የላቀው ስጦታ

0
13

የላቀው ስጦታ ሳባ ሙሉጌታ ሬድ  ሳተርደይ(red saturday)በሚል ኢትዮጵያን፣ ደቡብ አፍሪካን እና  ናይጄሪያን ጨምሮ ከአስር በላይ ሀገራት የተሳተፉበት የደም ልገሳ መርሀ ግብር (ፕሮግራም)  ከሰሞኑ ተካሂዷል።  በአፍሪካ ደረጃ በተካሄደው “አንድ አህጉር፣ አንድ ዓላማ፣ አንድ ቀን አህጉር አቀፍ የደም ልገሳ መርሐ ግብር” የአማራ ክልል ደም ባንክ ከአዲስ አበባ ደም ባንክ አገልግሎት በመቀጠል በአንድ ቀን አንድ ሺህ 96 ከረጢት ደም በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።በኢትዮጵያ ደም ልገሳ የተጀመረው  በ1969 ዓ.ም ነው፡፡  ልገሳው የተጀመረውም  በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ነበር፡፡ በወቅቱ በሀገሪቱ የተለያዩ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በማጋጠማቸው  ምክንያት የደም ባንክ ሊቋቋም መቻሉን ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮም በጎ ፈቃደኛ  ሰዎች ደም እየለገሱ ሕይወት እያተረፉ ይገኛሉ።

 

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በሰላም ካምፓስ ደም ልገሳ መርሀ ግብር(ፕሮግራም) ላይ ያገኘነው ተማሪ ሚኪያስ ቃልኪዳን ለ12ኛ ጊዜ ነበር ደም እየለገሰ ያገኘነው፡፡ “ደም ለመለገስ የማንም ጉትጎታ እና ቅስቀሳ አያስፈልግም” የሚለው ሚኪያስ፤ ደም በመለገስ የእናቶችን እና የሕጻናትን ሞት በመታደጉ ውስጣዊ ሰላም እንደሚሰማው ነግሮናል፡፡ “ደም ብትለግሱ የሚጎዳችሁ ነገር የለም ትጠቀማላችሁ፤  ስለዚህ “ደም ለግሱ! ሕይወት አትርፉ!” በማለት  መልእክቱን አስተላልፏል።

 

ሰዎች በሕይወት እንዲቆዩ ሁለተኛ እድል ከሚሰጡ በርካታ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች መካከል ሌላዋ ተማሪ ሳሮን አታክልቲ ናት፡፡ ሳሮንን በባሕር ዳር ከተማ  ለአራተኛ ጊዜ ደም ስትለግስ ነበር ያገኘናት፡፡ ሳሮን ሰዎች ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ  በደም እጥረት  ሲሞቱ በማየቷ “ለምን እኔስ  ደም አልለግስም” በሚል ስሜት ተነሳስታ ደም መለገስ ጀመረች።  የእሷ  ደም  የሰዎችን ሕይወት እንደሚያስቀጥል ስታስብ ደግሞ ደስታ እና ሰላም እንደሚሰማት   ገልጻልናለች፡፡

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ  በሰላም ካምፓስ የደም ልገሳ መርሀ ግብሩን (ፕሮግራሙን) ሲያስተባብር  ያገኘነው ነርስ መላክ ውዴ እንደገለጸልን በአሁኑ ጊዜ ደም ለመለግስ ያለው የሰው ፍላጎት ከበፊቱ የተሻለ መሆኑን ነው፡፡ የጤና ባለሙያው እንደገለጸው ደም ለመለገስ በመጀመሪያ ሙሉ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡  ለመለገስም እድሜያቸው ከ18 እስከ 65፣ የሰውነት ክብደታቸው ከ45 ኪሎ በላይ መሆን አለበት፡፡ የስኳር ፣ የኩላሊት፣ በደም ሊተላለፉ ከሚችሉ  በሽታዎች(ሂፐታይተስ፣ ኤች.አይ ቪ  ) ነጻ  መሆን አለባቸው፡፡

ሰዎች ደም ለግሰው የሰውን ሕይወት ከታደጉ በኋላ በርካታ ጠቀሜታዎችን እንደሚያገኙም ነው የጤና ባለሙያው ያስገነዘበው፡፡ በዚህም  ለጋሾች የጤናቸውን ሁኔታ እና የደማቸውን አይነት  ያለ ክፍያ ማወቅ ያስችላቸዋል፣ የሰብዓዊ አገልግሎት ተሳታፊ ይሆናሉ፤ እንዲሁም  የሕሊና እርካታን ያገኛሉ፡፡

ደም የሚለግሱ ሰዎች ከማይለግሱት ጋር ሲነጻጸሩ  በድንገተኛ የልብ አደጋ እና በካንሰር  ሕመም የመጋለጣቸው አጋጣሚያቸው አነስተኛ ነው፡፡ በዓለም የጤና ድርጅት እ.አ.አ. በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ደም በመለገስ ብቻ የደም ፍሰትን ለማሻሻል እና የደም ቧንቧ መዘጋትን ለመቀነስ ይረዳል፡፡

የድርጅቱ መረጃ  እንደሚያመላክተው  ደም በሚለገስበት ጊዜ ለጋሹ በጥሩ ጤንነት ላይ መሆን አለበት፡፡ አንድ ሰው ጉንፋን፣ የጉሮሮ መቁሰል፣ የሆድ ቁርጠት ወይም ማንኛውም ኢንፌክሽን ካለበት ከበሽታው እስኪያገግም ድረስ ደም መስጠት አይችልም፡፡ አንቲባዮቲክ መድሃኒት የሚወስዱ ሰዎች ቢያንስ መድሃኒቱን ከጨረሱ ከሰባት ቀናት በኋላ  ደም መስጠት እንደ ሚችሉም አስገንዝቧል፡፡

ንቅሳት ከተነቀሰ ወይም ቀዶ ጥገና ካደረገ ስድስት ወር ያላለፈው ሰው ደም መለገስ እንደማይችልም መረጃው ጠቁሟል፡፡ ነፍሰጡሮች፣ ጡት የሚያጠቡ እናቶች፣  አስም ያለባቸው፣ ደም የሚፈሳቸው፣ የካንሰር ሕሙማን እና የደም ማነስ ያለባቸው ሰዎችም ደም መስጠት አይችሉም፡፡

ደም የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ደግሞ የደም ማነስ ያለባቸው፣ ከፍ ያለ ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ፣ በተለያዩ አደጋዎች ሳቢያ ደም የፈሰሳቸው፣ የካንሰር ሕሙማን፣ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ደም የሚያስፈልጋቸው እናቶች፣ በተለያያዩ የጤና ችግሮች እንደተወለዱ ደም የሚያስፈልጋቸው ሕጻናት፣ በዘር ውርስ የሚመጡ የደም መርጋት ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የጤና ባለሙያው አቶ መላክ ውዴ ማንኛውም ሰው ደም ለመስጠት መስፈርቶችን ካሟላ ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

 

የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው ደኅንነቱ የተጠበቀ ደም ሕይወትን ያድናል፡፡ አንድ ሰው አንድ  ጊዜ   የለገሰው ደም የሦስት ሰዎችን  ሕይወት ይታደጋል፡፡ እያንዳንዱ የደም ልገሳ የተስፋ ስጦታ ነው። ማንኛውም ሰው የትም ቦታ ደም መውሰድ ሲያስፈልገው ደኅንነቱ የተጠበቀ ደም በወቅቱ ማግኘት አለበት። ሆኖም በብዙ አጋጣሚዎች በተለይም በድንገተኛ ሁኔታዎች ወይም አሁንም የልገሳ ሥርዓቶች እየተካሄዱ ባሉበት ጊዜ እንኳ ፍላጎቱ ከአቅርቦት ይበልጣል።

ደም መለገስ  በድንገተኛ አደጋዎች እና  በወሊድ ጊዜ የሚፈጠር ደም መፍሰስን ተከትሎ የሚከሰትን ሞት ይከላከላል፡፡  በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ይታደጋል።  ደም መስጠት  ተስፋ መስጠት ነው፡፡ ደም መውሰድ ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በሕይወት እና በሞት መካከል ያለውን ልዩነት ሊያመለክት ይችላል፡፡

 

ደም መለገስ የሚችል ማንኛውም ሰው በየጊዜው በበጎ ፈቃደኝነት ያለ ክፍያ ደም ልገሳ ማድረግ እንዳለበት በማሰብ ሁሉም ሀገራት በቂ እና አስተማማኝ የደም አቅርቦት እንዲኖራቸው ማድረግ እንዳባቸው የዓለም ጤና ድርጅት ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ደም መለገስ የአብሮነት መንፈስን እንደሚያዳብርም ነው መረጃው የሚጠቁመው፡፡

 

ጤና አዳም

* ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ እስከ 54 በመቶ የሚደርሰው ደም ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት ይሰጣል። ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ግን በጣም በተደጋጋሚ ደም የሚለገሳቸው ከ60 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ነው፡፡ ከተሰበሰበው ደምም እስከ 76 በመቶ የሚሆነውን  ይጠቀማሉ።

* የተለገሰን ደም ከመጠቀም በፊት መመርመር እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል። ኤች አይ ቪ፣ ሄፐታይተስ ቢ፣ ሄፐታይተስ ሲ እና ለቂጥኝ ምርመራ ማድረግ የግዴታ መሆን አለበት።

*ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ደም መስጠት ታካሚዎችን ለከባድ አሉታዊ የደም ምላሾች እና ደም በመውሰድ ለሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ያጋልጣል።

 

ምንጭ:- የዓለም ጤና ድርጅት

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የህዳር  29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here