ማህበረሰብ ለማንሳት እንጂ ለመርሳት ምክንያት ሊሆን እንደማይገባም የእርሱ መልካም ተግባር ያስተምራል::

የአራት ጊዜ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች የሆነው ሳሙኤል ኤቶ “አፍሪካ ለሰጠችኝ ነገር ምላሽ መስጠት እፈልጋለሁ” ሲል ይናገራል:: ከሜዳ ውጪ በተለይም ለወጣቶች መብት እና እድገት የሚፋለም ታላቅ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋች ነው:: እ.ኤ.አ. በ2006 ያቋቋመው “ሳሙኤል ኤቶ ፋውንዴሽን” ዋነኛ አላማው በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ ህፃናትን እና ወጣቶችን መደገፍ ነው:: በካሜሩን፣ በጋቦን እና በኬንያ የእግር ኳስ አካዳሚዎችን በመክፈት ተሰጥኦ ያላቸውን በርካታ ወጣት ተጫዋቾች ህልማቸውን እንዲያሳኩ እድል ፈጥሮላቸዋል:: በዱዋላ ከተማ በሚገኘው ላኩንቲኒ ሆስፒታል ውስጥ አንድ ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ወጪ በማድረግ 48 አልጋዎች ያሉት የህፃናት የህክምና ክፍል  (ሳሙኤል ኤቶ ፓቪሊዮን) አስገንብቷል:: በተጨማሪም ለካሜሩን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዘመናዊ የቀዶ ጥገና መሳሪያዎች የተገጠመላቸው አምቡላንሶችንም አበርክቷል::

ሳሙኤል ኤቶ ስኬትን እና ተሰጥኦን በመጠቀም የቀጣዩን ትውልድ መንገድ ማቅናት ምን ያህል ታላቅ ሥራ እንደሆነ ያስተምራል:: እርሱ  ዐሳ ከማበርከት ይልቅ ዐሳ ማጥመድን የሚያስተምር መሪ ነው:: ሳዲዮ ማኔ በሊቨርፑል በባየር ሙኒክ እና አሁን በአል-ናስር ክለቦች ያስመዘገባቸው ስኬቶች የአፍሪካ ኩራት እንዲሆን አድርገውታል:: ነገር ግን የማኔ እውነተኛ ታላቅነት የሚለካው በሜዳ ላይ በሠራቸው ገድሎች ብቻ ሳይሆን በትውልድ መንደሩ “ባምባሊ” ሴኔጋል ውስጥ በሚሠራው በጎ ተግባር ጭምር ነው:: የሳዲዮ ማኔን የበጎ አድራጎት ሥራ ለመረዳት የእርሱን የህይወት ፍልስፍና መገንዘብ ወሳኝ ነው። በአንድ ወቅት “ለምን ዐስር ፌራሪ፣ ሃያ የአልማዝ ሰዓቶች ወይም ሁለት የግል አውሮፕላኖች ያስፈልጉኛል? እነዚህ ቁሶች ለእኔ እና ለዓለም ምን ይጠቅማሉ?” ሲል መናገሩ አይዘነጋም::

ማኔ በልጅነቱ የድህነትን ፅዋ ተጎንጭቶ ያደገ ሰው ነው:: ለማኔ ምግብ እና ትምህርት የቅንጦት በነበሩበት በዚያ የጨለማው ዘመን የህክምና ተቋም ባለመኖሩ አባቱን በሞት አጥቶታል:: ታዲያ ይህ የልጅነት ጠባሳው ዛሬ ያገኘውን ሀብት እና ዝና ትርጉም ባለው ሥራ እንዲያውል አድርጎታል:: የአባቱ ህይወት ያለፈው በህክምና እጦት መሆኑን የማይዘነጋው ማኔ 530 ሺህ ዩሮ በማውጣት በትውልድ መንደሩ ዘመናዊ ሆስፒታል አስገንብቷል:: ይህ ሆስፒታል ባምባሊን ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያሉ 34 መንደሮችን በማገልገል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ከሞት አደጋ እየታደገ ይገኛል::

በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ለሴኔጋል ብሄራዊ የጤና ኮሚቴ 41 ሺህ ፓውንድ በመለገስ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። 270 ሺህ ዩሮ በሆነ ወጪ አዲስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገንብቶም አስረክቧል:: ይህም ወጣቶች ለትምህርት ሲሉ ወደ ሌሎች ከተሞች ሲጓዙ የሚደርስባቸውን  እንግልት አስቀርቷል:: ለተማሪዎች ላፕቶፖችን ከማቅረቡም በላይ በየዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች 400 ዩሮ በመሸለም የትምህርት ፍላጎታቸውን ያነሳሳል:: በመንደሩ ውስጥ ላለ እያንዳንዱ ቤተሰብ በየወሩ 70 ዩሮ በመስጠት የኑሮ ጫናቸውንም ያቀላል:: በመንደሩ ውስጥ የነዳጅ ማደያ እና የፖስታ ቤት አገልግሎት አስጀምሯል:: በተጨማሪም ከኦሬንጅ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የትውልድ መንደሩን የ4ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኝ አድርጓል:: ይህም ትንሿ የትውልድ መንደሩ  ከዓለም ጋር  እንድትገናኝ አድርጓል::

ኑዋንኩ ካኑ፣ ቪክቶር ኦስሜንህ፣ ሚኬል ኢሴን እና ካሊዱ ኩሊባሊን የመሳሰሉ አፍሪካውያን ተጫዋቾች የእግር ኳስን ትርጉም ከጨዋታነት በላይ ከፍ አድርገው ሰቅለውታል። ስኬትን፣ ዝናን እና ሀብትን፣ የማኀበረሰብን ህይወት ለመለወጥ ዋነኛ መሳሪያ  አድርገውታል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር  8  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here