በመጠጥ ውኃ ውስጥ የሚገኝን “አርሰኒክ” የተሰኘ የመርዛማ ብክለት መጠንን መቀነስ የካንሰር እና የልብ ህመም በመሳሰሉ ስር በሰደዱ በሽታዎች የሚደርስ ሞትን 50 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት አስነብቧል::
የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በመረጃ ምንጭነት እንዳስታወቀው በባንግላዲሽ 11 ሺህ በሚደርሱ ለናሙና በተመረጡ ኗሪዎች ላይ ጥናት እና ምርምር ተድርጓል:: በዚሁ ለ20 ዓመታት በተደረገ ክትትል እና የጤና ምርመራም በውኃ ላይ ሰፎ ከሚገኝ “ አርስኒክ” ብክለት የፀዳ ውኃ መገልገል በዚሁ ሳቢያ የሚከሰት ሞትን 50 በመቶ ይቀንሳል::
ተመራማሪዎቹ በተፈጥሮ በተለይም በጉድጓድ ውኃ ውስጥ የሚከሰት የ “አርሰኒክ” ብክለት በዓለማችን በየሀገራት ተስፋፍቶ የጤና ስጋት መፍጠሩን ነው ያረጋገጡት:: ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ተመራማሪው ፌን በመጠጥ ውኃ ውስጥ የሚገኝ የ “አርሰኒክ” ተጋላጭነት መቀነስ ለሞት የመዳረግ አደጋን መቀነሱን በሽንት ናሙናዎች ምርመራ የአርሰኒክ ልኬታን ማረጋገጥ ችለዋል::
በኮሎምቢያ የሜልማን የህዝብ ጤና ትምህርት ቤት ኘሮፌሰር እና ዋና ተመራማሪው ጆሴፍ ግራዚያኖ ከ1998 እ.አ.አ የጀመረው ምርምር ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ግኝቱ አርኪ መሆኑን ነው ያሰፈሩት::
ተመራማሪው “አርሰኒክ” በተፈጥሮ በከርሰ ምድር ውኃ ውስጥ ጣዕም እና ሽታ አልባ ሆኖ እንደሚከማች ጠቁመው ሰዎች ሳያውቁት የተበከለውን ውኃ ጠጥተው ለከፋ የጤና ችግር እንደሚዳረጉ ነው ያሰመሩበት::
በጥናቱ የ “አርሰኒክ” ተጋላጭነታቸውን በቀነሱ እና ለ “አርሰኒክ” ተጋላጭ የሆነ የጉድጓድ ውኃን በተጠቀሙ መካከል በተደረገ የመጨረሻ ውጤት ንፅፅር የሞት መጠን 50 በመቶ መቀነሱን ነው ያረጋገጡት::
በጥናት እና ምርምር ኘሮጀክቱ ባካተታቸው የናሙና ቦታዎች የውኃ ጉድጓዶች የ “አርሰኒክ” ተጋላጭነት ወይም ደህንነታቸው ያልተጠበቀውን እንዲለዩ አድርገዋል፤ በዚህም በርካታ ቤተሰቦች ደህንነታቸው ወደ ተጠበቁ ጉድጓዶች እንዲቀይሩ ማስቻላቸው ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


