የባሕር በር… መልስ የሚያሻዉ ጥያቄ 

0
30

“ቀይ ባሕር ደማችን አሁንም ቀይ ናት

ጀግኖች በትግላቸው እስካሁን ያቆዩዋት…”

ቅድመ ግንቦት 1983 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሬድዮ እንዲሁም ቴሌቪዥን ከፍ ብሎ ይደመጥ የነበረ የዘፈን ግጥም ነው:: ግጥሙ ማንም ሰርዞ ደልዞ ሊያጠፋው የማይችል ታሪካዊ እውነታን የያዘ ነው፤ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ታሪካዊ ባለቤት የመሆኗን እውነት::

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል በተለይ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሰጡት አስተያየት እንዳወሱትም የቀይ ባሕር የቀድሞ ስም ባሕረ ነጃሽ (የሐበሻ ባሕር) ይባል ነበር:: በአክሱም ዘመነ መንግሥት የነበሩ የሐበሻ ነገሥታት ቀይ ባሕር ላይ ለሚፈጠር ውዝግብ እና አለመግባባት መፍትሔ ይሰጡ እንደነበርም የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ:: በጥቅሉ ቀይ ባሕር ከኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ ንግድ፣ ዕድገት… ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ነው::

ኢትዮጵያ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ከቀይ ባሕር ቀጣና ብትርቅም የቀደመ ታሪኳ ግን የዓለም ትልቁ የውኃ ላይ የንግድ መስመር ቀዳሚ ተዋናይ በዓለም የንግድ መስመር በከፍተኛ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ እንደነበረች ይመሰክራል::

ኢትዮጵያ ታሪካዊ የቀይ ባሕር ባለቤት ብትሆንም የግንቦት 1983 የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልመከረበት እንዲሁም ባልተስማማበት ሁኔታ፣ ውክልና የሌላቸው አካላት  ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንድታጣ እና የባሕር  በር እንዲዘጋባት አድርገዋል:: የሰው ዘር መገኛ እና የጥቁር ሕዝብ የነጻነት አርማ የሆነችው ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን በግፍ ተነጥቃ ለ36 ዓመታት ኖራለች::

ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣቷ የወጪ እና ገቢ ንግድ ዋጋ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጓል:: በዕድገት እና ሥልጣኔ ጎዳና ቀድማ ለመገኘት የምታደርገውን ጉዞ አስቸጋሪ አድርጎታል::

የዓለም ሀገራት በምጣኔ ሀብት ዕድገት ከፍተኛ ውድድር ውስጥ በገቡበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከቀሪው የዓለም ክፍል ጋር ተወዳዳሪ ሆና የምትወጣው፣ የንግድ እና የግንኙነት መረቧን የምታሰፋው የባሕር በር ሲኖራት መሆኑ አያጠያይቅም:: የባሕር በር እትዮጵያ በምጣኔ ሀብት ከሌላው ሀገር ጋር ተወዳዳሪ እና ቀዳሚ እንድትሆን ያስችላታል:: ለዚህም ነው  የባሕር በር ጥያቄ የኅልውና ጥያቄ ሆኖ የሚነሳው::

የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻርም የሚደገፍ እንደሆነ የሕግ ምሁራን ይገልጻሉ:: ኢትዮጵያ በታሪኳ የባሕር በር የነበራት ሀገር መሆኗ፣ በጂኦ ፖለቲካም ከቀይ ባሕር ያልራቀች (ከአሰብ ወደብ 60 ኪ.ሜ የምትርቅ መሆኗ) በመሆኗ ጥያቄው በየትኛውም መመዘኛ አግባብነት ያለው ለመሆኑ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው::

ጥያቄው ምላሽ ያገኝ ዘንድ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችው ባልተገባ የፖለቲካ ሸፍጥ፣ ዓለም አቀፍ ሕግን ባልተከተለ መልኩ መሆኑን ማጤን እና  የባሕር በር የማግኘት መብቷ እንዲከበር መጠየቅ ተገቢ ጥያቄ ነው::

 

በኲር የህዳር  8  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here