ብሔራዊ ፓርኩ በማዳጋስካር ደሴት ሰሜናዊ ቀጣና፤ በእሳተ ገሞራ በተፈጠረ ልምላሜን በተላበሰ ሰንሰለታማ ተራራ ላይ ነው የሚገኘው::
ፓርኩ በ1958 እ.አ.አ የተመሰረተ ሲሆን መገኛው ከ850 ሜትር እስከ 1475 ሜትር ከፍታን አካሏል:: አጠቃላይ ስፋቱም 230 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ነው::
የፓርኩን ቀጣና ባካተተው ተራራማ መልካአ ምድር ርጥበት አዘል ጥቅጥቅ ደን፣ ሐይቆች፣ የሚገኙበት ፀጥታ የሰፈነበት ለጐብኚዎች በእግር ለመጓጓዝም የተመቸ ነው::
ቀጣናው የነባር ማላጋሲ ጐሳዎች መኖሪያ ነው:: የሀገሪቱ የፓርኮች ጥበቃ ድርጅትም ከበጐ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ማህበረሰቡ በደን ሀብት ላይ ያለውን ጥገኝነት በሚቀንስ አማራጭ የኑሮ ዘዴን ለማብቃት እየሰራ ነው:: የፓርኩ ዓየር ንብረት ዝቅተኛው 15 ከፍተኛው ደግሞ 27 ዲግሪ ሴልሺየስ ተመዝግቧል::
በፓርኩ 75 የዓዕዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ ከነዚህ ውስጥ 35ቱ ብርቅዬ (እንዴሚክ) -መሆናቸውም ተጠቁሟል:: ከተሳቢ (አምፊቢያንስ) 60 ዝርያዎች፣ ከአጥቢዎች 25 ዝርያዎች መገኛም ነው::
በፓርኩ የሚገኘው ጥቅጥቅ ደን ለጐብኚዎች መስህብ ሆኖ ከሚያስገኘው ገቢ ለባሻገር ማገዶ እና ለመድሃኒት ግብአትነት ያገለግላል::
ብሔራዊ ፓርኩ ለሀገሪቱ ትክ የሌለው ተፈጥሯዊ ቅርስ ምሳሌ ነው:: ለም ለም መልክዓ ምድሩ እንስሳት እና እፅዋቱ፣ ተመራጭ የጐብኚዎች መዳረሻ አድርገውታል::
በቀጣናው የሚገኘውን ስነምህዳር በመጠበቅ ለብዝሃ ህይዎት ሀብቱ መጠለያነቱን ማረጋገጥ፣ ኗሪዎቹን በማሳመን አሁን ካለው ትውልድ ባሻገር ለመጪዎቹ ለማስተላለፍ ጥበቃውን ማጠናከር እንደሚገባም አፅንኦት በመስጠት ነው የድረገፆች ጽሁፍ የተደማደመው::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት (ትራቭለርስ) ኦፍ ማዳጋስካር፣ ኧርዝ ትሪጥ፣ ጂንማን ሰፋሪ ድረገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


