መገኛዋ ደቡብ ምስራቅ አውሮፓ፤ ከታላቁ ባልቲክ ባህር ደቡባዊ አካባቢ ነው። በደቡብ ዩክሬን፣ በምስራቅ ሞልዶቫ፣ በደቡብ ቡልጋሪያ፣ በምዕራብ ደግሞ ሰርቢያ እና ሃንጋሪ ያዋስኗታል። በዚህ ዕትም ዋና ዋና መገለጫዎቿን እየጠቃቀስን የምንቃኛት ሃገር ሮማኒያ።
የሮማኒያ መልካምድራዊ አቀማመጥ የተለያዩ ውበቶች መገለጫ ነው። ከነዚህ ውስጥ የካርፓቲያን ተራሮች፣ ሜዳዎች፣ ጥቅጥቅ ዛፎች እና የጥቁር ባህር ዳርቻ ይገኙበታል። ትራንቫሊያ አልኘስን ጨምሮ ጥቅጥቅ ዛፎች፣ የዴኖቭ ወንዝ ሜዳዎች እና ዳኖቭ ዴልታ ደግሞ ሮሜኒያ ገዝፋ ከምትታወቅባቸው መገለጫዎች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ሮማኒያ በቆዳ ስፋቷ በአውሮፓ 12ኛ ደረጃን ትይዛለች። በምስራቅ አውሮፓም ብቸኛዋ የላቲን ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሏት ሃገር ናት። 19 ሚሊዬን ለሚጠጋ ህዝብም መኖሪያ ሆናለች።
ቡካሬስ የሮማኒያ ዋና ከተማ ናት። ሁለት ሚሊዬን የሚጠጋ ኗሪ አላት። ጥንታዊ የኪነጥበብ ህንፃዎቿ እና በታዋቂ ባለሙያዎች የተቀየሱት ጎዳናዎቿ ደግሞ የውበቷ መገለጫዎች ሆነዋል።
የቡካሬስ ህንፃዎች ብዕር ሆነውት ዘመን ከጌጠኛ ድንጋይ፣ ከጥንታዊ ድንጋይም፣ ከአልሙኒየምም እያጣቀሰ ታሪክ የሳለባት የስዕል ሸራ ትመስላለች። ዋና ከተማዋ የሮማን፣ የኦቶማን፣ የኮሚኒዝም እና የካፒታሊዝም አሻራም ይታይባታል። በአንዱ የጎዳናዋ አቅጣጫ ብቻ የ15 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ የ600 ዓመታትን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያመላክታል።
የሮማኒያ ፓርላማ መቀመጫ ደግሞ በዓለማችን ከተገነቡ ህንፃዎች መካከል በክብደቱ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። 40 ቢሊዮን ኪሎግራም ወይንም አራት ሚሊዮን ቶን ይመዝናል። ይህም የምድራችን ከባዱ ህንፃ የሚል ማዕረግን አሰጥቶታል።
በስፋቱም ከፔንታገን ቀጥሎ ለአስተዳደር ሥራ ከዋሉ የዓለማችን ህንፃዎች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አጠቃላይ 365 ሺህ ካሬ ሲሆን አንድ ሺህ ክፍሎችም አሉት። ህንፃው ከፓርላማ መቀመጫነቱ ባሻገር ዓለማቀፍ እና ሃገርአቀፍ ስብሰባዎች የሚስተናገዱበት በርካታ አዳራሾች እና ሙዚየሞችም አሉት። ይህም ሆኖ 70 ከመቶው የህንፃው ክፍል ዛሬም ድረስ አገልግሎት ላይ አልዋለም። የኮሚኒዝም አሻራ ከሆኑት የከተማዋ ግንባታዎች መካከል ትልቁ ሲሆን በቡካሬስ ከሚገኙ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች አንዱ ነው።
በዋና ከተማዋ ቡካሬስ የሚገኘው የሮማኒያ ፓርላማ መቀመጫ ህንፃ እ.አ.አ ከ1984 እስከ 1997 ለግንባታው ብቻ 13 ዓመታትን ፈጅቷል። ለህንፃው ዲዛይን 700 የዘርፉ ባለሙያዎች፣ በግንባታው ደግሞ አንድ መቶ ሺህ ሰራተኞች ተሳትፈዋል። ከህንፃው ፊትለፊት ደግሞ ህብረት የተሰኘ አደባባይ ይገኛል። የቀድሞው ኮሚኒስት ሃገር እንደመሆኗ ህብረት፣ አንድነት፣ አብዮት … የሚሉ ስያሜዎች በሮማኒያ የተለመዱ ናቸው።
በሮማኒያ እ.አ.አ በ1989 ተካሂዶ የኮሚኒዝም አገዛዝ እንዲያበቃ ላደረገው አብዮት መታሰቢያ እንዲሆን የተሰየመ አደባባይ በቡካሬስ ይገኛል። ሮማኒያ እና ቱርክ ያላቸውን ወዳጅነት ለመግለጽ ታስቦም የሙስጦፋ አታካ (የዘመናዊ ቱርክ አባት) ሃውልት በመሃል ቡካሬስ ተገንብቷል።
የሮማኒያ ዋና ከተማ ቡካሬስን ሳይለቁ በሃይቅ እና ጫካ ተፈጥሮን ለማድነቅ ከሻቱም ሄርስት ሪው ፓርክ ወይንም ታሪካዊው የተጅመጅ ጋርደን ተመራጭ ናቸው።
ደሮማንስ እና ፕሪማቬሪ የቡካሬስ ዘመናዊ እና ቅንጡ ሰፈሮች ናቸው። የኤምባሲዎች መገኛ፣ የዲፕሎማቶች እና የአምባሳደሮች መኖሪያ፤ ጥንታዊ ቅንጡ ቪላዎች እና ዘመናዊ ካፌዎችም መገኛ ሰፈሮች ናቸው። በተለይም ፕሪማቬሪ፤ ድሮ የኮሚኒስት ሊሂቃን መኖሪያ ነበረች። ዛሬ ደግሞ ተረኞቹ ካፒታሊስት ባለሃብቶች ተረክበዋታል።
ከምድራችን አማላይ ጎዳናዎች መካከል ዋነኛው የሚገኘውም በሮማኒያ ነው። ትራንስቫግራን-ከቮላሃ የሚያገናኝ የ90 ኪሎሜትር መንገድ ነው። አንዳንዶች ትራንስቫግራን አውራ ጎዳና ሌሎች ደግሞ ዲኤን7ሲ ይሉታል። እ.አ.አ በ1974 ነው የተገነባው። በካርፒቲያን ተራሮች የደቡብ ጫፍ ይገኛል።
መንገዱ የአካባቢውን ውበት ብቻ ሳይሆን ሮማኒያን ኢንጂነሮች የምህንድስና ጥበብም ይመሰክራል።
የ2400 ሜትር ከፍታ ባለው ፈታኝ መልካምድር ላይ ተራራ እና ሸለቆ፣ ቋጥኝ እና ጫካዎችን የሚያቆራርጥ፤ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለወታደራዊ አገልግሎት ሲባል ስድስት ሺህ ወታደሮች ተሳትፈውበት የተገነባ ነው።
ኩርባዎችን እየታጠፉ፣ ድልድዮችን እያቋረጡ፣ ጫካዎች ውስጥ እየገቡ በትራስቫግራን ጎዳና ላይ ማሽከርከር ከድካም ይልቅ የመንፈስ እርካታን ያጎናፅፋል። ከሰኔ አጋማሽ እስከ ጥቅምት ወር ያለው ጊዜ ደግሞ የአካባቢው ውበት ጎልቶ የሚታይበት ነው። በጎዳናው አጋማሽ ላይ የተገነባው የቢራሩ ግድብ ደግሞ የአካባቢውን ውበት ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን አስችሎታል።
በሮማኒያ ውብ ተፈጥሯዊ ገፅታ እና የሰው ልጅ ድንቅ የጥበብ መገለጫ ብቻ አይደለም የቱሪስትን ቀልብ የሚስበው። የመቃብር ስፍራም ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ እናገኘዋለን። በሮማኒያ የዓለም ቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ ዴሜትሪ ሴሜትሪ ይጠቀሳል። ይህን የቀብር ቦታ ከሌሎች ለየት አድርጎ የተመልካችን ቀልብ እንዲስብ ያደረገው እውነትን በመያዙ ነው። “ሟች አይወቀስም” የሚለው የኛ አባባል አዚህ ቦታ ተሽሯል። ሟች በህይወት እያለ የነበረው ባህሪ እንዳለ በፅሁፍ ይገለፃል። ደግ በደግነቱ፤ መጥፎም በክፋቱ ሞቶም ይታወሳል።
በሮማኒያ ከኬጂ እስከ ዩኒቨርስቲ ያለው ትምህርት በነፃ ይሰጣል። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በምህንድስናው ዘርፍ ሮማኒያውያን ጥሩ ስም አላቸው። በህክምናው ዘርፍም ዓለማቀፍ ተማሪዎችን ተቀብላ ታስተምራለች። በሮማኒያ የሚገኝ የትምህርት ማስረጃ በአውሮፓ ህብረት ሃገራት ተቀባይነት አለው። ህክምናም በሮማኒያ ለዜጎች በነፃ ይሰጣል።
ሮማኒያ የአርብቶ አደሮችም ሃገር ናት። አርብቶ አደሮቹም ታዲያ እንደኛው ሃገር ከቦታ ቦታ ለእንስሳት መኖ ፍለጋ እየተንቀሳቀሱ የእንስሳት እርባታን ያከናውናሉ።
ምንጭ፡- Scemoc Hunter
– windo pia
– timisoala፡፡
አጫር እዉነታ
ሮማኒያ
- መገኛዋ ደቡብ ምስራቅ አውሮፓ፤ ከታላቁ ባልቲክ ባህር ደቡባዊ አካባቢ ነው።
- ሮማኒያ በቆዳ ስፋቷ በአውሮፓ 12ኛ ደረጃን ትይዛለች።
- በምስራቅ አውሮፓም ብቸኛዋ የላቲን ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሏት ሃገር ናት።
- 19 ሚሊዬን የሚጠጋ ህዝብ አላት።
- ቡካሬስ የሮማኒያ ዋና ከተማ ናት።
- የሮማኒያ ፓርላማ መቀመጫ ደግሞ በዓለማችን ከተገነቡ ህንፃዎች መካከል በክብደቱ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም።
- 40 ቢሊዮን ኪሎግራም ወይንም አራት ሚሊዮን ቶን ይመዝናል።
- ከምድራችን አማላይ ጎዳናዎች መካከል ዋነኛው የሚገኘውም በሮማኒያ ነው።
- ደሮማንስ እና ፕሪማቬሪ የቡካሬስ ዘመናዊ እና ቅንጡ ሰፈሮች ናቸው።
- በሮማኒያ የዓለም ቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ ዴሜትሪ ሴሜትሪ ይጠቀሳል።
(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር የታህሣስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


