‘‘የቀይ ባሕር ጥያቄ ከወደብ በላይ ነው”

0
41

ተወልደው ያደጉት በቀድሞ አጠራሩ ጐንደር ክፍለ ሀገር (በጌምድር)፣ ሊቦ አውራጃ፣ በለሳ ወረዳ፣ ጐሀላ በምትባል መንደር ውስጥ ነው:: ትምህርታቸውን የጀመሩትም በዚያው በጐሀላ  ሲሆን በወቅቱ ኢሕዴን ይባል የነበረው የፖለቲካ ድርጅት በአካባቢው የትጥቅ ትግል በመጀመሩ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል:: እንግዳችንም ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የቤተሰብ ግፊት አድሮባቸው እስከ አምስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን በአቅራቢያቸው በምትገኘው የአዲስ ዘመን ከተማ ቀጥለዋል:: ያም ሆኖ ግን ትምህርታቸውን ከስምንተኛ ክፍል በማቋረጥ ለትግል ወደ በረሃ አቅንተዋል::

እንግዳችን ትምህርታቸውን ለ10 ዓመታት ካቋረጡ በኋላ የደርግ መንግሥት መውደቁን ተከትሎ ትምህርታቸውን ካቋረጡበት ቀጥለዋል:: የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አያያዝ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሕዝብ ሥራ አመራር ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል:: በአሁኑ ወቅት የአማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዝደንት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ:: በብሔራዊ ጥቅም እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ!

 

በአንድ ሀገር ትውልዶች በዘመናት የሚያነሷቸው ብሔራዊ ጥቅሞች አሏቸው:: ብሔራዊ ጥቅም ምንድን ነው? የዚህ ትውልድ ዋነኛ ብሔራዊ ጥቅሞችስ ምንድን ናቸው?

ብሔራዊ ጥቅም አጠቃላይ ሀሳቡ አንድ ሀገር ሰላሙን፣ ደህንነቱን፣ ብልጽግናዉን እና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረውን ተሰሚነት እና ክብሩን ለማስጠበቅ ሲል የሚያስቀምጣቸው የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው:: ብሔራዊ ጥቅሞች በተለያዩ መንገዶች ተገልጸው ልናገኛቸው እንችላለን:: በጽሑፍ፣ በመሪዎች ንግግር እና በሌሎችም ሊሆን ይችላል::

ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ የብሔራዊ ጥቅም ሀሳብን ሕገ መንግሥታችን ላይ እናገኘዋለን:: የውጪ ጉዳይ ፖሊሲን በሚተነትነው አንቀጽ 86 ሰፍሮ እናገኘዋለን:: ከዛ ባሻገር ዘርዘር አድርጎ  የሚያስቀምጠው የውጪ ጉዳይ ፖሊሲያችን ነው:: ከዲፕሎማሲ ሥራዎች ጋር ተያይዞ በዝርዝር ተቀምጠዋል:: ከዚህ ባለፈ መሪዎቻችን በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ መድረኮች ላይ ከተናገሯቸው ተነስተን ብሔራዊ ጥቅም ምንድን ነው? ኢትዮጵያ በብሔራዊ ጥቅም ደረጃ ያስቀመጠቻቸው ግቦች እና መርሆዎች ምንድን ናቸው?  የሚለውን መገንዘብ እንችላለን::

በሀገራችን ከረጂም ጊዜ ጀምሮ የዘለቀው ብሔራዊ ጥቅም ሀገራዊ አንድነት ነው:: ከዚህ ባሻገር የግዛት አንድነት፣ ሰላም፣ ብልጽግና፣ እድገት፣ የመሳሰሉ ድርድር የማይደረግባቸው ናቸው:: እነዚህ አጀንዳዎች መንግሥትን እና ሕዝብን አንድ የሚያደርጉ ናቸው:: ምክንያቱም እነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱን ጠቅመው ሌላውን የሚጎዱ ሳይሆኑ  ከተሳኩ ሁሉንም ይጠቅማሉ ካልተሳኩ ሁሉንም ይጎዳሉ:: ከላይ የጠቀስናቸውን ብሔራዊ ጥቅሞች ከዚህ ቀደም የነበሩ መንግሥታት እና ትውልዶች ዋጋ የከፈሉባቸው ናቸው:: የአሁኑ ትውልድ እነዚህን ብሔራዊ ጥቅሞች ሊያስጠብቅ ይገባል:: ከእጃችን በታሪክ አጋጣሚ የወጡ እና የሚያስቆጩ ብሔራዊ ጥቅሞችም አሉ::

 

በታሪክ ከእጃችን ከወጡ ብሔራዊ ጥቅሞች መካከል ከቀይ ባሕር መገለላችን አንዱ ነው፤ ስለቀይ ባሕር ምን ሀሳብ አለዎት?

ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የረጅም የንግድ መስመሮች ባለቤት እና ዘዋሪ፤ በቀጣናው ተፅኖ መፍጠር የምትችል ኃያል ሀገር እንድትሆን ያደረገ የታሪካችን መሰረት፣ የገቢ እና የብልፅግናችን ምንጭ የነበረ ነው። ቀይ ባሕር ሀገራችን በታሪክ ያስመዘገበቻቸው የኃያልነት ሁነቶች ካስማ ነው፤ ባሕሩ መለያችን ነበር። እንዲሁም አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት መከፋፈል እና የይዞታ መገንጠልን ያስተናገዱት በቅኝ ግዥ ተይዘው ነበር፤ የዓለም ኃያል ሀገራት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው የጦር ሰፈር በመሰረቱበት በዚህ ቀጣና፤ በነፃነት የኖረች ሀገር ይዞታዋ ስለምን ሊገነጠል ብሎም ከባህር ልትርቅ ቻለች?’ በማለት ልንጠይቅ ይገባናል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ እንቅልፍ የሚነሳቸው፣ እድገቷን እና በቀጣናው ያላትን ሚና ዓይናቸውን ሳይነቅሉ የሚመለከቱ ታሪካዊ ጠላቶች አሏት። በዚህም ስትራቴጂካዊ እቅድ በመንደፍ የባሕር በር እንድናጣ እና ከእጃችን እንዲወጣ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ ባሻገር ለቀጣናዊ ደኅንነት መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን እንድታጣ የተደረገበት መንገድ ሕጋዊ መሰረት የሌለው በሀገር ላይ የተፈጸመ በደል ነው። ቀይ ባሕር ምዕተ ዓመታትን በተሻገረ ዘመን የኢትዮጵያ የንግድና የሥልጣኔ ማዕከል ሆኖ ማገልገሉን የታሪክ መዛግብትና ጸሐፍት የከተቡት የትውልዶች ሐቅ መሆኑ ይታወቃል። ከጥንት የአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮም ቀይ ባሕር የኢትዮጵያና ዜጎቿ የገናና ታሪክ መገለጫ እና የታላቅነት ሕያው ምስክር የተፈጥሮ ወሰን በመሆን ጭምር ማገልገሉን የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ።

ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የወቅቱ የኢትዮጵያ አስተዳደር ማስረጃ ባልተገኘለት አኳኋን ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት ከነበረችበት የቀይ ባሕር ቀጣና ውሉ በማይታወቅ የፖለቲካ ሴራ እንድትገፋ ሆኗል። የስልጣኔ መነሻ፣ የንግድ ግንኙነት ማዕከል፣ የተፈጥሯዊና ሕጋዊ ወሰን ከሆነው ቀይ ባሕር የተገፋችበት የታሪክ ስብራትም በዜጎቿ ላይ የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋትና የጂኦ-ፖለቲካ ስጋት ደቅኖ ቆይቷል። በአንድ ጥላ ስር የነበሩት የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች በታሪካዊ ጠላቶች በተሸረበ ሴራ በሁለት ሀገርነት ስም እንዲነጣጠሉ ተደርጓል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተነጠለችበት ኢ-ፍትሕዊ እና ፍርደ ገምድል ውሳኔም ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ቀጣና የመግፋት ታሪካዊ የፖለቲካ ሴራ ውጤት ነበር።  የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት እንድታጣ የተደረገበት መንገድ ሕጋዊ መሰረት የሌለው በሀገር ላይ የተፈጸመ በደል ነው። የኢትዮጵያ አካል የነበረው የአሰብ ወደብና አካባቢ ከአስመራ ከ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከኢትዮጵያ ግን  60 ኪሎ  ሜትር  በማይሞላ ቅርብ ርቀት ይገኛል።

 

ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር ለመግባት ያቀረበችው ጥያቄ የሚሳካ  ነው?

ኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይን በተመለከተ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እየሄደችበት ያለው መንገድ ተገቢና ፍትሐዊ ነው። ቀይ ባሕርን በጋራ ብንጠቀም ለተሻለ ትብብር በር የሚከፍት ነው። ቀይ ባሕር ሰፊ ሃብት የያዘ በመሆኑ ለቀጣናው ሀገራት ሁሉ ይበቃል፤ ስለዚህ በጋራ ብንጠቀም ምንም አይነት አሻሚ ጉዳይ አይነሳም። ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተነሱ ጫናዎችን በመቋቋም ግድቡን አጠናቃለች፤ በቀጣይም የባሕር በር ጥያቄ የማይመለስበት ምክንያት አይኖርም።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ቢኖራት የቀጣናውን ሀገራት ሕዝብ በልማት በማስተሳሰር ረገድ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል። ከባሕር በር ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ አካላት የተለያዩ ተጽዕኖዎችን ለማሳደር ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መብቷን ሁሉም ዜጋ ሊጠይቅ ይገባል፣ ቀደም ባለው ጊዜ በባሕር በር ጉዳይ ላይ የተፈፀመው ስህተት በአዲስ ታሪክ መታደስ አለበት።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ መውጫ ኮሪደር እፈልጋለሁ ስትል የባህር በር ብቻ ሳይሆን ህልውናዋንም ጭምር ለማስጠበቅ በማሰብ ነው:: የዓለም ሀገሮች 24 ሰዓት ዓይናቸውን የማይነቅሉበትን ቀይ ባሕርን ኢትዮጵያ በአንድ አጋጣሚ በስህተት አጥታዋለች። ቀይ ባሕር ጥንትም ቢሆን የኢትዮጵያ ይዞታ እንደነበር ይታወቃል። ቀይ ባሕርን ያጣነው አለአግባብ ነው።  ኢትዮጵያ የባሕር በር የመፈለጓ መሰረታዊ መነሻ የህልውና ጉዳይ ነው። የምትሠራውም የተነጠቀችውን ለማስመለስ እንጂ አዲስ ፍጠሩልኝ እያለች አይደለም። እኛ ኢትዮጵያዊያን በአባይ ግድብ ያሳየነውን አንድነታችንን በቀይ ባሕርም መድገም ካልቻልን ከአለም ተለይተን ተዘግቶብን መኖራችን ነው።

 

ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር ከምንገኝበት ሁለንተናዊ ችግር በምን እንውጣ?

ችግራችን የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጭ ጫናም ያለበት ነው:: ከሰላም ማጣታችን በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱ የሀገራችንን ሕዝብ በእጅጉ እየፈተነው ነው:: በተለይም የአማራ ክልል ብዙ ውስብስብ ችግሮች ገጥመውታል::  እነዚህን ችግሮች በተናጠል ሳይሆን በጋራ መፍታት ካልተቻለ የአንደኛው ክልል መታመም ለሌላውም ሕመም ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም:: የጋራ እሳቤ ከሌለን ሀገርን በጋራ ማዳን አንችልም:: ስለዚህ የጋራ እሳቤ ይዘን ለብሔራዊ ጥቅሞቻችን መረጋገጥ በአንድነት መነሳት ይኖርብናል::

 

ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የህዳር  8 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here