አፋር

0
22

“የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አይደለም የአፋር ሰው የአፋር ግመል ታውቀዋለች…!” ሲባል ሁልጊዜ እንሰማለን። አፋር የኢትዮጵያ ጥንታዊ አካል ስለሆነ እና ሕዝቧ ለሀገር ፍቅር ያላቸውን ፅኑ እምነት ለማሳየት አዘውትሮ የሚነገር አባባል ነው። ግመል በአፋሮች ባህል እና ማህበረ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ስፍራ ያላት መገለጫቸውም ናት። በክልሉ አርማ ውስጥ ያለው የግመል ምልክት ለዚህ ማሳያ ይሆናል።

አፋር በሰሜናዊ ምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል የሚገኝ ክልል ነው። በታሪክ ውስጥ በዓለም ውዱ የኦፊር ወርቅ መገኛ ስፍራ፣ የአህጉረ አፍሪካ ስም መነሻ መሆኑንም የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ። ኤርትራ በሰሜን፣ ጅቡቲ በሰሜን ምስራቅ ያዋስኑታል። ከሀገር ውስጥ ከትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች ጋር ይጎራበታል።

የአፋር ትሪያንግል ሰሜናዊ ክፍሉ የዴናክል ስርጉድ ስፍራ ሲሆን የታላቁ ስምጥ ሸለቆ መገኛ አካል ነው፤  በክልሉ ሰሜን አካባቢ ይገኛል። በኢትዮጵያ ዝቅተኛው ስፍራ እና ከአፍሪካም አንዱ ዝቅታማ ስፍራ ነው።  የክልሉ ደቡባዊ ክፍል ደግሞ የአዋሽ ወንዝ ሸለቆ ወንዝ ይገኛል። ሌላው ታዋቂ ስፍራ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ነው።

የዴናክል ስርጉድ (ዲፕረሽን)፣ ንቁው የኤርታሌ እሳተ ገሞራ፣ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ ያንጉዲ ራሳ ብሔራዊ ፓርክ፣ የሃዳር እና አራሚስ አካባቢዎች የአፋር ክልል ዋና ዋናዎቹ የቱሪስት መስህብ አካባቢዎች ናቸው። ሙቅ ፍልውሃዎች፣ የአፋር ባህል እና ባህላዊ ጨዋታዎችም ሌላ የቱሪስት መስህብ ናቸው።

 

የደናክል ስርጉደት

በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ተመስርቶ የአፋር ትሪያንግልን እናገኛለን። የአፋር ትሪያንግል ሰዎች ከሰፈሩበት ራቅ ብሎ የሚገኝ እና ለመኖሪያ የማይመች ስፍራ ነው። አፋር ትሪያንግል ከከርሰምድር አንፃር ግን አንዱ የሳይንሳዊ ሀብት ነው። ይህ ወና፣ በርሃማ ክልል የዴናክል ዲፕሬሽን መገኛ ነው። ዴናክል ደግሞ የመሬት አካል ከመምሰል ይልቅ የሌላ ዓለም አካል ይመስላል። በዓለም ሞቃታማው ስፍራ ያለው እዚህ ነው፤  በበጋ ወራት የሙቀት መጠኑ እስከ 55 ዲግሪ ሴሊሺየስ ድረስ ከፍ ይላል፡፡

ዴናክል በዳሎል አካባቢ ባለ የእሳተገሞራ ስርጉዶች  መሀል  የሚንተከተክ የላቫ ሀይቅ አለበት፡፡ ሞቃት ፍል ውሃዎች እና ሀይድሮተርማል ኩሬዎች አየሩን የገማ እንቁላል ሽታ ባለው ሳልፈር መርዘውታል። ዳሎል የተባለው እሳተገሞራ በአንፃራዊነት አዲስ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የፈነዳውም በ1918 ዓ.ም  ነው። አጠቃላይ አካባቢው ከባህር ወለል 100 ሜትር በታች ናቸው። ይህ በፕላኔቷ ዝቅተኛው ስፍራ ያስብለዋል። አስገራሚው ነገር ግን ከመርዛማ አካባቢነቱ እና የዝናብ እጥረት እያለበት ለአንዳንድ ነፍሳቶች መኖሪያ ነው።

አርባ በአስር ኪሎሜትር ስፋት ላይ ያለው ይህ የአፍሪካ ክልል በተራሮች እና በከፍታማ አምባ የተዋሰነ ነው። የስረኛው የመሬት ንጣፎች ሲራራቁ የተፈጠረ ስፍራ ነው። ይህ ስፍራም ስርጉድ ስፍራ(ዲፕሬሽን) የተባለ እና ቅርፁን የያዘውም ከአፍሪካ እና እስያ አህጉራት ስር ያሉት ሶስት የመሬት ንጣፎች ከሚሊዮኖች ዓመታት በፊት ከተጋጠሙበት በተለያዩበት ጊዜ ነበር። አንድ ወቅት ስፍራው በውቅያኖስ ውሃ የተሸፈነ ነበር። ከዚያም ንጣፎቹ በየጊዜው እየተለያዩ መሄዳቸውን በቀጠሉ ጥቁር በውስጡም ስርጉድ ስፍራ ያለበት ስምጥ ሸለቆ ተፈጠረ።

የደናክል ስርጉድ ስፍራ አንዳንድ በጣም ወጣ ያሉ ገፅታዎች አሉት። ጋዳ አሌ የሚባል ትልቅ የጨው ጉልላት እሳተ ጋሞራ አንዱ ሲሆን ሁለት ኪሎሜትር የሚያቋርጥ ስፍራ እና የእሳተ ገሞራ ላቫ በክልሉ ዙሪያ በትኗል። በአቅራቢያ ከሚገኙ የውሃ አካል አንዱ የካሩም ሀይቅ የሚባለው የጨው ሀይቅ የሚገኝ ሲሆን 116 ሜትር ከባህር ጠለል በታች ይገኛል። ከዚያ ብዙም ሳይርቅ ደግሞ አፍሬራ የተባለው እጅግ ጨዋማ ሀይቅ ይገኛል።  በአካባቢው ከአንድ ሚሊዮን ዓመታት በታች ለሆነ ጊዜ ኖሯል፤ ያም በዙሪያው የለውን አካባቢ በአመድ እና በላቫ በመሸፈን ከአንድ ሚሊዮን ዓመታት በታች የኖረው የካትሪን ጋሻ እሳተጎሞራ ይገኛል።

በክልሉ ዋና ዋና የጨው ክምችቶች ይገኛሉ። ምንም እንኳ አደገኛ የሆነ ሙቀት የሚገኝበት ስፍራ ቢሆንም ጨው ዋና የኢኮኖሚ በረከት ነው። አፋሮች  ይህንን ጨው ያመርቱ እና በአቅራቢያ ላሉ ከተሞች በግመል ጭነው በርሃውን እያቋረጡ በማቅረብ ይነግዳሉ። የፖታሽየም ማእድንም ከፍተኛ ክምችት ይዟል የደናክል ስርጉድ ስፍራ። በጥንት ዘመን የአሞሌ ጨው እንደገንዘብ ያገለግል ነበር። ለምግብነት የሚውለው አሻቦ ጨው ምንጩም እዛው ነው።

ይህ የከርሰ ምድር ገፅታ ከምድሪቷ ትላልቅ ንቁ የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴዎች ካለባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በዚህ የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴ አማካይነት የስርጉደቱ ስፍራ ወለል በላቫ፣ በስፋት ደግሞ በባዛልት ማእድን የተሸፈነ ነው።  ቀጣይነት ያለው የእሳተ ጎሞራ ሂደት እንደ ፖታሽ፣ ሰልፈር፣ ቤንቶናይት እና ጂፕሰም የተባሉ ዋና ዋና ማእድናት እንዲፈጠሩ አድርጓል። አልፎም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የጅኦተርማል ሀይል ምንጮች እና ሞቃት ፍል ውሃዎች ይገኙበታል። አብዛኛው የክልሉ የማእድን አቅም የሚገኘው በዳሎል፣ በርሃሌ እና አፍዴራ በተባሉት የዞን ሁለት ወረዳዎች ነው። እንዲሁም ኤሊዳር፣ ዱብቲ እና ሚሌ ከዞን አንድ እና ገዋኔ ከዞን ሁለት የተወሰነ የማእድን ተስፋ ያለባቸው ስፍራዎች ናቸው።

ዳሎል አንዱ የዴናክል ክልል ሲሆን ከባህር ጠለል 92 ሜትር በታች ይገኛል። በምድራችን ከፍተኛው አማካይ የሙቀት መጠን የሚመዘገብበት ስፍራ ነው። ዳሎል የሞቃታማ በርሃ አየር ንብረት ከልክ ያለፈ መገለጫ ሲሆን የደናክል በርሃም የተለየ ስፍራ ነው።  ዳሎል በምድሪቱ አመቱን ሙሉ ሞቃታማ  ስፍራ ሲሆን በቅርብ ጊዜም እንደ ክብረ ወሰን  ከፍተኛ አማካይ የሙቀት መጠን የተመዘገበበት ነው። እስካሁን የተመዘገበው ከፍተኛው የሙቀት መጠን 49 ዲግሪ ሴሊሺየስ ነው።

ኤርታሌ በዴናክል ስርጉድ(ዲፕሬሽን) ውስጥ የሚገኝ የአለማችን አስገራሚ ስፍራ ነው። ኤርታሌ የባዛልት ጋሻ እሳተጎሞራ ሲሆን ከዴናክል ስርጉድ 631 ሜትር ከፍ ብሎ የወጣ ልዩ ስፍራ ነው። እሳተገሞራው ንቁ የላቫ ሀይቅ የያዘ ነው። የሚንተከተከው የእሳት ፈሳሽ እየዘለለ ይረጫል። ለአይን የሚማርክ የተለያዩ ቀለማትን የሚታይበት ልዩ ስፍራ ሲሆን የአካባቢው ሰዎች “የሲኦል መግቢያ በር” ይሉታል።

ከኤርታሌ የሚወጣው ጭስ ጠንካራ እና ሁሌም ያለ ነው። እናም ሁሉም ጎብኝዎች ዳር ቆመው ከልክ በላይ ጭስ እንዳይስቡ ማስክ ይለብሳሉ። በተለይ አስም ላለባቸው ወይም በሌላ መንገድ ጭስ የማይስማማቸው አጋዥ መተንፈሻ መያዝ እና ብዙ ሰዓት በቦታው ማሳለፍ እንደሌለባቸው ይመከራል።

ይህ በእንዲህ ባለበት ነው በቅርቡ በዚያው ስፍራ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ንቁ ያልነበረ እሳተጎሞራ ፈንድቷል። ፍንዳታው ከፍተኛ የነበረ ሲሆን የእሳተጎሞራ አመድ እና ትቢያ አህጉራትን አቋርጦ ያለበሰ እና በህንድ እና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በረራ እንዲቋረጥ አድርጓል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ 50 የታወቁ እሳተ ጎመራዎች ያሉባት ሲሆን አብዛኞቹ ለሺዎች ዓመታት ንቁ ሳይሆኑ የቆዩ ናቸው።

 

አጫር እዉነታ

 

አፋር መገኛ

 

የመገኛ ቦታ…. ኢትዮጵያ

መዲና………. ሰመራ

ስፋት…….. 72ሺህ53 ኪሎ ሜትር ስኩዌር

የሕዝብ ቁጥር….. አንድ ሚሊዮን  152 ሺህ 3መቶ

ዞኖች… ስድስት ዞኖች፣ 32 ወረዳዎች፣ 47 ከተሞች አሉት

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የህዳር  29  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here