የልማቱ  አካል ብንሆን…

0
57

በዓለማችን አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ለአካል ጉዳት የተዳረጉ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያም 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ለዚሁ ችግር ሰለባ ናቸው። በተመሳሳይ በአማራ ክልልም አራት ሚሊዮን የሚጠጋ አካል ጉዳተኛ እንዳለ ከአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማሕበራት ፌደሬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል። ታዲያ ይህን ያህል ቁጥር ያለውን ማህበረሰብ ታሳቢ ያደረጉ የልማት ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ብዙዎች ያሳስባሉ።

ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን አካል ጉዳተኛ የሚለውን ፅንስ ሐሳብ ሲያብራራ አንድ ሰው በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በማኅበረሰቡ ውስጥ የአካል ጉዳት እንደሌለባቸው ሰዎች በእኩልነት መሳተፍ ባለመቻል ምክንያት የሚፈጠር ውስንነት መሆኑን አስቀምጧል። አካል ጉዳተኝነትም በተለያየ መልኩ የሚገለፅ መሆኑን ያነሳል፡፡

አቶ ፍሬሰላም ዘገዬ የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማሕበራት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ናቸው፤ አካል ጉዳት ተከሰተ የሚባለው ከሰውነት አካላችን አንዱ የሚጠበቅበትን ሥራ ማከናወን ሳይችል ሲቀር ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ። ለአብነትም ዓይን ተግባሩ ማየት ሲሆን ማየት ሳይችል ሲቀር የዓይን ስውርነት ጉዳት ተከሰተ ይባላል።

አካል ጉዳተኝነት በየትኛውም ጊዜ፣ በማንኛውም የዕድሜ ክልል፣ በማንኛውም ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ብሔር እና ቀለም ሳይለይ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ የሚከሰት ጉዳት መሆኑንም አስገንዝበዋል። በመሆኑም የአካል ጉዳተኞችን መብት እና ሰብዕና የሚጋፉ ተገቢ ያልሆኑ ንግግሮች መታረም እና መስተካከል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸው እንዲከበር፣ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ሁለንተናዊ ጥቅማቸው (ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ) ተጠብቆ ተሳትፏቸው እንዲጨምር በየዓመቱ የአካል ጉዳተኞች ቀን እየተከበረ ይገኛል። የዘንድሮው የአካል ጉዳተኞች ቀንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ “የአካል ጉዳተኝነትን ያካተተ ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማሕበራዊ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ይገኛል።

የክልሉ አካል ጉዳተኞች ማሕበራት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ፍሬሰላም ዘገዬ ለአሚኮ እንደተናገሩት ፌደሬሽኑ በክልሉ ያሉ ማሕበራትን በማስተባበር አካል ጉዳተኞች የልማቱ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ የልማቱ አካል እንዲሆኑ በቁርጠኝነት እየሠራ ነው። በመሠረተ ልማት ሥራዎች መልካም ጅማሮች ቢኖሩም ገና ብዙ ሥራን የሚጠይቅ ነው። በሀገር ምጣኔ ሀብት ግንባታ የአካል ጉዳተኞች ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ፍሬሰላም አዲስ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች እነሱን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

አቶ ፍሬሰላም እንዳሉት ዘንድሮ በዓሉን እንደወትሮው በአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በሰፊው ለመሥራት ታስቦ የኅዳር ወር ሙሉ “የአካል ጉዳተኞች ወር” ተብሎ እየተከበረ ይገኛል። አከባበሩ ከወረዳ ጀምሮ (ከኅዳር 01 -15)፣ ከዚያም በዞን እና ከተማ አስተዳደር (ከኅዳር 15 -20)፣ በመጨረሻም በክልል ደረጃ ኅዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ነው። ይህም ከፍተኛ ንቅናቄ በመፍጠር የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል ነው የተባለው።

ማኅበረሰቡ ስለ አካል ጉዳተኝነት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የኅዳር ወር ሙሉውን ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራባቸው ነው። ለዚህም ሰነዶች ተዘጋጅተው እስከ ታችኛው መዋቅር ተልከዋል፤ እሱ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በዚህም ከ288 በላይ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ከ280 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ ለአካል ጉዳተኞች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የቅስቀሳ እና የማግባባት ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፣ ለአብነትም ለሦስት ሺህ አካል ጉዳተኞች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ ስለመሆኑ አቶ ፍሬሰላም ነግረውናል። “አካል ጉዳተኞች በራሳቸው የገቢ ማስገኛ ላይ ተሰማርተው ኑሯቸውን መምራት፣ ቤተሰቦቻቸውንም ማስተዳደር እንዲችሉ፣ ከራሳቸው አልፈው በሀገር ምጣኔ ሀብት ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በራሳቸው የገቢ ማስገኛ በመሰማራት በቋሚነት ወደ ሥራ እንዲገቡ እየሠራን ነው” ብለዋል።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከሁለት ሺህ 500 በላይ አካል ጉዳተኞች የምግብ፣ የአልባሳት እና የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም እየተሠራ ነው። ለዚህም እስከ 14 ሚሊዮን ብር ሀብት ከኅብረተሰቡ፣ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ከመንግሥት ለማሰባሰብ ታቅዷል። የሙያ ክህሎት ስልጠናዎችን እንዲያገኙም እየተደረገ ነው።

ከባድ መሰናክሎችን አልፈው ውጤታማ የሆኑ አካል ጉዳተኞችን ለሌሎች አርዓያ እንዲሆኑ ማበረታታት እና ዕውቅና መስጠት አቶ ፍሬሰላም ያነሱት ሌላው ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው። ለአብነትም በዚህ ዓመት ለ810 አካል ጉዳተኞች ዕውቅና ለመስጠት መታቀዱን ነው ያነሱት።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን ዘርዝረዋል፤ አሁንም በኅብረተሰቡ ዘንድ አካል ጉዳተኝነትን እንደ ርግማን ወይም ኃጢአት መቁጠር እና ልጆችን ደብቆ ማሳደግ አሁንም ያልተሻገሩት ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል። የመሠረተ ልማቶች (መንገዶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ የትራፊክ መብራቶች፣ ህንፃዎች) እና የአገልግሎት መስጫዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆን፣ የሚሠሩትም “ራምፖች” (Ramps) ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆን አቶ ፍሬሰላም ያነሷቸው ፈተናዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ሕጎች ቢኖሩም፣ ወደ ተግባር የመቀየር ሰፊ ክፍተት አለ። በተለይ ከትምህርት ጋር በተያያዘ በርካታ ክፍተቶች ይታያሉ። የልዩ ፍላጎት ትምህርት ባለሙያዎች እጥረት፣ የግብዓት ችግር እና አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች አካታች አለመሆን ይጠቀሳሉ።

በአማራ ክልል አራት ሚሊዮን የሚጠጋ አካል ጉዳተኛ እንዳለ ያመላከቱት ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ውስጥ 98 በመቶ የሚሆነው  ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ገደማ ደግሞ ዛሬም በችግር ውስጥ የሚገኝ ነው። የተለያዩ ድጋፎችም (ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማሕበራዊ፣ ስነ ልቦና) ይፈልጋሉ።

በተሰጠው ትኩረትም አሁን ላይ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የሁሉም ማኅበረሰብ ጉዳይ እና አጀንዳ እንዲሆን መደረጉን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ልመና እና የመርዳት ብቻ አድርጎ የማሰብ እንደነበር ያነሱት አቶ ፍሬሰላም በተፈጠረው ግንዛቤ “የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መብት ስለመሆኑ ማኅበረሰቡ መረዳት የጀመረበት፣ አካል ጉዳተኞችም ራሱ መብታቸውን መጠየቅ የጀመሩበት ነው” ብለዋል።

አቶ ፍሬሰላም በተለይ መንግሥት ቢያከናውናቸው ያሏቸውን ሐሳችም አንስተዋል፤ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እና የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊ መብቶች የሚያስከብሩ፣ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ፣ የአካል ጉዳተኞችን ነጻነት እና ውክልናቸውን የሚያረጋግጡ ሕጎችን ማውጣት፣ መተግበር እና ማስፈጸም ደግሞ ያነሷቸው ሐሳቦች ናቸው።

ሥራዎች አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ እንዲሆኑ፣ በበጀት ጭምር በመደገፍ መንግሥት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል። በሕግ አውጪ፣ በሕግ ተርጓሚ እና በሕግ ፈጻሚ አካላት ላይም አካል ጉዳተኞች ራሳቸው እንዲሳተፉ ዕድሉን መስጠት እና ማመቻቸት ሐሳቦችንም አለበት ነው ያሉት። ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ፈጻሚም እንዲሆኑ ዕድሉን መስጠት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ደግሞ  ከጊዜያዊ ድጋፍ ይልቅ አካል ጉዳተኞች በዘላቂነት ራሳቸውን የሚችሉበትን የሙያ ስልጠና እና የሥራ ዕድል ላይ ቢያተኩሩ ሲሉ ነው ያመላከቱት። የሙያ ስልጠና፣ የብድር አገልግሎት፣ ግንዛቤ ፈጠራ እና የወጡ የሕግ ድንጋጌዎችን ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲያግዟቸው ነው የጠየቁት።

መገናኛ ብዙኃን ደግሞ “ስለ አካል ጉዳተኞች ግንዛቤ መፍጠር፣ ውጤታማ የሆኑ አካል ጉዳተኞችን በማቅረብ ሌላው ማኅበረሰብ እንዲማርባቸው፣ ሌላውን አካል ጉዳተኛም እንዲነሳሳ አርዓያነታቸውን  መዘገብ፣ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ማስተዋወቅ እና ግንዛቤ መፍጠር፣ ሕጎችንም ማስተዋወቅ፣ አተገባበራቸውን እና ችግሮችንም ከነመፍትሄው በመዘገብ ማንቃት ይገባል” ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች ያሉባቸው ችግሮች ምንድን ናቸው? መፍትሔዎቹስ? ለውጥ ማምጣት የሚቻለው እንዴት ነው? የሚሉትን ደግሞ ምሁራን ጥናት በማድረግ ምክረ ሐሳብ መስጠት እንዳለባቸው ጠይቀዋል።

ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አካባቢን መፍጠር፣ ማበረታታት፣ ራሳቸውን እንዲችሉ ማገዝ እንዲሁም ወደ አደባባይ እና ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ማድረግ ደግሞ ከማኅበረሰቡ የሚጠበቁ ተግባራት ስለመሆናቸው አንስተዋል።

በተመሳሳይ አካል ጉዳተኛው ራሱ “እኔ አካል ጉዳተኛ ነኝ፤ ነገር ግን የአካል ጉዳቴ ከምንም አይገድበኝም፤ መሥራት እችላለሁ ብሎ ማመን ይገባዋል” ብለዋል።

አደረጃጀቶችን በማጠናከር መብታቸውን መጠየቅ እና በተፈጠሩ ዕድሎች (ትምህርት እና ስልጠና) በመጠቀም ራሳቸውን ብቁ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል። በዚህም ዕድሉን ያላገኙ አካል ጉዳተኞች ዕድሉን እንዲያገኙ ያስችላል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here