ዕድሜያቸው በሰባዎቹ አጋማሽ ላይ ይገኛል። አባቴ በሕይወት እያለ ጓደኛው ነበሩ። በድንገት ከእኔ ጋር መንገድ ተገናኘንና ወደ አንድ የጀበና ቡና መሸጫ ጎራ አልን። ብዙ ተስተገናጋጅ ነበረና ቡናችን ዘገየ፤ በዚያ መሀል ሹክሹክታ በሚመስልና ቀሰስ ባለሁኔታ “ስማኝ ልጄ ማግባት ቤተሰብ መመስረት አለብህ፣ ውጭ አታምሽ፣ አባካኝ አትሁን፣ ጥሪት ያዝ…” እያሉ ለእኔ ይበጃል ባሉት መንገድ ብዙ መከሩኝ።
ድንገት አስተናጋጇ ከፊታችን በተሰደረው ስኒ ውስጥ በእጇ ከያዘቸው የብረት ቀለም ካለው ፔርሙስ መሳይ ዘመናዊ ጀበና እያንቆረቆረች ሲኒውን አረፋ ባለው ቡና ስትሞላው ሁለታችንም እንደመባነን ብለን ከሀሳባችን ተናጠብን። የአስተናጋጇን መሄድ ተከትለን ሁለታችንም “የቡና ስብቱ መፋጀቱ“ እንደሚባለው በፍጥነት ቡናችንን ፉት ማለት ጀመርን።
የቡና ተጠቃሚው ብዙ ነው፤ በዙሪያችን የተኮለኮለው ሰው እየተበራከተ መጥቷል። ተግሳፅ መሳይ ምክርን ያዘንብ የነበረው የአቶ ወርቁ እጅጉ አንደበትም ለአፍታ ፀጥ ብሏል፤ ምክንያቱ የእኔን በንቃት መከታተል ለማረጋገጥ ይሁን በሌላ በውል አልተረዳሁትም።
በዚህ ጊዜ ሳላውቀው ከኪሴ የነበረውን ሳምሰንግ ተንቀሳቃሽ ስልክ አውጥቼ የኢንተርኔት ዳታዬን አብርቼ ከስልኬ ጋር ተጣባሁ። እውነት ለመናገር ከስልኬ ጋር የተፀናወተኝ ውል አልባ ወዳጅነት በዋዛ አልለቀቀኝም። ዐይኖቼን፣ ጆሮዎቼን፣ እጆቼን፣ ሀሳቤን ምንአለፋችሁ ነፍሴም አልቀረ ሁለንተናዬን ተቆጣጥሮታል።፧
በእኔ እና በአዛውንቱ መሀል ፀጥታ ሰፍኗል። በእኔና በስልኬ መካከል ደግሞ መደባበሱ መተሻሻቱ ደርቷል። አንዴ ፈገግ ሌላ ጊዜ ኮስተር ደሞ ፍጥጥ እንደገና ምስጥ… እንደ ደራሽ ውሃ በየደቂቃው የሚለዋወጥ ስሜት ፊቴ ላይ በጉልህ ይነበባል።በዚህ ሁኔታ ከሃያ አምስት እስከ ሰላሳ ደቂቃዎች አለፉ።
በእጆቼ መዳፍ መሀል ያለውን ስልኬን እየደባበስሁ አንዴ ፌስቡኩን ቆየት ብዬ ወደ ዩቲዩብ እንደገና ወደ ቲክቶኩ ስማስን ቆይቼ ብዙ ገለባ እና ጥቂት እፍኝ ፍሬን ቃርሜ ድንገት ቀና ስል ሽማግሌው አቶ ወርቁ አንገታቸውን ዘንበል አድርገው በሀዘኔታም በትዝብትም መልክ ዐይናቸውን እኔ ላይ ተክለው በአፅኖት ይመለከቱኛል። በአንክሮ ሲከታተሉኝ እንደቆዩ ሲገባኝ ደንገጥ አልሁ።
አባ ወርቁ ግን “አይዞህ! ከሰው ጋር ስትሆን ስልክ አትነካካ፤ ለሰው ክብር የለሽ ያደርግሀል”በማለት ምክራቸውን በሌላ አጀንዳ ቀጠሉ።” ልጄ የዚህ ስልክ ጉዳይ ምንድን ነው ነገሩ? ድሮ ሰው በመኪና ሲጓዝ እና እንዲህ ቡና ሲጠጣ ጨዋታው ብዙ ነበር:: ዛሬ ምኑ ነው እንዲህ ሰው ሰውን አስጠልቶት ከስልኩ ጋር ያወዳጃችሁ?” ሲሉ ጠየቁኝ፤ እኔም መልስ አጣሁና አንገቴን ደፍቻ ዝም አልሁ።
አቶ ወርቁ ቀጠሉ፤ “ሰው በየቦታው ከስልኩ ጋር የተፀናወተው በሽታ ከፍቷል፤ ኪሱን እንኳን መጠበቅ እየተሳነው ነው። ይሄ ቲክቶክ ዩቲዩብ እንደኛ ላለ ታዳጊ ሀገር አይሆንም:: ብርቱ ጉልበት ያለውን የወጣቱን ሥነልቦና እየሰለበብን ነው“ በማለትም በሀዘኔታ ተናገሩኝ። ቀጠሉ፤ ወጣቱ በስልኩ የሚረባውንም የማይረባውንም እየሰበሰበ የሱስ ተገዥ ሆኗል። ወጣቱ ጫት አይቃም፤ መጠጥ አይጠጣ፤ ሲጋራ አያጭስ እያልን በምንታገልበት ወቅት ይሄ ቲክቶክ ዩቲዩብና ፌስቡክ መጥቶ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ“ ሆኖብናል። ማህበራዊ ሕይዎታችንንም ቀምቶናል በማለትም በቁጭት ተናገሩ::
“ እኛ ብዙ መሥራት ያለብን ኢትዮጵያዉያን ነን:: ግን ታዳጊውና ወጣቱ ስልኩ ጋር ተቀምጦ መዋሉና ማምሸቱ የሚያስጨንቀን ሳያንስ ለስድብና ለግጭት የሚጋብዙ ቃላትን እየተመላለሰ ሲሰዳደብ ስንመለከት ልባችን እያዘነ ነው። ይሄ ቲክቶክ፣ ፌስቡክና መሰል ነገሮች ወጣቱን ተቆጣጥረውታል፤ ከጫት እና ከሲጋራው በላይ ክፉ ደባል ሱስም ሆኖታል። ስለዚህ የሚመለከተው አካል ሁሉ ‘ሳይቃጠል በቅጠል‘ ካላለው ችግሩ ይከፋል” በማለት በሀዘኔታ ተናገሩ።
አቶ ወርቁ ንግግራቸውን ቀጠሉ፤ ወጣቶች ስልክ ላይ ሲተከትኩ መዋል መሰልጠን አይደለም፤ ጊዜ ሀብት ነው፤ ጊዜውን በሥራ እና በንባብ ካላሳለፈው ነገ የራሱንም፣ የሀገሪቱንም ተስፋ እያጨለመው ነው። ቀንም ስልኩ ጋር፤ ማታ ተኝቶም ስልኩን የሙጥኝ የሚለው እየበዛ ነውና ችግሩ ስር ሳይሰድ መፍትሔ እዲያገኝ ተመኙ::
የአቶ ወርቁ ትዝብት አላበቃም፤ ‘ከቤቴ ሰፌድ የሚያክል ስልክ ጨብጦ የሚነካካ እንጂ እንደ ሰው ቁጭ ብሎ የሚያወራኝ ሰው አጣሁ “ ይላሉ “ቤቴ ማታ ቡና አስፈልቼ ከልጆቼና ከባለቤቴ ጋር ማውራት፣ መወያየት ቢያምረኝም ከወዴት ተገኝቶ! ሁሉም ጥጉን ይዞ ስልኩን ይጠቀጥቃል፤ የቤተሰቦቼን ሳቅ ጨዋታ ነጥቆኛል፤ ማህበራዊ ግንኙነታችንንም አሳጥቶናል” በማለትም በምሬት ነገሩኝ።
“ሌላው“ ብለው አቶ ወርቁ ቀጠሉ፤ “ ድንኳን ቤት ሀዘንተኛን ልናስተዛዝን ሄደን ከማስተዛዘን ይልቅ ከኪሱ ስልኩን አውጥቶ ፌስቡክ ላይ የሚወዳጀው ወጣት ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ስመለከት ልቤ ማዘንም መፍራትም ጀምሯል” ይላሉ። ይሄንን የስልክ አጠቃቀም ችግር በጊዜ መፍትሔ ካልተገኘ የሚያስከትለው ችግር እየከፋ ነው። በየቢሮው ሥራ እየተስተጓጓለ ነው :: በየተቋሙ ጉዳይ ይዘን ሄደን ማን ይፈፅምልን ? አብዛኛው በጁ ባለው ስልክ ቪዲዮ ነገር እያየና ሌላ ነገር እየተመለከተ ስናናግረው እንኳን ምላሽ የሚሰጠን አገልጋይ ሠራተኛ እየጠፋ መሆኑን አጫወቱኝ::
አቶ ወርቁ ይሄ ቅጥ ያጣ የስልክ አጠቃቀም ከጫትና ከሲጋራው የከፋ ሱስ ሆኗል ይላሉ፤ ጫቱና ሲጋራው ደግሞ ቤት ተከትሎ አይመጣም ነበር ይሄ ከስልክ ጋር የተዳበለው ሱስ ግን ቀን አብሮ ውሎ አብሮ ያመሽና ወጣቱ ለምኝታ አንሶላ ውስጥ ሲገባም አብሮ የሚገባ አደገኛ ሱስ እየሆነ ነውና እባካችሁ በማለት ምክራቸውን ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ተመኙ::
እኔም ስለምክራቸውና ስለአስተያየታቸው አመስግኜ ከመቀመጫዬ ተነሳሁ። በዛች የጀበና ቡና መሸጫ ውስጥ ያለው ሰው ተበራክቷል። ሁሉም ሰው በጋራ ከቦ ተቀምጧል። አብዛኛው የሚጫወተው ግን በእጁ ካለው ስልክ ጋር እንደሆነ ስመለከት የአቶ ወርቁ ምክር እና አስተያየት እውነታነት ለማረጋገጥ እንደ ህያው ምስክር ሆኖ ታየኝ። የችግሩ አሳሳቢነትም ተሰማኝ።
እኔም ስለሁኔታው ይበልጥ ለማወቅና መፍትሔ ለማግኘት ወደ ፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል የሥነ አዕምሮ ህክምና ክፍል ጎራ አልሁ። ዶክተር ማቲዎስ ማሳኔ ይባላሉ፤ የስነ አዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት ናቸው። እኔን ጨምሮ አሁን ላይ ከህጻናት ጀምሮ እስከ አዋቂ ድረስ ስልክ ሰፊ ጊዜ መጠቀም የሚያስከትለውን ማህበራዊ መስተጋብር መጓደል እና የሚያመጣውን የጤና ጠንቅ በተመለከተ ጠየቅኋቸው:: በስልክችን የምናካሂደው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ብዙ ሰዓት የሚወስድብን ከሆነ2 ከሚጠበቀው በላይ ትኩረት የምንሰጠውና አዕምሮና ሀሳብን መቆጣጠር ከጀመረ2 ከማህበራዊ ህይወት እየነጠለና ተገዢ እያደረገን ከሆነ የሱስ ህመም ሆኗል ማለት ነውና በጊዜ መታከም እንደሚገባው ይመክራሉ።
የንጥረ ነገር ሱስ እና የባህሪ ሱስ እንዳለ የሚገልፁት ዶክተር ማቲዎስ፤ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን እየገዛን ሰዓታችን እና ሥራችን … እየተሻማን ከሆነ እንደ አዕምሮ በሽታ ስለሆነ መታከም አለበት።
ዘመኑ የኢንተርኔት ዘመን መሆኑ፣ የኮምፒውተር ጌም፣ ቲክቶክ፣ ዩቱብ…በባህሪያቸው አዕምሯችን ውስጥ ሱስ የማስያዝ አቅም ስላላቸው በቀላሉ ሰዎች ለመዝናናት እና ለመደሰት በሚል አብዝተው በመጠቀም የሱስ ህመም ደረጃ እንደሚደርስባቸው ዶክተር ማቲዎስ አስጠንቅቀዋል።
“ወጣቶች ትንሽ ፈታ ለማለት፣ ለመደሰት፣ ከጭንቅት ለመላቀቅ እና በሌሎች ምክንያቶች ወደዚህ ሁኔታ እንደሚገቡ የሚጠቅሱት ዶ/ር ማቲዎስ፣ ጉዳት የለውም ብሎ ማሰብ ግን ስህተት እንደሆነ ይገልፃሉ። ሥራ ላይ፣ ማህበራዊ ሕይወት ላይ፣ በቤተሰብ መካከል የአዕምሮ መዛባት እና ጭንቀትን ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቁመዋል።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ከልክ ያለፈ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ልቅ እየሆነ ከሱስ ህመም ደረጃ ከደረሰ በጊዜው ባለሙያ አማክሮ መታከም ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን ስሜቱ ይበላሻል፣ ጭንቀት ያገኘዋል፣ ቀስ እያለ ጤናማ የስነ ልቦና ህይወት አይኖረውም:: ከጊዜ በኃላም የአዕምሮ ጤና መታወክ ይገጥመማል፣ ከዛም ራስን አስከ ማጥፋት ያደርሰዋል።
“ስሱ በባህሪው እጅግ አስቸጋሪ ህመም ነው:: የሀኪም፣ የጓደኛ፣ የቤተሰብ፣ የማህበረሰብ… እገዛን የሚሻ ነው:: የስልክ አጠቃቀም ሱስ የሆነበትም ሰው በመድሀኒት፤ በንግግርና በስነ ልቦና መንገድ ታክሞ መዳን አለበት፤ ካልሆነ የከፋ ችግር ሊፈጥር ይችላል “ ይላሉ የስነአዕምሮ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ማቲዎስ። እኔም “ልብ ያለው ልብ ይበል” እያልኩ ፅሁፌን በዚህ ቋጨሁ፡፡
(ግርማ ሙሉጌታ)
በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


