በቅኝ ግዛት ያላጣነውን የባሕር በር ዛሬ እንዴት?

0
86

በቅኝ ግዛት ያላጣነውን የባሕር በር ዛሬ እንዴት?

ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ፒ ኤች ዲ ዲግሪያቸው ሕግ ላይ ያተኮረ የትምህርት ዝግጅት አላቸው። ሦስተኛ ዲግሪያቸው ደግሞ ዓለማም አቀፍ ሕግ ላይ ነው። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም የሕግ መምህር ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል። በክልሉ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ሠርተዋል። የተለያዩ የምርምር ስራዎችን አበርክተዋል፡- የአማራ ክልል የሕግ እና የፍትህ ኢንስቲትዪት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደሴ ጥላሁን፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ቅቡልነት ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር እንዴት ይታያል? የሚለውን እና ሌሎችን ነጥች በማንሳት ከአሚኮ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርባለን።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምን ያህል ተቀባይነት አለው?

ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ኢትዮጵያ በሴራ ፖለቲካ ምክንያት ከባህር በር እንድትገለል ከተደረገች ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሀገራቸውን የሚወዱ የዘርፉ ሙሁራን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያየ መንገድ ጥያቄውን ሲያነሱ እንደነበር ይታወቃል። ነገር ግን በመንግሥት ደረጃ እንዳይነሳ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ይከላከል የነበረ የፖለቲካ ስርዓት በመሆኑ የሕዝብ ውይይት ሳይደረግበት ቆይቷል። በእውነቱ ይህ ታሪካዊ ስህተት ነው። በዚያ ደረጃ እንዲህ አይነት የብሔራዊ ጥቅም ትኩረት አግኝቶ እንዳይነሳ ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ አልነበረም። እናም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በዚህ ስርዓት ውስጥ ያለፍን ሰዎች አሁን ወደ ትክክለኛው መስመር ስንመጣ ይህንን ጉዳይ ሙያዊ በሆነ መንገድ በመተንተን ማህበረሰቡ እንዲገነዘበው በማድረግ እና በዓለም የፍትህ አደባባይ የኢትዮጵያን የባህር በር የመጠቀም መብት ተሰሚነት እንዲያገኝ ማድረግ በጣም ተገቢ ነው ብየ አስባለሁ።

ሁለተኛ አንባቢዎቻችን አያይዘውም ማየት ያለባቸው ነገር እንደሚታወቀው አሁን ላይ በሀገራችን በሕዝባችን የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች አሉ። እውነት ነው መዋቅራዊ ሕዝባዊ ጥያቄዎች አሉ፤ ምላሽ ማግኘት ያለባቸው። ሆኖም ግን የባህር በር ጉዳይም በተመሳሳይ  ከምናነሳቸው ከተለያዩ መዋቅራዊ ጥያቄዎች ባልተናነሰ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ጠንካራ ሀገር እንዲኖረን ከሚሻ ማንኛውም ዜጋ በእኩል የሚነሳ ጉዳይ በመሆኑ ይህን ጉዳይ ማንሳት ተገቢ ነው የሚል መነሻ አለኝ ።

ይህን ብየ በአጠቃላይ የጥያቄው አግባብነት እንዴት ነው የሚታየው? የሚለውን በተመለከተ በጣም ብዙ መሰረታዊ ምክንያቶችን በማንሳት የጥያቄውን አግባብነት በአመክንዮ ማስረዳት ይቻላል። በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ለዘመናት በታሪኳ ለዘመናት እንደ ሀገረ መንግሥት በቆየችባቸው ጊዜያት ሁሉ የቀይ ባህር ቃጣና ባለቤት እና ተዋናይ ሆና የቆየች መሆኗ አንደኛው ምክንያት ነው። ሁለተኛው ከጅኦፖለቲካም አንጻር ይኸው የሴራ ፖለቲካ እንኳ ታክሎበት ከቀይ ባህር ርቃ ያልራቀች ሀገር ናት። ሶስተኛ ከኢኮኖሚ ምክንያቶች አኳያ አሁን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጣም ግዙፍ እየሆነ ነው። የሕዝብ ቁጥሯ በጣም ከፍተኛ ነው። በሴራ ፖለቲካ ምክንያት የባህር በር ባለቤትነት መብቷን በማጣቷ ምክንያት በወደብ ኪራይ የምታወጣው ገንዘብ በየጊዜው በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር መሆኑ፣ እናም ደግሞ አሁን ሴራውን እያሸነፈች መሆኗም አብሮ መታየት መቻል አለበት።

የባህር በሩን ያጣንበት መንገድ ሲወሰድ ኢትዮጵያ ከህግ አንፃር የነበሩትን ዓለማቀፍ የሕግ መብት በሚጥሱ በጣም በርካታ ምክንያቶች የታጣ በመሆኑ በታሪክም፣ በሕግም፣ በጀኦ ፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከዚህ በፊት የነበረውን የመንግሥት ስርዓታዊ ስህተት በማረም አሁን እንደ መንግሥት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ግንባር ቀደም አጀንዳ አድርጎ ማቅረብ በጣም ተገቢነት አለው:: በየትኛውም ረገድ ብታቀርበው ተገቢና የማያሳፍር ነው እላለሁ::

አለማቀፍ የውሃ ሕጎችስ ይህን ጉዳይ እንዴት ይድግፋታል? ከሕጎች አንፃርስ እንዴት ነው ቅቡልነቱ የሚገለፀው?

ከዓለማቀፍ ሕግ አኳያ እዚህ ጋር በጥንቃቄ መታየት መቻል ያለበት የባህር በርን የማግኘት ሉዓላዊ መብት በዓለማቀፍ ሕግ ፊት ሁለት ዓይነት መልክ ያለው ነው:: አንደኛው የባህር በር ባለቤት ሀገሮች በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የሚጠቀሟቸው መብቶች ምንድን ናቸው የሚለውን የሚያይበት ነው:: ሁለተኛው ደግሞ የባሕር በር የሌላቸው ሀገሮች የባህር በር ያላቸውን ሀገሮች ወደብ ተጠቅመው መብቶታቸውን እንዴት ይተገብራሉ ነው:: ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በሁለቱም ነው መታየት መቻል ያለበት:: አንደኛው ቅድም እንዳልኩት ኢትዮጵያ በታሪክ የባህር በር ባለቤት የነበረች ሀገር ናት:: የተለያዩ የዓለም ሕግ ጥሰቶች ተፈፅመውባት እና ሴራ ተጨምሮበት ነው መብቷን ያጣቸው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ስንል ያጣችውን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ እንደገና የማግኘት ፍሬ ሀሳብ ያለው ነው ማለት ነው:: ስለዚህ ይህንን በተመለከተ የኢትዮጵያን መብት ሊያስከብሩ የሚችሉ የሚደግፉ በርካታ ዝርዝር የዓለማቀፍ ሕግ ድንጋጌዎች ያሉ ስለሆነ ከነበረን ታሪክ ጋር በማስተሳሰር ይህንን በዲኘሎማሲያዊ መንገድ ወደ አለም አደባባይ በማቅረብ ይህንን መብት የመጎናፀፍ ነው አንደኛው:: ሁለተኛው በጣም ግዙፍ ሀገር ናት፣ ግዙፍ ኢኮኖሚ አየገነባ ያለ ሀገር ነው። እያደገ የሚሄድ ሀገር ነው:: ስለዚህ የባህር በር ባለቤትነቷን እንኳን ብታስመልስ በእነዚህ ወደቦች ብቻ ተጠቅማ አይደለም ኢኮኖሚዋን ማንቀሳቀስ የምትችለው:: ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ወደቦቹን በጋራ የመጠቀም አካሄድንም በተመሳሳይ ሁኔታ መጠቀም መቻል አለባት ማለት ነው::

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ጉዳይ ከዓለምቀፍ ሕግ አንፃር እንዴት ይታያል ሲባል ጠበብ ባለ መንገድ  የባህር በር የሌላቸው ሀገሮች ይህንን መብት ከመጠቀም አኳያ ማብራሪያ የሚሰጡ አንዳንድ ነገሮች ይታያሉ፤ እንደማስበው ይኼ አንደኛው እይታ ብቻ ነው፤ ይልቁንስ በጣም ትልቁ እይታ ብየ የማስበው እኔ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ጀምሮ በተለይ የኤርትራ ሀገር መሆን ጋር ተከትሎ የተሰሩ ስህተቶች በዝርዝር ስታይ በርካታ የዓለማቀፍ የሕግ ጥሰቶች የተካሄዱባቸው ናቸው:: ክርክር ሊካሄድባቸው የሚገቡ፣ በዚያን ወቅት ውክልና የሌላቸው አካላት የብሔራዊ ጥቅምን የሚያክል ትልቅ ጉዳይ አሳልፈው የሚሰጡ ስህተቶች የተፈፀሙበት ስለሆነ ይህንን እንደገና በዓለማቀፍ ሕግ መሰረት በዓለም አደባባይ ሕግን መሰረት አድርጎ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመሞገት የኢትዮጵያን የባህር በር ጉዳይ ባለቤትነት ማስመለስ ይቻላል ተብሎ ነው የሚታመነው እና ሁለት እይታዎችን ማየት በጣም ጠቃሚ ነው ከሕግ አንፃር::

ከዲፕሎማሲ አንፃር የባህር በር የማግኘት ጥረቷ የዲፕሎማሲ አቅሟን በማሳደግ በኩልስ ምን ያህል ጠቃሚ ነው? የዲኘሎማሲ ሂደቷስ ምን ይመስላል?

ዲኘሎማሲን በተመለከተ ባለፉት 30 ዓመታት ስንከተል የነበረው በጣም የተሳሳተ ሁኔታ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎችም ላይ ሲንፀባረቁ ስለነበረ የወደብን ጉዳይ እንዴት ሲደረግ እንደነበረ በጣም የሚታወቅ ጉዳይ። የባህር በር ባለቤትነቱን በሴራ ነው ያጣችው:: ስለዚህ ዓለማቀፍ ሕግ ይደግፈናል፣ ዓለማቀፍ ማህበረሰቡ ይደግፈናል፤ ይህንን ማስረዳት እንችላለን፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ ይህን ማምጣት ይቻላል ብሎ አጀንዳ ማድረግ በራሱ መሰረታዊ የሆነ የውጭ ግንኙነት ለውጥ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል:: በተለያዩ ትልልቅ መድረኮች ላይም አጀንዳው ከፍ ብሎ የተነሳበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ስለዚህ የሀገራት ምላሽ ምንድን ነው? ዲኘሎማሲው እንዴት ነው ውጤት እያመጣ ያለው? የሚለውን ለመገምገም የሀገራትን ምላሽ መውሰድ ይቻላል::

እንግዲህ በቅኝ ግዛት ጊዜ እንኳን በጣም በሚገርም ሁኔታ በተለይ በ1952 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን ግምት ውስጥ በማስገባት የወሰናቸው ውሳኔዎች በቅኝ ግዛት ዘመን እንኳን ያላጣነውን ነው እኛ በሴራ ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈን የሰጠነው:: ስለዚህ ትልልቅ ሀገሮች አሁን ላይ ለዚህ ጥያቄ ድጋፍ እየሰጡ ነው:: ኢትዮጵያ የባህር በር አያስፈልጋትም የሚል አንድም ሀገር አታይም:: ነገር ግን ይህን ጉዳት እንዴት ነው ማስፈፀም ያለብን ወደሚል ነው እየመጣ ያለው::

ወደብ ያላቸውና ወደብ የሌላቸው ሀገራት ኢኮኖሚያቸው አኩል የሚራመድ አይሆንም:: ለምሳሌ ከዚህ አንፃር ቢዘከሩ ተደጋግመው ቢዘከሩ የምውደው ዶ/ር ያእቆብ ኃ/ማሪያምን ማንሳት ይቻላል:: አሰብ የማን ናት? ብለው በፃፉት መፅሃፍ ላይ ሁኔታውን በዝርዝር አስቀምጠዋል:: እኩል ሁኔታዎች ኑረው ልማትን ብትሰራ ወደብ የሌለው ሀገር ወደብ ካለው ሀገር በ12 ዓመት ወደ ኋላ የሚጎተት መሆኑን በግልፅ አሳይተዋል:: ወደብ አልባነት የውጭ ኢንቨስትመንትን ከ30 እስከ 40 በመቶ እንዲቀንስ ያደርጋል:: ስለዚህ እንደዚህ አይነት ጥቅሞችን የሚያሳጣ ጉዳይ ስለሆነ በሴራ ደግሞ ስታጣው የበለጠ የእግር እሳት ነው የሚሆነው። ስለዚህ ዋና ዋናዎች የዓለማቀፉፍ ሕግ ገዢ ሁኔታዎች ባለቤት ስለሆነች ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ የፍትህ ጥያቄዎች ስታነሳ በቀናነት አይቶ ማስተናገድም አለበት ብየ አስባለሁ::

 

በሕጉ ዘርፍ ያሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ምን አይነት ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ለዚህ ውጤታማነት?

የመጀመሪያው ይህ ዘመን የኢትዮጵያን ሕጋዊ ፍላጎት ለማስጠበቅ ግንባር ቀደም መሆን ካለብን የሕግ ባለሙያዎች፣ የፓለቲካ ሳይንስ ሙሁራን ግንባር ቀደም ሆነው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከታሪክ አንፃር ለማስከበር በሰለጠነ መንገድ ትግል ማድረግ  ያለባቸው ወቅት ነው ብየ አስባለሁ:: ስለዚህ ከዚህ አንፃር የሕግ ባለሙያዎቹ የመጀመሪያው የሚጠበቅባቸው ነገር የእውቀት ማስተላለፍ ስራ ነው። የሚያውቁትን የሚረዱትን አግባብነት ያለውን ነገር ሕዝብ እንዲያውቀውና እንዲረዳው ማድረግ:: በጥናትና ምርምር ማዳበር፤ ልምዶችን መቀመር፣ የተለያዩ ሕትመቶችን ማሳተም፣ እንዲህ አይነት ሕጋዊ ማብራሪያዎችን መስጠት ያስፈልጋል:: ሁለተኛ ከሕዝብ አንፃር ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋለ:: የተደበቀ ነገር ስላልሆነ ከውስጥ መመለስ ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ:: እነዚህን ጊዜ ሳይሰጡ ለዚህ ለምናነሳው ትልቅ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ተጨማሪ አቅም እንዲሆን በፍጥነት መቋጨት ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

መንግሥት አሁን የያዘውን አቋም አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብየ አስባለሁ። ስለዚህ በዓለማቀፍ ሕግ መሰረት በባለቤትነት ልናገኘው የሚገባን የባህር በር ጥያቄ እንደገና ማስመለስ አንድ ነገር ነው። ከዚያ በተጨማሪ የወደብ አማራጮችን ማስፋት በጣም ጠቃሚ ነገር ነው።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here