ልጆች እና ወላጆች እንዴት ሰነበታችሁ፡፡ ልጆች ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት እየተባባሰ መጥቷል። ነገሩን
የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ አብዛኛው ጥቃት የሚፈፀመው በቅርብ ሰዎች (ጎረቤት፣ ዘመድ፣ እንጀራ አባት…ወዘተ)
መሆኑ ነው። ልጆች የፆታ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመከላከል ረገድ ተቀዳሚው ኃላፊነት የሚወድቀው በልጆች ላይ ሳይሆን
በወላጆች ላይ ነው። በመሆኑም ስለዚህ ጉዳይ ልጆችን ከማስተማር በፊት ወላጆችን ማስተማር ያስፈልጋል።
ልጆችን እንዴት ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ማስተማር ለወላጆች በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ከጥቃት
መጠበቅ እንደሚችሉ የተወሰኑ የሚረዱ ነጥቦችን እነሆ፦
1) ልጆችን የግል የአካል ክፍሎች (Private body parts) ማስተማር። እነዚህን የሰውነት ክፍል ልጆች ራሳቸው እንዲታጠቡ
ከአራት ዓመት ጀምሮ ማስተማር።
2) ብዙ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሆነው የሚያውቁት ሰው ሲመጣ “ሂጂና ሳሚው!” ይላሉ። ቅርርብ ያላቸው አካላዊ ንኪኪዎች
ማለትም መተቃቀፍ/መሳሳም ልጆች ካልፈለጉ ፈቃዳቸውን ማክበር ወሳኝ ነው። ይሄም የማይፈልጉትን ነገር “እምቢ” የማለት ፈቃድ
እንዲኖራቸው ያግዛል።
3) ወላጆች በሌሉበት ማንም ሰው ታፋ ላይ አስቀምጦ እንዳያጫውታቸው መምከር።
4) ማንኛውም ትልቅ ሰው ህፃናትን “ሚስቴ” ወይም “ባሌ” እንዳይል መከልከል።
5) ስለ ፆታዊ ጥቃት ስርጭት፣ መከላከያ መንገዶች…ወዘተ ማስተማር ናቸው።
ከእነዚህ በተጨማሪ ወላጆች በሌላችሁበት አንድ ሰው ልጃችሁን በፆታ ሊያስነውረው ቢሞክር ልጁ ሊያደርግ የሚገባውን አንዳንድ
ነገሮች ማስተማር ነው። ብዙውን ጊዜ ወላጆች እንዲያደርጉት የሚመከሩት አንዱ ዘዴ በጨዋታ መልክ ማስተማር ነው። ወላጆች “. .
. ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል ጥያቄ ይጠይቁት እና ልጁ መልስ ይሰጣል። እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ:- “አብረን ገበያ ሄደን
ብንጠፋፋ ምን ታደርጋለህ/ጊያለሽ? እንዴት አድርገህ/ሽ ታገኘኛለህ/ኚኛለሽ?” ልጁ ወይም ልጅቷ የሚሰጡት መልስ ከምትጠብቁት
የተለየ ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ “ከዚህ የተሻለ ምን ማድረግ የምትችል/ይ ይመስልሃል/ሻል?” እንደሚለው ያሉ ተጨማሪ
ጥያቄዎችን በመጠየቅ ምን ማድረግ እንዳለባቸአው እንዲያውቁ ልትረዱ ትችላላችሁ።
ምንጭ፡ ሲትዝን ኢንፎርሜሽን እና ሴቭ ዘ ቺልድረን
ተረት
ጋብቻው
በአንድ ወቅት አይጦች ሁሉ ተሰባስበው ችግራቸውን እየተወያዩ ሳለ “አንደኛው ምን ብናደርግ ይሻለናል? ድመቶች ዝርያችንን
እየጨረሱ ነው! ”አለ:: ሌሎቹም አይጦች “አይጦችን በድመቶች ከመበላት የሚያድነው ብቸኛው መንገድ ከድመቶች ጋር በጋብቻ
መተሳሰር ነው” አሉ:: ከዚያም አንጋፋ አይጦችን መርጠው ለሽምግልና ወደ ድመቶች ላኳቸው::
ሽማግሌ አይጦቹም “እባካችሁ ጠላትነት ይቅርብን:: ፀባችንን አቁመን በጋብቻ እንተሳሰር” ብለው ድመቶችን ጠየቁ:: ከድመቶቹም
አንዱ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለ:: አይጦቹም “አንዲቷን ሴት አይጣችንን ለአንዱ ወንድ ድመታችሁ ሚስት ትሆነው ዘንድ
እንሰጣችኋለን” አሉ:: በዚህም ተስማምተው የሰርጉ ቀን ተቆረጠ:: ሽማግሌዎቹም ወደ አይጦቹ ተመልሰው ስለሆነው ነገር ሁሉ
ሲነግሯቸው አይጦቹ በጣም ተደሰቱ:: በሰርጉም እለት ድመቶቹ ወደ አይጦቹ ቤት እየጨፈሩ መጡ:: እየጨፈሩም እያለ
ጭራዎቻቸው ቀጥ ብለው ቆመው ነበር:: አይጦቹም በሩቅ በጥንቃቄ ያዩአቸው ነበር:: ድመቶቹ “ቤቷ እዚያ ላይ ነው አንገቷም
እንደ ለጋ ዛፍ ነው” እያሉ እየዘፈኑ ሲመጡ አንዱ አይጥ ይፈራና “እባካችሁ ወደ ቤት ውስጥ ገብተን እዚያ ሆነን እንያቸው::” አለ::
ሌላዎቹ አይጦች “ለምን? ሰርግ አይደለም እንዴ?” ቢሉም አንዳንዶቹ ወደቤት በመግባቱ ስለተስማሙ ወደ ቤት ውስጥ ሲገቡ
የቀሩቱ ውጪ ሆነው ሙሽራውን ይጠባበቁ ጀመር:: ድመቶቹ እየጨፈሩ ደርሰው አይጦቹን ዘለው ያዟቸው:: ቤት ውስጥ የነበሩት
አይጦች ግን ተረፉ:: እንዲህም አሉ “ይህ እንደሚሆን አውቀን ስለነበር አመለጥን”፡፡
ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ተረቶች
ሞክሩ
- ዝናብ ወደ ምድር ሲወርድ ወደላይ የሚወጣ ምንድን ነው?
- መሬት ላይ ብናዬውም ሁልጊዜም የማይቆሽሽ ምንድን ነው?
- ትንሽ ዕቃ ከገደል ተጣብቃ ምንድን ናት?
መልስ
- ጆሮ
- ጉም (ጪስ)
- ጆሮ
ነገር በምሳሌ
- እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል፤ ባለፈ ነገር ከመቸንከር ወደ ፊት መቀጠል እድል ይዞ ይመጣል፤
- ሀሰትና ስንቅ እያደር ያልቅ፤ ውሸት አንድ ቀን ይጋለጣል፡፡
- ማምሻም ዕድሜ ነው፤ ባለችው ጊዜ መጠቀም::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የታህሣስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


