ዴንማርክ ሙስናን እንዴት ተከላከለች?

0
60

“ሙስና” የሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም ያለው ቢሆንም የሥልጣን ወይም የኃላፊነት ቦታን ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም አላግባብ መጠቀም የሚለው ትርጉም ግን ብዙዎችን የሚያስማማ  ነው። ሙስና ማለት ሕግን፣ ደንብን ወይም የሥነ-ምግባር መርህን በመጣስ የግል ጥቅም ለማግኘት ሲባል የሚፈጸም እምነትን የማጉደል (ክህደት) ድርጊት ነው።

ሙስና ዓለማችንን ከጦርነት፣ ከረሃብ፣ ከበሽታ እና ከተፈጥሮ አደጋ ባልተናነሰ ኢኮኖሚን እያደቀቀ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። ዓለም ባንክ እ.አ.አ በ2017 ኮምባቲንክግ ኮራፕሽን (Combating Corruption) በሚል ባወጣው መረጃ ላይ በዓለማችን ግለሰቦች እና የንግድ ተቋማት በዓመት ከአንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ጉቦ እንደሚከፍሉ አመላክቷል።

በአንዲት ሀገር ሙስና እንዲንሰራፋ ከሚያደርጉ ምክንያቶች የመጀመሪያው የሀገራት የሕግ፣ የአሠራር ሥርዓት እና የመንግሥት አደረጃጀት ክፍተት መኖር እንደሆነም መረጃው አክሏል::  ሀገራት የፀረ-ሙስና ሕጎች ቢኖሯቸውም ግን በብቃት የማይተገበሩ ወይም ሙስና  የፈፀሙትን ለመቅጣት የሚያስችል ጠንካራ የፍትሕ ተቋማት ካልገነቡ  ድርጊቱን መከላከል አዳጋች መሆኑ ተጠቁሟል::

በሙስና ዙሪያ መረጃዎችን የሚያወጣው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት እ.አ.አ በ2024 ባወጣው ሪፖርት ሶማሊያ፣ ቬንዝዌላ፣ ሶሪያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ የመን ሊቢያ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኤርትራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሙስና ችግር እንዳለባቸው አረጋግጧል። ለዚህም ሀገራት በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በሕግ የበላይነት መዳከም፣ በኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በመንግሥት ተቋማት መዳከም፣ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በመንግሥት ግልጽነት መጓደል፣ የፖለቲካ ሥልጣንን ያለአግግባብ በመጠቀም ምክንያት የተፈጠረ እንደሆነ ድርጅቱ በሪፖርቱ አመላክቷል።

መረጃው እንደሚጠቁመው በዓለም ሙሉ በሙሉ  ከሙስና ቅሌት ነጻ የሆኑ ሀገራት የሉም፤ ይሁን እንጂ ሙስናን በመከላከልና በመቆጣጠር  የላቀ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት አሉ፤ ከእነዚህ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ዴንማርክ ናት። ዴንማርክ ሙስናን በመከላከል ረገድ ከሌሎች ሀገራት ለየት የሚያደርጋት የጸረ ሙስና ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን መገንባቷ እና ገለልተኛ የፍትሕ  ተቋማትን ማጠናከሯ ነው። ይህም የሕግ የበላይነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን አስችሏታል።

ሀገሪቱ ጉቦ መስጠትንና መቀበልን፣ ማጭበርበርን እና የመንግሥትን ገንዘብ መዝረፍን የሚከለክሉ ጥብቅ ሕጎችን አውጥታለ፤ ተፈጻሚም ናቸው።

የሀገሪቱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው ደግሞ የዴንማርክ የፍትሕ ተቋማት  ከፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ሙሉ በሙሉ ነፃ ናቸው። ዳኞች የሚሾሙት በችሎታ እና በታማኝነት ላይ ብቻ ተመሥርተው ነው:: የሙስና ወንጀልን ጨምሮ ማንኛውም ሕገወጥ ድርጊት ያለ ምንም አድልዎ እና እጅ መንሻ /ጉቦ/ ይዳኛሉ። የመንግሥት ባለሥልጣናት  የሙስና ወንጀል ሲፈጽሙም ያለምንም ይቅርታ እንደ ማንኛውም ዜጋ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃዎች ይወሰንባቸዋል፤ ይፈረድባቸዋል። ውሳኔዎች ለሕዝብ ክፍት በመሆናቸው  ማንም ሙስናን በድብቅ መፈጸም አይችልም።

የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖርም ሌላው መከላከያ መንገዷ ነው። የፖለቲካ መሪዎች ከሙስና ጋር ለመዋጋት ያለማቋረጥ ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል።

ሀገሪቱ የመንግሥት ሠራተኞች በሕይወታቸው ዘላቂና የተረጋጋ ገቢ እንዲያገኙ የሚያስችል  በቂ ደመወዝ  ትከፍላለች::   ይህ የፋይናንስ መረጋጋት ደግሞ የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል እና ሙስና ለመፈጸም የሚገፋፋውን የኢኮኖሚ ፍላጎት ለመቀነስ ያለመ ነው። ይህም የፋይናንስ ስጋትን በመቀነስ ጉቦ እንዲቀበሉ የሚገፋፋቸውን ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ገድቦላታል። የመንግሥት ሠራተኞች የሙስና ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦችንም ሆነ ባለሥልጣናትን ሲያዩ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ሲያደርሱ  ጥበቃ እና ከለላ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን አስቀምጣለች። ይህም ሠራተኞች ያለፍርሃት የሙስና ወንጀልን እንዲያሳውቁ እና ሙስናን እንዲዋጉ  አስቻይ ሁኔታን ፈጥሮላታል።

የመንግሥት የሥራ ቅጥርና ምደባም ቢሆን በሕጉ መሠረት ይፈጸማል። የመንግሥት ሠራተኞች በዝምድና ወይም በገንዘብ ሳይሆን በትምህርት ላይ በተመሠረተ ብቃትና ዕውቀት እንዲቀጠሩ ተደርጓል። ይህም ታማኝ እና ብቁ የአስተዳደር አካል እንዲገነባ አስችሏል።

ሌላው  የሙስና መከላከያ መንገዷ በመንግሥ ላይ እምነት ያለው ማህበረሰብ  መገንባቷ ነው። ዴንማርክ ሙስናን ለመከላከል ባደረገችው ዘላቂ ጥረት የዜጎች ተሳትፎ መሰረታዊ እና ወሳኝ ሚና አለው። ዴንማርክ ጠንካራ የሆነ የማኅበራዊ ዋስትናና ከፍተኛ የግብር ሥርዓት አላት። ይህ የገቢ ልዩነትን በመቀነስ ኢኮኖሚያዊ እኩልነትን ያሰፋል። በዚህ ምክንያት ዜጎች የመንግሥት ሀብት በፍትሐዊነት እንደሚመራ ያምናሉ፣ ይህም ሙስናን የመቃወም ባህል እንዲጎለብት አግዟታል።: ዜጎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት አንዳቸው ለሌላው ከፍተኛ አክብሮትና መተማመን ፈጥሮላታል። ሙስናንም ለመከላከል አስችሏታል::

ዴንማርኮች “ሙስናን ምንጊዜም ቢሆን  እንዋጋዋለን፣ ሙሰኞችንም አይቶ ከማለፍ ይልቅ በገሀድ ያለምንም ፍርሃት እናጋልጣለን:: ምክንያቱም ሀገሪቱ እኛን ሊጠብቅ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ ዘርግታለች” የሚል አቋም አላቸው::

የቢቢሲ መረጃ እንዳመላከተው የዴንማርክ የፀረ-ሙስና ስኬት የመረጃ ግልጽነት እና ተደራሽነት ሕግን ማስፈኗ ሌላው ምክንያት ነው። ዜጎችም ነፃ እና ገለልተኛ ለሆኑ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን መረጃ በማቅረብ እና በማጋለጥ የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

ዴንማርኮች በመንግሥት አገልግሎት ሠጭ ተቋማት ጉዳያቸውን የሚያስፈጽሙት በጉቦ አይደለም። ምክንያቱም አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ።  አገልግሎት  ለማግኘት ለመንግሥት ሠራተኞች ጉቦ ለመስጠትም ፈቃደኛ  አይደሉም። የሚሰጥ ካለም ያወግዛሉ።  በጉቦ ጉዳዩ እንዲፈጸምለት የሚፈልግ ሠራተኛም ሆነ ባለሥልጣን ካለ ለሚመለከተው አካል ለማጋለጥ ወደ ኋላ አይሉም። ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበትም ክትትል ያደርጋሉ።

የሕዝብ ገንዘብ በታቀደለት ዓላማ ላይ መዋሉን ወይም ወደ ሙሰኞች ኪስ መግባቱን ይከታተላሉ፣ ያጣራሉ።: በትላልቅ የመንግሥት ግዢዎች ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት መኖሩንም ያረጋግጣሉ።

ሕጻናት ከልጅነታቸው ጀምሮ ስለሙስና አስጸያፊነት እንዲሁም የሞራልና ግብረገብ ትምህርቶችንም ይማራሉ። ይህ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር አስችሏታል።

የዴንማርክ ባሥልጣናት በማንም አይታጀቡም። በሕዝብ ገንዘብም የቅንጦት መኪና አይገዛላቸውም። በነዋሪዎችና በባለሥልጣን መካከል ልዩነት የለም። በመካከላቸው የበላይና የበታች የሚባል ነገር የለም። በሕግ ፊት ሁሉም እኩል ይዳኛሉ።

በተመሳሳይ ሙስናን ለመዋጋት የሚያስችል ብሎክቼይን የተሰኘ ቴክኖሎጂን በማበልጸግ እየተጠቀመችበት መሆኑን ፍራንስ 24 አስነብቧል። ይህ ቴክኖሎጂ የመንግሥት  ግዥዎችን፣ ጨረታዎችን እና ውሎችን በግልጽነት ለመከታተል፣  ማጭበርበርን ለመከላከል እና  ተጠያቂነትን ለማስፈን አስችሏታል። ቴክኖሎጂው ግለሰቦች ሙስና የፈጸሙ አካላትን ያለምንም ፍርሀት እና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲያጋልጡ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቶላታል። የግዥ ሂደቶችን በዲጂታል በመከታተል የበለጠ ግልጽ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ሥርዓት እንዲፈጠር ብሎም ሙስና እና ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ  አስችሏል።

ሌላው በሀገሪቱ ሙስናን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወተው የመገናኛ ብዙኃን (Media) ነው። መገናኛ ብዙኃን ሙስናን በመዋጋት ረገድ ሚናው እጅግ ወሳኝ ነው። የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ነጻና ገለልተኛ በመሆን የሙስና ወንጀልን መመርመርና በማጋለጥ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ።

የሕዝብ ገንዘብ ያለአግግባብ የሚውልባቸውን ፕሮጀክቶች፣ አድሏዊ የሆኑ ኮንትራቶችን እና የባለሥልጣናት የንብረት መጨመርን በምርመራ ዘገባ (Investigative Journalism) በመከታተል በአደባባይ ያጋልጣሉ። በሙስና የተጠረጠሩትን ግለሰቦች፣ ባለሥልጣናት እና ድርጅቶች ስም ያጋልጣሉ። ሙስና በሀገሪቱ ማኅበራዊ ተቀባይነት የሌለው አስነዋሪ ተግባር እንደሆነም ያስተምራሉ።

በሙስና ዙሪያ ሕዝባዊ ውይይቶች የሚካሄድበት መድረክም ይፈጥራሉ። በዚህም  ፖሊሲ አውጪዎችና የፀረ-ሙስና ተቋማት የሕዝብን አስተያየት በመስማት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ያደርጋሉ።

ታዲያ ይህ ሁሉ ሚና ውጤታማ እንዲሆን ያደረገው ሀገሪቱ ለመገናኛ ብዙኃን ነፃነት መስጠቷ ነው::

ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚናም ከፍተኛ ነው። እነዚህ ድርጅቶች በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረቱ እና የሕዝብን ጥቅም የሚያስጠብቁ ናቸው። ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ብሎም  ለመልካም አስተዳደር  ዋጋ በመስጠት ሙስናን ይዋጋሉ።

ዴንማርክ ሙስናን በመከላከሏ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን አስገኝቶላታል። በኢኮኖሚ ዘርፉ  የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን እንድትስብ አስችሏታል። ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ያለምንም ስጋት በዴንማርክ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ በንግድ ግንኙነት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ያላትን ተሰሚነት አሳድጎላታል።

እንደ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ ዴንማርክ በዓለም ላይ በጣም ደስተኛ ዜጋ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

በአጠቃላይ ዴንማርክ ሙስናን በመከላከል  ዜጎቿ በመንግሥት ላይ ጠንካራ  እምነት እንዲኖራቸው አስችሏል። ይህም የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብርን እና ፖለቲካዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ አስችሏታል።

እንደ መውጫ

አፍሪካ ኢንስቲትዩት ኦፍ ማኔጅመንት፣ ዴቬሎፕመንት ኤንድ ገቨርናንስ የተሰኘ ተቋም በአፍሪካ ባደረገው ጥናት ሙስና ሀገሪቱን   በየዓመቱ 148 ቢሊዮን ዶላር ያሳጣታል። አፍሪካዊያን ከተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ባለፈ በሙስና የሚደርስባቸው ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር ከፍተኛ ነው::

የሕግ አንቀጽ

 

የሙስና ወንጀል አይነቶች

በአዋጅ 881/2007 በርካታ የሙስና ወንጀል ተግባራት የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከባድ እምነት ማጉደል ይገኝበታል፡፡

እምነት ማጉደል አስቀድሞ የተሰጠን አምነት ካለአግባብ መጠቀምን ያመለክታል፡፡ በዚህም ከባድ እምነት ማጉደል ሲባል በአዋጅ 881/07 አንቀጽ 31 መሰረት ያልተገባ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ  የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት ወይም በአደራ የተሰጠውን ዋጋ ያለውን እቃ ወይም ገንዘብ  በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ማድረግ፣ መውሰድ፣ መሰወር፣ ለራሱ ወይ ለሌላ ሰው አገልግሎት ማዋል እና መሰል ድርጊቶችን መፈጸም ነው፡፡ ድርጊት ፈጻሚውም ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ  ጽኑ እስራት እና ከአስር ሺህ ብር እስከ ሀምሳ ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ደንግጎ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የስሥልጣን ደረጃ፣የደረሰው ጉዳት መጠን ከፍተኛነት እየታየ ቅጣቱ ከሰባት እስከ ሀያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት እና ከሀምሳ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር መቀጮ ድረስ ሊቀጣ ይችላል።

ምንጭ፡- የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር፡፡

 

(ቴዎድሮስ ደሌ)

በኲር የሕዳር  15 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here