ብሔራዊ ፓርኩ ከዋና መዲናዋ አዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ 565 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል፣ ቦረና ዞን ነው የሚገኘው:: የፓርኩ ስፋት 2500 ሜትር ሲሆን መልካ ምድራዊ አቀማመጡም ዝቅተኛው 1400 ሜትር፣ ከፍተኛው 2000 ሜትር ተለክቷል4 አማካዩም 1700 ሜትር መሆኑን ልብ ይሏል::
የፓርኩ ከባቢ ዓመታዊ ዝናብ መጠን በአማካይ 700 ሚሊ ሜትር ነው:: ከፍ ያለ የዝናብ መጠን የሚጥለው በጥር እና የካቲት ወራት መሆኑንም ድረ ገፆች አስነብበዋል::
የዓየር ንብረቱ ወይና ደጋ የሚባል ነው፤ ቀዝቃዛው 13 ዲግሪ ሴልሺየስ፣ ሙቀቱ ደግሞ 25 ዲግሪ ሴልሺየስ ተለክቷል፤ አማካይ 19 መሆኑ ነው:: በጣም ሞቃቱ የአየር ንብረትም በጥር እና የካቲት ወራት ተመዝግቧል::
የፓርኩ መገኛ የአፈር አይነቱ ቀይ ሲሆን ቀጣናው በለበሰው የግጦሽ ሳር መካከል የግራር ዛፍ በርከት ብሎ ይታያል:: ቀደም ባሉት ዓመታት በየኮረብታው ከፍተኛ ቦታዎች “ጃኒፐርስ ኘሮሴራ” ወይም የጥድ ዛፍ ነበር የሚታይባቸው:: ዛሬ ላይ ግን የጥድ ዛፍ ሳይሆን ግራር እና ሳር ለበስ ሆኗል::
በፓርኩ 210 የዓዕዋፍ ዝርያዎች መኖራቸውም ተመዝግቧል፤ ከነዚህ ውስጥ ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡት “ቡሽ ክሮው” እና “ኃይት ቴይልድ ስፓሮው” መገኘታቸው ተረጋግጧል:: ከሁሉም በበለጠ ባለግርማ ሞገሷ ሰጐን፣ የሶሟሌ “ ስፓሮ” እንደሚገኙ ነው የተጠቀሰው:: በአካል ግዝፈት ካላቸው የዱር አራዊት ቆርኬ “ስዋይን ኸርት ቢስት”፣ የሜዳ አህያ እና የሜዳ ፍየል በፓርኩ ተጠልለው ይገኛሉ::
ፓርኩ ለጐብኚዎች ዓመቱን ሙሉ ክፍት ቢሆንም በአየር ንብረቱ ምቹነት የዝናብ መጠኑ አነስተኛ የሆነበት ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉት ወራት ተመራጭ ናቸው:: በዚህ ወቅት የዕፅዋት ሽፋኑም ጥቅጥቅ ባለመሆኑ ጐብኚዎች እንደፈለጉ ለመመልከት ወደ አካባቢው ይተማሉ::
የፓርኩ ጐብኚዎች ማረፈያ፣ ምግብ እና መጠጥ የሚያገኙባቸው እንደየአቅማቸው እና ፍላጐታቸው ቅንጡ ማረፊያ ሎጂዎችም ተዘጋጅተዋል:: ከዚህ ባሻገር በፓርኩ ክልል ውስጥ በተመቸ ቦታ ድንኳን ተክለው በቅርበት የዱር አራዊት ለመመልከት፣ የአፅዋፉን ዝማሬ ማድመጥም ያስችላል::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ኢትዮጵያን ዋይልድ ላይፍ፣ ባሌ ማውንቴንስ ትራኪንግ እና ሎንሊ ኘላኔት ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


