በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት የሰው ልጆችን አሁናዊ የምግብና የኢንዱስትሪ ግብዓት ፍላጎት ከ40 እስከ 50 በመቶ ድረስ የሚሸፍን መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያን በተመለከተ እየተስፋፋ እየመጣ ያለው የመስኖ ልማት በምግብ ሰብል አገሪቱን ለማስቻል ያለውን ሚና እየጨመረ መምጣቱን ማሳያ ነው። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመስኖ ስንዴ ልማት የአንበሳውን ድርሻ እየወሰደ መሆኑና በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል በሚደረገው ጉዞ የጎላ ሥፍራ አለው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የዓለም
ሀገራት የውኃ አጠቃቀምን በማሻሻል የምግብ
ፍላጎታቸውን ለማሳካት እና በዓለም ገበያ
ተወዳዳሪ ምርቶችን ለማቅረብ መስኖን በዋናነት
እየሠሩበት ይገኛሉ:: ውጤታማ
የውኃ አጠቃቀምን በመተግበር መስኖን
ለምርታማነት ቀዳሚ መፍትሔ አድርገው
ለመሥራት ላቀዱ ሀገራት በተሞክሮነት ከሚነሱ በርካታ ሀገራት ሀገራችንም ይህን ልምድ በመውሰድ እየተገበረች ይገኛል::
የአነስተኛ መስኖው የአገሪቱን የአትክልትና ፍራፍሬ በተለይም እንደ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ጎመንና ሌሎች ተመሳሳይ አትክልትን ፍላጎት በማሟላት ያለውን ሚና እስካሁን ተኪ አልተገኘለትም። ከዚህ በተጨማሪም የአነስተኛ መስኖ ልማት ለገጠር አካባቢ ማኅበረሰብ፣ በተለይም ለወጣት ሴቶች፣ ትልቅ የሥራ ዕድልን ያበረክታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በአነስተኛ ማሳ ላይ ሕይወቱን ለመሠረተው አርሶ አደር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከመሆን ባሻገር የተሻለ የአመጋገብ ስብጥር እንዲኖረው ብሎም ጤናው የተጠበቀ እንዲሆን ይረዳል።
ግብርና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሰረት በሆነበትና የዝናብ እጥረት መከሰት እንደችግር እየተነ ባለበት በዚህ ወቅት ዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆኖ ማምረት የህዝቡን የምግብ ዋስትና ከመሸርሸር ባሻገር ባጠቃላይ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ፤ እንዲሁም በኢንዱስትሪያላይዜሽንና በዓለም አቀፍ ምርትና ንግድ ስርዓቱ ውስጥ ሚናችንን የመወጣት ርእይ መሰናክል መሆኑ አይቀርም።
በሌላ በኩል ከፍኛ የውኃ ጸጋ ያላት ኢትዮጵያ ባላት ሀብት ልክ ተጠቃሚ አይደለችም፤ ዘርፉ አለመዘመኑም ተጠቃሽ ምክንያት ነው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ያላትን ከፍተኛ የእርሻ መሬት ከእምቅ የውኃ ሀብቷ ጋር በማቀናጀት ምርታማነትን
ለማሳደግ ትኩረት ሠጥታለች፤ ይህም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡
ይህ እውን እንዲሆን እንደማሳያ ሀገሪቱ ካላት የተመቸ የልማት ቀጣና ውስጥ ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችለውን በጥናት መለየት፣ የተለያየ አቅም ያላቸውን የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን መገንባት፣ የወደፊት ልማትን ሊሸከም እና ሊያዘምን የሚችል ዘመናዊ አሠራርን ማስተዋወቅ እና የአፈር ማዳበሪያን የአቅርቦት እና የዋጋ ውድነት በመፍታት በዘርፉ ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ ለመውጣትም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት ላይ መሆን ለዘርፉ ለተሰጠው ትኩረት እንደማሳያ ነው::
የእርሻ መሬታችን ለዘመናት ሳይንስ በብቃት ባልደገፈው ዓይነት ሲመረትበት መኖርና በየጊዜው ምርታማነቱ እየቀነሰ መሄደ ሲታይ በዝናብና በባህላዊው የአመራረት ዘይቤ ላይ ጥገኛ ሆኖ የማምረት ባህል መቆም እንዳለበት እንረዳለን፡፡
ኢትዮጵያም እንደሀገር የመስኖ ልማት
ሥራን በትኩረት እያከናወነች ትገኛለች:: ውጤትም አስገኝቷል፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየዳረጋት የነበረውን
የስንዴ ምርት ለማስቀረት በተሠራው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ መሆኗ ደግሞ ማሳያ ነው:: መንግሥት ለመስኖ ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ስንዴ ከውጪ ማስገባት አቁማለች፡፡ በ2018 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ልማት
ከአራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማትም ታቅዷል::
በዚህም ከ175 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል:: ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ለግብርና መር ኢንዱስትሪ ዘላቂ ስንቅ ነው::
ይህን ለማሳካት ዝናብ ላይ ጥገኛ በሆነ
የግብርና ሥራ (መደበኛ የእርሻ ሥራ) ሳይሆን
ከመስኖ ልማት
በሚገኝ ምርት መሆን አለበት፡፡
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


