መውጣት እና መውረድ

0
180

ዝና እንደ እሳት ነው፤ ሕይወት ያሞቃል ወይም ያቀዘቅዛል። በዓለም ላይ የምናውቃቸው ብዙ ታዋቂ ሰዎች የወደቁት ከችሎታ ማነስ የተነሳ ሳይሆን ስም የሚባለውን ከባድ የቢዝነስ ተቋም በብቃት መምራት ሲሳናቸው ነው።  ዝነኞች በብዙ ምክንያቶች ቢወድቁም እንኳን ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ።

የመጀመሪያው የፋይናንስ መሃይምነት እና የሚያደንቋቸውን ሰዎች ብቻ መስማት ነው። ታዋቂዎች ለውድቀት የሚዳረጉበት ዋነኛው ምክንያት በዙሪያቸው እውነትን የሚነግሯቸውን ባለሙያዎች አባርረው፣ ለጥቅም ያደሩ  ሰዎችን መሰብሰባቸው ነው።

እ.አ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሂፕ ሆፕ ንጉሥ የነበረው ሀመር፣ 33 ሚሊዮን ዶላር ሀብት ነበረው። ሀመር ገንዘቡን እንደማያልቅ ይቆጥር ነበር። ከ200 በላይ የሆኑ የሰፈር ጓደኞቹን እና ዘመዶቹን ቀጥሮ በወር ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ደመወዝ ይከፍል ነበር። ይህ አያዋጣህም የሚለው ሰው ስላልነበረ፤ በ1996 በ13 ሚሊዮን ዶላር እዳ ተዘፍቆ የኪሳራ አዋጅ አወጀ።

ታዋቂው ተዋናይ ኒኮላስ ኬጅ  በሆሊውድ ውስጥ 150 ሚሊዮን ዶላር ያካበት ሰው ነበር። ገንዘቡን ያዋለበት ነገር አስቂኝ ነው። ሁለት ደሴቶች፣ 15 መኖሪያ ቤቶች፣ እና 276 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የዳይኖሰር ቅሪት (ራስ ቅል) ገዛ። እውነትን የሚነግረው የፋይናንስ አማካሪ ባለመኖሩ፤ በመጨረሻ ለግብር ባለስልጣን (IRS) ስድስት ሚሊዮን ዶላር መክፈል እስኪያቅተው ድረስ ደቀቀ።

ዝነኞች የሚወድቁበት ሁለተኛው ምክንያት ትዕቢት እና ከህግ በላይ ነኝ የሚል ስሜት ነው። አንዳንድ ታዋቂዎች ችሎታቸው ከማንኛውም ህግ እና ስነ-ምግባር በላይ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህ ትዕቢት ከንግድ አጋሮቻቸው ጋር ያጋጫቸዋል። ድምጻዊ ካንዬ ዌስት ከሙዚቃ እና የፋሽን ንጉሥ ከአዲዳስ ጋር በነበረው የ “Yeezy” ብራንድ አማካኝነት ቢሊየነር ነበር።

እ.ኤ.አ በ2022 የአይሁድን ህዝብ የሚጠላ ዘረኛ ንግግር  ተናገረ። የባሰ ትዕቢት ደግሞ “ጸረ-አይሁድ ንግግር መናገር እችላለሁ፤ አዲዳስ ግን አያባርረኝም” አለ።

አዲዳስ ወዲያውኑ ውሉን አቋረጠ። ፎርብስ እንደዘገበው የካንዬ ሀብት በአንድ ሌሊት ከ 2 ቢሊዮን ዶላር ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር ወረደ። ትዕቢቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር አሳጣው።

የማህበራዊ ሚዲያ ጥንቃቄ ጉድለት ሦስተኛው የዚህ ዘመን ዝነኞችን የሚጥላቸው ችግር ሆኗል። በአሁኑ ዘመን አንድ ታዋቂ ሰው ስልኩ ላይ በሚጽፈው ነገር የ30 ዓመት ዝናውን በ30 ሰከንድ ሊያጠፋ ይችላል። ሮዛን ባር ጥሩ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ነበረች።

እ.አአ በ2018 የእርሷ ቲቪ ሾው በአሜሪካ ቁጥር አንድ ነበር። በአንድ ክፍል ፕሮግራም ብቻ 250,000 ዶላር ታገኝ ነበር።  ሌሊት ላይ በትዊተር ገጿ የቀድሞ የኦባማን አማካሪ በዘረኝነት ዘለፈች። በሰዓታት ውስጥ ሾውዋ ተሰረዘ። በሚቀጥለው ዓመት ልታገኝ የነበረውን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እና ቀሪ የህይወት ዝናዋን አጣች።

ማይክ ታይሰን እና ማይክል ጃክሰንን ጨምሮ ዓለም ያደነቃቸው ታዋቂ ሰዎች ለውድቀት የተዳረጉበት መንገድ ለሁሉም ሰው ትልቅ ትምህርት አለው። የእነዚህ ዝነኞች ችግር ገንዘብ ማጣት ሳይሆን ገንዘብንና ህይወትን መምራት አለመቻል ነበር።

በቦክስ ታሪክ “ብርቱ” እየተባለ የሚጠራው  ማይክ ታይሰን፤ በስራ ዘመኑ ከ 400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሰብስቦ ነበር። ነገር ግን በ2003 እ.ኤ.አ 23 ሚሊዮን ዶላር እዳ እንዳለበት በማሳወቅ የኪሳራ አዋጅ አወጀ።

የታይሰን ትልቁ ስህተት ዶን ኪንግ የተባለውን አጭበርባሪ ፕሮሞተር ማመኑ ነበር። ዶን ኪንግ የታይሰንን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ይወስድ እንደነበር በኋላ ተረጋግጧል። ታይሰን የፋይናንስ እውቀት ስላልነበረው የፈረመባቸውን ውሎች አያውቃቸውም ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ትርጉም የለሽ ወጪ ያወጣ ነበር። ታይሰን ገንዘብን እንደ ወረቀት ነበር የሚቆጥረው። ቤንጋል የተባሉ ነብሮችን በቤት ውስጥ ለማሳደግ፣ ወርቅ የተለበጡ የመታጠቢያ ገንዳዎችን ለመግዛት እና ለጓደኞቹ ውድ መኪናዎችን በስጦታ ለመስጠት ያወጣው ገንዘብ ወሰን አልነበረውም።

ከተዋናይት ሮቢን ጊቨንስ ጋር ያደረገው ፍቺ እና የደረሰበት የክስ ሂደት የሀብቱን ግማሽ አሟጠጠው። በተመሳሳይ የማይክል ጃክሰን የቅንጦት እና የብድር ወጥመድ ሕይወቱን አቃውሶታል። የፖፕ ንጉሱ ማይክል ጃክሰን በዓለም ላይ በጣም ታዋቂ እና ሀብታም ከነበሩት አንዱ ነው። እሱ ከራሱ ሙዚቃ በተጨማሪ የ”Beatles” ዘፈኖችን መብት (Catalog) በመግዛቱ በየዓመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኝ ነበር። ነገር ግን ሲሞት ከ 400 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ እዳ እንደነበረበት ይነገራል።

ከገቢ በላይ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ነበረው። ማይክል የሚኖርበት “Neverland” የተሰኘው ግዙፍ ርስት (አካባቢ) የራሱ መካነ እንስሳት እና የመዝናኛ ፓርክ ነበረው። ይህንን ቤት ለመጠገን እና ለማስተዳደር ብቻ በዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር ያወጣ ነበር።

በህፃናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ክስ ሲገጥመው ራሱን ለመከላከል በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለጠበቃዎች ከፍሏል። በዚህም የመጥፎ ብድሮች አመል ነበረበት። ማይክል በእጁ የነበረው ጥሬ ገንዘብ ሲያልቅ፤ የሙዚቃ መብቶቹን (Music Catalog) ማስያዣ እያደረገ ከፍተኛ ወለድ ያላቸውን ብድሮች ይወስድ ነበር። ወለዱ እየተጠራቀመ ዋናውን ገንዘብ በላው።

የ”Pirates of the Caribbean” ፊልም ኮከብ የሆነው ጆኒ ዴፕ 650 ሚሊዮን ዶላር እንዳካበተ ይነገራል። ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በፊት ለኪሳራ ተቃረበ። ቁጥጥር የሌለው ወጪ ነበረበት። በፍርድ ቤት በተገለጸ መረጃ መሰረት ጆኒ ዴፕ በወር ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያደርግ ነበር። ለወይን ጠጅ  ብቻ በወር 30,000 ዶላር ያወጣ እንደነበር ተሰምቷል።

በመጨረሻም አስተዳዳሪዎችን መክሰስ ጀመረ። እሱ ማኔጀሮቹ ገንዘቤን ሰረቁ ሲል፤ ማኔጀሮቹ ደግሞ “እኛ አስጠንቅቀንህ ነበር፤ አንተ ግን ገንዘብ ማባከን ማቆም አቃተህ” ብለው ወቅሰውታል።

የድምጻዊት ዊትኒ ሂውስተን  ሱስ እና መጥፎ ግንኙነት ታሪክ ለብዙዎች አስተማሪ ነበር። ዊትኒ በድምፅ ብቃትዋ ወደር አልነበራትም። ነገር ግን ህይወቷ የተበላሸው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በግል ህይወት ቀውስ ነው።

ኮኬይን እና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን መጠቀም ስትጀምር ድምፅዋ ተጎዳ፤ ኮንሰርቶችን መሰረዝ ጀመረች። ይህ የገቢ ምንጭዋን አደረቀው። ከባለቤቷ ቦቢ ብራውን ጋር የነበራት ሁከት የሞላበት ትዳር ለስነ-ልቦና ቀውስ እና ለተጨማሪ የዕፅ ሱስ ዳረጋት። በሞተችበት ጊዜ የነበራት ሀብት በጣም ተመናምኖ ነበር።

ዝና ብርጭቆ ነው። በአግባቡ ካልተያዘ፤ በትንሽ ስሕተት እንክት ብሎ ሊሰበር ይችላል።

እውነተኛ አማካሪዎችን መቅጠር ዝነኞችን ከነስማቸው የጠበቃቸው ጥበብ ነው። “አማካሪ የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግስ” እንደሚባለው ጥሩ አማካሪ የሌላቸው ዝነኞች በስማቸው አይቀጥሉም፤ ቶሎ ይሰበራሉ፤ ቶሎ ይደምቃሉ፤ ቶሎ ይጠፋሉ። የገንዘብ፣ የህግ፣ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ዝነኞችን ይጠብቋቸዋል።

የማህበራዊ ሚዲያ ፍሬን ለዝነኞች መጠበቂያቸው ነው።  ከመጻፋቸው በፊት ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው። ብዙ ታዋቂዎች ስልክ የሚያቀብላቸው ሰው በመቅጠር ራሳቸውን ከስሜታዊ ልጥፎች ያድናሉ። የግል ስሜታቸው የህዝብ እይታቸውን እንዳያበላሸው ይጠብቃቸዋል።

ዝና ቋሚ አይደለም። ዛሬ የሚያገኙትን ገንዘብ ነገ ዋጋቸው በሚጨምር ነገሮች (መሬት፣ ቤት፣ አክሲዮን) እንጂ ዋጋቸው ለሚቀንስ ነገሮች (ውድ መኪና፣ ልብስ፣ ፓርቲ) ማዋል ተገቢ አይደለም።

ወደ ዝና ማማ መውጣት ቀላል ነው፤ እዛ ላይ መቆየት ግን ጥበብ ይጠይቃል። ታዋቂነት መብት ሳይሆን በህዝብ የተሰጠ ኃላፊነት ነው። ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ ያልያዘ ሰው፣ ልክ እንደ ካንዬ ዌስት ወይም ኤምሲ ሀመር፣ መጨረሻው የቁልቁለት መንገድ ይሆናል።

 

ማረፈያ

ትህትና ለሞላው ውብ ልብ፤ ለሰውነት ክብር አዋቂ

ለባለ ሚዛን ጭንቅላት፤ ለአስተዋይ ብርሀን ሠናቂ

ዝና አንጡራ ጸጋ ነው፤ እድሜ ቀጥል ቀን ቀን አድማቂ

ላልተገረዘ ልቦና፤ ለማይታወሰው ትናንት

ለድድር ጥሬ ህሊና፤ ትዕቢት ቤቱን ለሠራበት

ዝና ዘነዘና ነው፤ ራሱን የሚገድልበት፡፡

ከቴዎድሮስ ፀጋዬ ነፍሰጡር ስንኞች የግጥም መጽሐፍ የተወሰደ፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here