ድሮ ልበለው:: ከ15 ዓመታት በፊት አስተማሪዎቻችን የነገ ሀገር ተረካቢዎች ናችሁ ብለው ሲመክሩን እናሾፍ ነበር:: የሚደርስም እውነትም አይመስለንም ነበር:: ዛሬ ሀገር የተረከብሁ ሰው መሆኔ ገባኝ። በዚህች አገር ውስጥ አሻራ ያለኝ ሰው መሆኔን አወቅሁ:: ማናችንም ዛሬ ያለንበት ሕይወት የአስተዳደጋችን ውጤት ነው። ድካም እና ጥንካሬ፣ ክፋት እና ደግነት ያለፍንበት መንገድ እንዴት እንደ ሰራን የሚያሳይ አሻራ ነው። ዛሬ ስለአስተዳደግ እናወራለን::
ልጆች እንደ ባዶ ወረቀት ናቸው:: ወላጆች እና አካባቢ ደግሞ በላያቸው ላይ የሚጽፉ ጸሐፊዎች ናቸው:: የልጆች አስተዳደግ አንድን ልጅ በሥጋዊ፣ በስሜታዊ፣ በህሊናዊ እና በማህበራዊ ህይወቱ የመቅረጽ ሂደት ነው:: ይህ ሂደት በልጁ የወደፊት ህይወት ላይ ጥልቅ የሆነ ጥቅም ወይም ጉዳት አለው::
ብዙ ጊዜ ስኬታማ ሰዎች የተመቻቸ የልጅነት ህይወት የነበራቸው ናቸው ብለን እናስብ ይሆናል። ነገር ግን ታሪክ የሚያሳየው ሁለት አይነት መንገዶችን ነው:: አንዳንዶቹ ድጋፍ በበዛበት ቤተሰብ ሲያድጉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከከባድ ችግር ውስጥ ወጥተዋል::
አምፖልን የፈጠረው ቶማስ ኤዲሰን በልጅነቱ ትምህርት ቤት ሲገባ አስተማሪዎቹ “ጭንቅላቱ አይሰራም፣ መማር አይችልም” ብለው አባረሩት:: እናቱ ግን ይህንን ደብዳቤ ደብቃ “ልጅሽ ልዩ ተሰጥኦ ስላለው ትምህርት ቤቱ አይመጥነውም። ቤት ውስጥ አስተምሪው” ተባልሁ ብላ ነገረችው:: ኤዲሰን የዓለም ታላቅ የፈጠራ ሰው የሆነው በእናቱ እምነት እና የቤት ውስጥ ትምህርት ነው። እናቱ ጠንካራ በመሆኗ ዓለምን ብርሀን ያሳዬ ጀግና ሆነ:: ልጆች በእነሱ የሚያምን እና የሚደግፋቸው አንድ ሰው ካላቸው ዓለምን መቀየር ይችላሉ::
ኦፕራ ዊንፍሬይ የዓለም ሚዲያ ንግሥት ተብላ ትጠራለች:: እጅግ ደሃ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ እና በከባድ ጥቃት ውስጥ ነው ያደገችው:: ነገር ግን አባቷ ጋር በሄደችበት ወቅት የነበረው ጥብቅ ስርዓት እና መጽሐፍ የማንበብ ግዴታ ህይወቷን ቀየረው፤ ችግሩ እንድትጠነክር አደረጋት::
አስቸጋሪ የልጅነት ጊዜ የልጆችን የመቋቋም አቅም ሊገነባ ይችላል:: ይህ ግን የሚሆነው ትክክለኛ አቅጣጫ የሚያሳይ ሰው ሲኖር ነው:: ኦፕራ ከጉዳት ወደ ጥንካሬ አደገች::
ባለጸጋው ኢሎን መስክ በልጅነቱ መጽሐፍትን በማንበብ የተጠመደ ነበር:: ወላጆቹ ለቴክኖሎጂ እና ለንባብ የነበረውን ፍላጎት አልገደቡበትም:: ምንም እንኳን ቤተሰባዊ ህይወቱ ውጣ ውረድ የነበረበት ቢሆንም ነፃነቱ እና የማወቅ ጉጉቱ ዓለምን የሚቀይር ሰው አደረገው:: ዛሬ የዓለም የሀብት እና ፈጠራ ቁንጮ ለመሆን የወላጆቹ ፍላጎቱን መደገፍ እና መርዳት ትልቅ አሻራ አሳርፏል::
የቢል ጌትስ ወላጆች ሀብታም ነበሩ:: ነገር ግን ዋናው ስኬታቸው ገንዘብ መስጠታቸው ሳይሆን ገና በልጅነቱ ለኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እንዲጋለጥ ማድረጋቸው እና የውድድር መንፈስን ማስተማራቸው የኋላ ኋላ ማይክሮ ሶፍት ኩባንያን እንዲመሰርት አድርጎታል:: ከዓለም ባለጸጋዎች አንዱ ሆነ።
የልጆች አስተዳደግ ለስኬት ወሳኝ መሰረት ነው:: ነገር ግን ስኬት የሚመጣው እንከን የለሽ ከሚመስል የልጅነት ህይወት ብቻ ሳይሆን እችላለሁ የሚል አመለካከት ከመፍጠርም ነው:: ባህሪ ይዘነው የምንወለድ አይደለም፤ የምንማረው እንጂ::
ሃሪ ሃሪሰን “ፋዘር ቱ ሰን” በሚለው መጽሐፉ “አንድን ወንድ ልጅ ማሳደግ ማለት ቀጥሎ ለሚመጣው ትውልድ ጥሩ ባል፣ ጥሩ አባት እና ጥሩ ዜጋ ማዘጋጀት ነው” በማለት የወላጅን ሚና በሚገባ አስቀምጧል:: አባት ለልጁ የሚሰጠው ጊዜ እና ምክር ከገንዘብ በላይ ዋጋ እንዳለው ያስገነዝባል::
የስነ-ልቦና ባለሙያዋ ዳያና ባውምሪንድ እና በሌሎች ዘመናዊ ተመራማሪዎች መሠረት የአስተዳደግ ዘይቤዎች በልጆች ማንነት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንዳላቸው ተረጋግጧል:: በርካታ ጥናትና ምርምሮችም በዚህ ዘርፍ ላይ ተደርገዋል::
የዘርፉ ምሁራን በአጠቃላይ አራት ዋና ዋና የአስተዳደግ ዘይቤዎች እንዳሉ አስቀምጠዋል። እያንዳንዱም ዘይቤ የራሱ የሆነ ውጤት አለው::
ዴሞክራሲያዊ አስተዳደግ
ይህ በጣም ተመራጭ የሚባለው የአስተዳደግ ዘይቤ ነው:: ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅርን ይሰጣሉ:: የልጆቻቸውን ስሜት ያዳምጣሉ::
ነገር ግን ግልጽ የሆነ ህግ እና ገደብ ያስቀምጣሉ። በዚህ ያደጉ ልጆች በራስ የመተማመን አቅማቸው ከፍ ያለ ነው። ማህበራዊ ግንኙነታቸው የተሳካ ነው። እንዲሁም ለችግሮች የመፍትሄ አቅማቸው የዳበረ ነው:: ደስተኛ፣ ራሳቸውን የቻሉ እና ውጤታማ ዜጎች ይሆናሉ።
አምባገነን አስተዳደግ
“እኔ ያልኩትን ብቻ ስሙ” በሚል መርህ የሚመራ ነው። ፍቅር እና ውይይት በዛ ያለበት ሊሆን ይችላል። ቅጣት እና ጥብቅ ቁጥጥር ይበዛበታል። ልጆች ታዛዥ ሊሆኑ ይችላሉ ነገር ግን ደስተኞች አይደሉም። በራስ መተማመን ይጎድላቸዋል። ውሳኔ ለመወሰን ይቸገራሉ። እናም አንዳንዴም አመፀኛ ይሆናሉ። ቅጣትን ከመፍራት ለውሸት ቅርብ ሊሆኑ ይችላሉ::
ለዘብተኛ አስተዳደግ
ወላጆች እንደ ጓደኛ እንጂ እንደ ወላጅ አይሆኑም። ልጆች የፈለጉትን እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸዋል። መተዳደሪያ ህግ የለም። ልጆች ስነስርዓት አይኖራቸውም። የሌሎችን መብት አያከብሩም:: ትምህርት ቤት ላይ ውጤታቸው ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል። “ሁሉም ነገር ይገባኛል” የሚል ስሜት (ኢንታይትልመንት) ይይዛቸዋል::
ቸልተኛ አስተዳደግ
ወላጆች የልጆቹን መሰረታዊ ፍላጎት (ምግብና መጠለያ) ከመሙላት ውጪ ስሜታዊ ቅርበት የላቸውም። ይህ እጅግ ጎጂው አስተዳደግ ነው። ልጆች ብቸኝነት ይሰማቸዋል። ለድብርት ይጋለጣሉ። እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ቦታ እንደሌላቸው ያስባሉ።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጤናማ አስተዳደግ የሚከተሉትን ሁለንተናዊ ጥቅሞች ይሰጣል:: የመጀመሪያው የአእምሮ እድገት ነው። ወላጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚያናግሯቸው እና የሚያጫውቷቸው ልጆች የአይ.ኪው (IQ) መጠናቸው ከፍ ያለ ነው::
ሁልተኛው የስሜት ብልህነት ነው። ስሜታቸው የተደመጠላቸው ልጆች የራሳቸውን እና የሌሎችን ስሜት የመረዳት አቅም ይኖራቸዋል። ይህ ለትዳር እና ለስራ ዓለም ስኬት ወሳኝ ሚና ይጫዎታል::
ሦስተኛው ፈተናዎችን የመቋቋም አቅም ነው። ልጆች ሲወድቁ “አይዞህ” እየተባሉ ከተደገፉ፣ በህይወት ፈተናዎች ፊት አይሰበሩም። ወድቀው የሚነሱ ይሆናሉ:: መውደቅ እንዳለ ሁሉ መነሳትም የሚቻል መሆኑን ያምናሉ::
ሁሉም ሰው አሁን ያለበት ሕይወት ትናንት የመጣበት ድምር ውጤት ነው። የዛሬ ባህሪ ከተጓዝንበት መስመር የመጣ ነው። የተዘራብንን አብቅለናል። ፍርሀትን ስንመለከት እና ስንሰማ ካደግን ያንኑ እንሆናለን። ጀግንነትን ካየን እና ከሰማን ያንኑ እንኖረዋለን:: ወላጆች ልጆችን ሲያሳድጉ ሚዛናዊ መሆን ይኖርባቸዋል። ፍቅርን ከስርዓት ጋር ማዋሀድ ተገቢ ነው። ልጆች እንዲደመጡ ይፈልጋሉ። ልጆች የሚሰሙትን ሳይሆን የሚያዩትን ነው የሚሆኑት። ለዚህም ዓርዓያነት ከወላጆች ይጠበቃል:: ልጆች ውድቀትን መማር አለባቸው:: ወላጆች ልጆች ሲወድቁ እንዲነሱ ማገዝ እንጂ ከመውደቅ መከልከል የለባቸውም። ምክንያቱም የነገው ዓለም ፈተና የበዛበት ነውና።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


