ልጆችዬ! እንዴት ናችሁ? መቼም በርትታችሁ እንደምትማሩ እርግጠኛ ነን:: ልጆችዬ! ከመደበኛ ትምህታችሁ በተጨማሪ ምን ዝንባሌ አላችሁ? መቼም ከትምህርታችሁ ጎን ለጎን የተለያዩ ዝንባሌዎችና ተሰጥኦዎች እንደሚኖራችሁ አንጠራጠርም::
በባሕር ዳር ከተማ ሠርጸ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነውን አዲስ ተስፋ ከትምህርቱ ባሻገር ያለውን ዝንባሌ ልናስነብባችሁ ወደናል:: በትምህርቱ መካከለኛ ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ ይመደባል:: ይህ ውጤት አመርቂ አለመሆኑን አምኖ ለማሻሻል እየጣረ እንደሆነ ነግሮናል:: በቀጣይ ከመካከለኛ ወደ ጐበዝ ተማሪዎች ተርታ ለመሰለፍ ቆርጦ ተነስቷል:: የተለያዩ አጋዥ መጽሐፍትን በማሰባሰብ የተሻለ ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ዝግጅቱን አጠናክሮ ጥናቱን መጀመሩን ገልጾልናል::
ተማሪ አዲስ በትምህርት ቤት ባሉ ክበቦችም ይሳተፋል:: በተለይ በስፖርት ክበብ ውስጥ በንቃት ይሳተፋል:: ተማሪ አዲስ ሲያድግ ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆን ይፈልጋል፤ ሀገሩን ኢትዮጵያንም በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሆና ዋንጫ እንድታገኝ ህልም አለው:: ይህንንም ለማሳካት ከትምህርቱ ጎን ለጎን በእግር ኳስ ፕሮጀክት ታቅፎ ልምምድ እየሠራ ይገኛል:: ከዚህ ባሻገር ቤተሰቦቹን በተለያዩ ሥራዎች ያግዛል:: ልጆች አዲስ ተስፋ ጎበዝ ነው አይደል? እናንተስ ምን ተሰጥኦ አላችሁ? እናንተም እንደ አዲስ በተለያዩ ክበባት እና የስፖርት ልምምዶች መሳተፍ አትርሱ፤ ቤተሰባችሁንም በሥራ አግዙ፤ ሰላም ሁኑ ልጆች!::
ተረት
ሦስቱ ወንድማማቾች
በድሮ ጊዜ ሦስት ወንድማማቾች በአንድ ላይ አብረዉ ይኖሩ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ለሞፈር የሚሆን እንጨት ለመቁረጥ በአቅራቢያቸው ወዳለው ጫካ ተያይዘው ሄዱ። ጫካው ለሞፈር የሚሆን እንጨት ያላቸው ብዙ ዛፎች አሉት። ነገር ግን ሦስቱም ለመቁረጥ የማያደክም አጠር ያለ ዛፍ ማማረጥ ጀመሩ::
ሲያማርጡ፣ ሲያማርጡ፣ በመጨረሻ ከገደል አፋፍ/ጫፍ ላይ የቆመ አንድ አጠር ያለ ዛፍ መረጡ። ነገር ግን ከሦስቱም ወንድማማቾች አንዳቸውም መጥረቢያ አልያዙም ነበር። ሦስቱም “አንተ አምጣ፤ አንተ ሂድና አምጣ” ሲባባሉ ቆይተው መስማማት አቃታቸው። በመጨረሻም ከሦስቱም አንዳቸው እቤት ሄደው መጥረቢያ ለማምጣት ሰንፈዉ ዛፉን ወዝዉዘዉ እንዲወድቅ ለማድረግ ተስማሙ።
ዛፉ ገደል አፋፍ ላይ ስለቆመ ከገደሉ በተቃራኒ እንዲወድቅ ለማድረግ አቀዱ። ከዛም ሦስቱም ዛፉን በኃይል ከገደሉ በተቃራኒ አቅጣጫ እንዲወድቅ መነቅነቅ ጀመሩ:: ትንሽም እንደቆዩ ዛፉ ከነሥሩ መሬቱን ገንድሶ ወደ ገደሉ ዉስጥ ሲሰምጥ ሦስቱ ወንድማማቾችም አብረዉ ወደ ገደሉ ወድቀው ክፉኛ ተጎዱ:: ከሦስቱ አንዳቸው እቤት ሂደው መጥረቢያ ለማምጣት በመስነፋቸው ክፉ አደጋ ደረሰባቸው። የስንፍና መዘዙ ብዙ ነው፤ ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ!
ምንጭ- የኢትዮጵያ ተረቶች
ይሞክሩ
ላዩ ሰርዶ ሆኖ ውስጡ ብርንዶ የሚባለው ምንድን ነው?
ልብስም ጉርስም መሆን የሚችል ምንድን ነው?
አልወለድም፤ ማንም ሳይሰለቸው እሽሩሩ ይለኛል፤ እኔ ማነኝ?
መልስ
ቀይ ሽንኩርት
በግ
እንስራ
ነገር በምሳሌ
- መኮርኮሚያ ያላገኘ፤ መዘርጊያን ተመኘ
ጥቂት ሳያገኝ ብዙ ነገር ተመኘ
- ልጅ እንዳባቱ፣ እንደቤቱ፡፡
ሰው ሰው የሚመስለው
አስተዳደጉን እና አኗኗሩን
ነው፡፡
- መላ እንደ ሴት፤ ግርማ
እንደ ሌሊት፡ ፡
ሴቶች መላ መፍጠር
ይችሉበታል፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


