የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት!

0
27

በሀገራችን በኢትዮጵያም ሆነ በአማራ ክልል የበጋ መስኖን ጨምሮ  አዳዲስ መሬቶችን ወደ ምርት በማስገባት፣ ዘመናዊ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችንም በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

ምርትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ቢሆንም የምርት ብክነት እና ጥራት ጉድለት ደግሞ የዘርፉ ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ሰብልን በወቅቱ አለመሰብሰብ፣ የተሰበሰበን ሰብል ዝናብ  በማያስገባ እና እርጥበት በማይፈጥር መልኩ አለመከመር፣ ሰብልን በከብት እና በሰው ኃይል መውቃት፣ ወዘተ ለምርት ብክነት  ዋና መንስኤዎች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡

የጎተራ ተባዮችን የሚቀንሱ የተሻሻሉ የሰብል ማከማቻ ዘዴዎችን  ወይም ቴክኖሎጂዎችን አለመጠቀም፣ የከረመ እና አዲስ ሰብልን ቀላቅሎ ማስቀመጥ፣ የሰብል ማከማቻዎችን በአግባቡ አለማፅዳት እንዲሁም  ፀረ-ተባይ መድኃኒቶችን በአግባቡ አለመጠቀምም የምርት ብክነትን የሚያስከትሉ ምክንያቶች ናቸው፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአማራ ክልል በ2017/18 የምርት ዘመን 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኜት አቅዶ እየሠራ ቢሆንም በምርት ዘመኑ በምርት አሰባሰብ እና በአያያዝ ጉድለት ምክንያት ከፍተኛ ምርት ይታጣል፡፡

በመሆኑም ብክነትን ለማስቀረት በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኜው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ምርትን በወቅቱ መሰብሰብ፣ ዝናብ   በማያስገባ እና እርጥበት በማይፈጥር መልኩ መከመር እንዲሁም መውቃት፣ ከውቂያም በኋላ በጥንቃቄ ወደ ጎተራ ማስገባት፣ የተሻሻሉ የእህል ማከማቻ ዘዴዎችን (ቴክኖሎጂዎችን) መጠቀም እንዲሁም ጎተራን በአግባቡ ማፅዳት በየደረጃው እየተተገበሩ ያሉ የምርት ብክነት መቀነሻ ዘዴዎች ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሠማሩ አርሶ አደሮች  የምርት ብክነትን ለመከላከል የደረሱ  ሰብሎችን ወቅቱን ጠብቀው በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ የሰበሰቡትን ምርት ወደ ገበያ እስከሚያቀርቡ ድረስም ደረጃውን በጠበቀ መጋዝን ውስጥ አከማችተዋል፡፡ የግብርና ባለሙያዎችም ለአርሶ አደሮች ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡

ብክነትን በመቀነስ የታቀደውን ምርት ለማሳካት በየደረጃው እየተደረገ ያለው ይህን መሰሉ ድጋፍ እና ክትትል ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩልም የእርሻ ሜካናይዜሽንን ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ነው፡፡ ይህ ርምጃም ለዘመናት በበሬ ትከሻ በማረስ፣ በሰው ጉልበት ምርት በመሰብሰብ እና በእንስሳት ጉልበት ምርትን ከገለባ በመለየት ይባክን የነበረውን የአርሶ አደሩን ጉልበት እና ጊዜ ከመቆጠብ ባለፈ የምርት ብክነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ነው፡፡

ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን በስፋት መተግበርም አርሶ አደሮች ያላቸውን የተበጣጠሰ መሬት አቀናጅተው በዘመናዊ መንገድ  እንዲያመርቱ  ዕድል የሚፈጥር እና ለምርት ብክነት በከፍተኛ መጠን መቀነስ ሁነኛ መፍትሄ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

በኲር የህዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here