የበጋዉ ሲሳይ

0
40

የአማራ ክልል ከፍተኛ የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር ውኃ ባለቤት ነው:: ዓባይን ጨምሮ እንደ ተከዜ፣ ሽንፋ፣ አይማ፣ አንገረብ፣ ፈጣም፣ ተምጫ፣ ሽና፣ ብር ወንዝ… ያሉ ትላልቅ ወንዞች እንዲሁም የጣና፣ የዘንገና እና ሌሎች ኃይቆች መገኛም ነው። እነዚህ ሀብቶች ለመስኖ ልማት በእጅጉ የተመቹ ቢሆኑም የክልሉ ተጠቃሚነት ግን ከዓመታት በፊት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።

ክልሉ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የመስኖ ልማቱን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግም በክልሉ በየአካባቢው ባሉ የውኃ ሀብቶች እና ለአየር ሁኔታው ተስማሚ በሆኑ ሰብሎች ላይ ተመስርቶ በጥናት የታገዘ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም መረጃው አክሏል።

በዚህ ወቅት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር ባደረግነው የስልክ የመረጃ ልውውጥ እንደተገነዘብነው አርሶ አደሮች በመኸር ያለሙትን ሰብል ከመሰብሰብ ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ዝግጅት እያደረጉ ነው። ከቅድመ ዝግጅት አልፎም ማሳቸውን በዘር እየሸፈኑ  እንደሆነ መገንዘብ ችለናል።

አርሶ አደሮቹ የመሬት ልየታ፣ ደጋግሞ ማረስ፣ የመስኖ ቦይ (ካናል) ጠረጋ፣ የውኃ ጠለፋ፣ የግብዓት እና ዘር ዝግጅት  ማድረጋቸውን ነው በስልክ ያጋሩን። ከእነዚህ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አገኘሁ እንየው አንዱ ናቸው።

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የጓንጓ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አገኘሁ እንየው፤ ”ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመስኖ ልማት ላይ በልዩ ትኩረት በመሥራቴ የተሻለ ምርት እያገኘሁ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት የስንዴ ልማት ለመንግሥት ጥቅም እንጂ በግል ሕይወቴ ለውጥ የሚያመጣ አደለም የሚል አመለካከት ነበርኝ” በማለት በፊት ለመስኖ ልማት የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት ለበኵር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል።

እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ የመስኖ ልማትን የጀመሩት በ2013 ዓ.ም ነው። በወቅቱ በዜሮ ነጥብ 75 ሄክታር /በሦስት ገመድ/ መሬታቸው ላይ ያገኙት ምርት ካሰቡት በላይ እንደ ነበር ያስታውሳሉ:: ያኔ በስጋት የተጀመረው የመስኖ ልማት ዛሬ ድረስ በውጤት ታጅቦ ዘልቋል፤ የቤተሰቡን ኑሮም  እንዳሻሻለው ይመሰክራሉ::

አርሶ አደሩ እንደተናገሩት በበጋ መስኖ  የላቀ  ምርት እንዲገኝ በቂ ግብዓት በተመጣጣኝ ዋጋ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተደራሽ ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል::

ሌላው ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደሚገኙ የነገሩን በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ብርብራ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ስዩም አግዜ ናቸው። አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅት ለመስኖ የሚሆን ማሳቸውን አርሰው ለዘር ዝግጁ አድርገዋል። በግማሽ ሄክታር/በሁለት ጥማድ/ መሬታቸው ላይ ቀይ ሽንኩርት ለማምረት ያቀዱት አርሶ አደሩ ከዚህም 80 ኩንታል ምርት አገኛለሁ የሚል ዓላማ አላቸው።

ከስንዴ እና ቀይ ሽንኩርት በተጨማሪ በበጋው ወቅት ቲማቲም እና አቮካዶ እንደሚያመርቱም ተናግረዋል። አርሶ አደር ስዩም በመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን በማስታወስ ሌሎች አርሶ አደሮችም በመስኖ ልማቱ በመሳተፍ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የእርሳቸውን ተሞክሮ ዋቢ አድርገው ምክር ለግሰዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ በ2018 ዓ.ም 42 ሺህ 977 ሄክታር መሬት በነባር እና በአዲስ በተለያዩ ሰብሎች በመስኖ ለማልማት ማቀዱን አስታውቋል። በምርት ዘመኑ በመስኖ ከሚለማው ሰብል አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን ነው የገለፀው።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ አዲሱ ዓለሙ ለበኵር በስልክ እንደተናገሩት በብሔረሰብ አስተዳደሩ በዘንድሮው የበጋ ወቅት አዳዲስ አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመስኖ ለማልማት በትኩረት እየተሠራ ነው።

በመኸር ተዘርተው ምርቱ በተሰበሰበባቸው ቆላማ አካባቢዎች ቀድመው ወደ እርሻ (የበጋ መስኖ ልማት) እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ቡድን መሪው ጠቁመዋል:: ምርታማነትን ለማሳደግ ለሥራው የሚያገለግሉ ግብዓቶችን የማሟላት ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በዚህ ዓመት በነባር መስኖ 37 ሺህ 49 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ በ26 ሺህ 824 ሄክታር መሬት ላይ የእርሻ ሥራ ተከናውኗል። አምስት ሺህ 977 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም ገልፀዋል። በአዲስ መስኖ ለማልማት ከታቀደው አምስት ሺህ 928 ሄክታር መሬት እስካሁን ሦስት ሺህ 258 ሄክታር  ተለይቶ 896 ሄክታር ታርሷል። 45 ሄክታሩ ደግሞ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።

በበጋው በመስኖ ከሚለማው  መሬት ውስጥ 28 ሺህ ሄክታሩ  በመስኖ ስንዴ የሚሸፈን እንደሆነም ተመላክቷል። ከዚህም አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ  ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ባሁኑ ወቅት  16 ሺህ 530 ሄክታር መሬት ታርሷል፤ ከዚህም አንድ ሺህ 409 ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል።

ቡድን መሪው እንዳሉት የመስኖ ልማት ዕቅዱን ለማሳካት የእርሻ ሥራ እና የቦይ ጠረጋን ጨምሮ ሰፊ ዝግጅት ተከናውኗል:: ለመስኖ ልማቱ በቂ የማዳበሪያ  እና የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል::  አሁን ላያ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አንድ ሺህ 800 ለሥራ ዝግጁ የሆኑ የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች እንዳሉ እና ሌሎች ብልሽት የገጠማቸው ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ጠጋኝ ባለሙያ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው። ዕቅዱ ስኬታማ እንዲሆን  በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት እና የግብርና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን  እንዲወጡም  መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የበጋ መስኖ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን ለበኵር ጋዜጣ አስታውቋል። የዞኑ ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ ዘሩ ገረመው  በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት በነባር 35 ሺህ 417 ሄክታር፤  በአዲስ 19 ሺህ 804  ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማ ጠቁመዋል። በመስኖ ከሚለማው አጠቃላይ ማሳ ውስጥ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ገልጸዋል። ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ለአርሶ አደሮች 126 ሺህ 250 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 39 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ተዘጋጅቷል:: ከግብዓት በተጨማሪ ስድስት ሺህ 645 የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችም ለአርሶ አደሮች መሠራጨታቸውን ተናግረዋል።

የአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት ባለሙያው፤  ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ድረስ 25 ሺህ 362 ሄክታር መሬት  የታረሰ ሲሆን ከዚህም 12 ሺህ 525 ሄክታሩ  በዘር ተሸፍኗል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2018  በበጋ መስኖ የሚገኘውን ምርት  ለማሳደግ ከ331 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በነባር እና ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአዲስ ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከዚህም ከ52 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን አክሏል::

ከዚህም ክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ 260 ሺህ ሄክታር መሬት  በማልማት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ነው የቢሮው የመስኖ ውኃ አጠቃቀም አግሮኖሚ ባለሙያ አቶ ንጋቴ አለማየሁ ለበኵር የተናገሩት። በክልሉ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ የሚለማ ምቹ መሬት ቢኖርም እስካሁን ማልማት የተቻለው ግን ከ300 ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥ ነው ባለሙያው ያመላከቱት።

ባለፈው ዓመት (2017 ዓ.ም) 208 ሺህ 236 ሄክታር  የሚጠጋ ማሳ በመስኖ ስንዴ በማልማት ሰባት ሚሊዮን 464 ሺህ 389 ኩንታል ምርት እንደተገኘም አስታውሰዋል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት (ኅዳር 11 ቀን 2018 ዓ.ም) 25 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም ነው ባለሙያው የተናገሩት። ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ21 ሺህ ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል:: ይህም የሆነው ቀድሞ ወደ ሥራ መገባቱ ነው:: የመስኖ ልማትን በትንሽ ማሳ ላይ በማልማት ክንውኑ  ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። በመስኖ ልማቱ ላይ የአርሶ አደሩ እውቀት፣ አቅም እና ልምድ እያደገ መሆኑንም ጠቁመዋል::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በበጋ መስኖ ስንዴ በሄክታር 37 ኩንታል የነበረውን ምርታማነት በዚህ ዓመት (2018 ዓ.ም) ወደ 40 ኩንታል ለማሳደግ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር መግባባት ተፈጥሮ ወደ ሥራ ተገብቷል። የታቀደውን  ምርት ለማሳካት  አጋር እና ባለድርሻ አካላት በቅንጀት እና በትብብር መሥራት እንደሚገባቸውም የውኃ አጠቃቀም ባለሙያው መልዕክት አስተላልፈዋል። አርሶ አደሩ የእርጥበት ጊዜው ሳያልፍ እና የውኃ መጠኑ ሳይቀንስ ፈጥኖ ማሳውን በዘር ለመሸፈን   ያለውን የውኃ አማራጭ ተጠቅሞ በመስኖ ልማቱ ላይ በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል።

 

ዜና

ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰብሎችን በፍጥነት እየሰበሰበ መሆኑን አስታወቀ

የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እና በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታውቋል።

በ2017/18 የምርት ዘመን 58 ሺህ 763 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች መሸፈኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያው ብርሐኑ ሞገስ ለበኵር ተናግረዋል። ከዚህም ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ቦሎቄ እና ማሾ እየተሰበሰቡ ያሉ ሰብሎች ናቸው ብለዋል::

መረጃው እስከተጠናቀረበት ኅዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም 22 ሺህ 923 ሄክታር  የተሸፈነ ሰብል መሰብሰቡንም ባለሙያው  ገልፀዋል:: የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እና በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሠራ ስለመሆኑም አክለዋል::

አርሶ አደሩም ሰብሎን በወንፈል (በደቦ) እየሰበሰበ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ብርሐኑ፤ አርሶ አደሮችም የደረሱ ሰብሎችን የምርት ብክነት እንዳይኖር በፍጥነት እና በጥንቃቄ የመሰብሰቡን ሥራ በትኩረት እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 15 ቀን 2018  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here