ነገ እንዴት ይሠራል?

0
16

“የነገ ሀገር የዛሬ ሕጻናትን ትመስላለች፣ ዛሬ ሕጻናት ላይ  ካልሠራን ደግሞ የነገ ሀገርን እንደዘነጋን ይቆጠራል። እንደ አለመታደል ሆኖ በርካታ ሕጻናት ከችግር ጋር ይጋፈጣሉ። ይህም የነገዋን ዓለማችንን ወደ ከፋ ችግር እንዳያስገባት ሁሉንም ሊያሳስብ ይገባል፡፡” በማለት  የተባበሩት መንግሥታት  የሕጻናት መርጅ ድርጅት (ዩኒሴፍ)በድረ ገጹ ያሰፈረው  መልዕክት ነው።

መረጃው እንዳብራራው በሕጻናት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ይከፋል። ይህ ደግሞ ወትሮውንም በድህነት ውስጥ ለሚገኙት ሀገራት ችግሩን  “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ“ እንዲሉ  ያደርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቅድመ ሕጻናትን አስተዳደግ በተመለከተ ከሰሞኑ የጥናት ውጤት ይፋ ተደርጓል። በአማራ ክልል እስከ ስድስት ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ ሕጻናትን አስተዳደግ ትኩረት ያደረገው ጥናቱ በፖሊሲ የተመሠረተ ርምጃ ለመውሰድ ያስችላል ተብሏል።

የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በትብብር ያቀረቡት የጥናት ውጤት በተለይ የልጅነት ልማት አገልግሎቶችን (ጤና፣ ምግብ፣ ትምህርት፣ ወዘተርፈ) ለመስጠት መሠረት ይሆናል ነው የተባለው።

የጥናቱን ሂደት በተመለከተ ያቀረቡት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ነጻነት ፋንታሁን (ፕ/ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ250 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ችግር ውስጥ (globally at risk) እንደሚገኙ አንስተዋል። ግጭት፣ የምግብ እጥረት፣ የመሠረታዊ አገልግሎቶች (ጤና፣ ትምህትርት) አለመሟላት ደግሞ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። በመሆኑም “አስቸኳይ እና ዓለምአቀፍ ጣልቃ ገብነት (ድጋፍ) ያስፈልጋል ብለዋል።

ፕሮፌሰር ነጻነት በጥናቱ እንዳመላከቱት ችግሩ በሀገራችንም የከፋ ነው። ይህ ደግሞ የሀገራችንን ነገ አሳሳቢ ያደርገዋል። ምክንያቱም የነገዋ ሀገር የምትመስለው የዛሬ ሕጻናትን ነው። ሕጻናት ላይ በትኩረት መሥራት ደግሞ ነገን በጽኑ መሠረት ላይ መገንባት ነው።

የጥናቱን ግኝቶች ያቀረቡት ደግሞ የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ከፍተኛ የምርምር አማካሪ ስንታየሁ አባተ (ዶ/ር) ናቸው። “ለምን ሕጻናት ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈለገ?” በሚል ነበር ሐሳባቸውን የጀመሩት። ሕጻናት ላይ መሥራት የሁሉም ነገር መሠረት ነው የሚሉት አቅራቢው፤ ለአብነት ከስድስት ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት ሁለንናዊ ዕድገት አንድ ዶላር (አሁን ባለው ምንዛሬ 158 ብር ገደማ) ወጭ ማድረግ በአጸፋው 37 ዶላር (አምስት ሺህ 800 ብር ገደማ) ገቢን ያስገኛል።

በጥናቱ ውጤት እንደተመላከተው በአማራ ክልል የሕጻናት እንክብካቤ ማዕከላት (ማቆያዎች) 80 በመቶ ያህሉ ፍጹም ያልተመቹ፣ ሕጻናት ሊውሉባቸው የማይገቡ ናቸው። 46 በመቶ ያህሉ የቅድመ መደበኛ ተማሪ ሕጻናት ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት ያልሄዱ ናቸው። ገጠሩ አካባቢ ሙሉ ለሙሉ ከተጠና ደግሞ ችግሩ ከዚህ ይከፋል።

በአማራ ክልል ቀዳማይ የልጅነት ዕድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሕጻናት 21 ነጥብ ሰባት ያህሉ የሚጠበቀውን የዕድገት ደረጃ የማያሟሉ መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል። ይህም ከአምስት ሕጻናት አንዱ የዕድገት ውስንነት አለበት እንደማለት ነው። ችግሩ እንደ ዓለም አምስት በመቶ መሆኑን ልብ ይሏል።

የተመጣጠነ ምግብ እጦት፣ በእርግዝና ወቅት ተገቢውን ክትትል እና እንክብካቤ አለማድረግ፣ ተገቢውን የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች አለማግኘት ለሕጻናት ዕድገት ውስንነት በዋና ምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

ዶክተር ስንታየሁ በጥናቱ እንዳመላከቱት በሕጻንነት የዕድሜ ክልል በዋናነት እስከ ስድስት ዓመት በትኩረት ካልተሠራ ሀገራዊ ጉዳቱ የከፋ ነው። ሕጻናት መቀንጨርን ጨምሮ ለበርካታ ችግሮች ይጋለጣሉ። የትምህርት አቀባበላቸው እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ ሀገርን የከፋ ዋጋ ያስከፍላል።

ረዳ ዳርጌ (ዶ/ር/)  በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና መምህር እና የጥናቱ መሪ እና ተማራማሪ ናቸው። ምሁሩ እንዳሉት በክልሉ ያለው የሕፃናት የዕድገት ውስንነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል። ችግሩን ለማሻሻል ደግሞ ዘርፈ ብዙ ጣልቃገብነትን ይፈልጋል። ለዚህም የጥናቱ ውጤት ለሚመለከታቸው ሁሉ ፖሊሲ ማውጣትን ጨምሮ ዋና ግብዓት ይሆናል።

ዶክተር ረዳ እንዳስገነዘቡት ሕጻናት የሁሉም ነገር መሠረት ናቸው፤ በሕጻናት ዕድገት ላይ መሥራት ታዲያ ነገን በጽኑ መሠረት ላይ ማስቀመጥ ነው፡፡ ክልሉም በዚህ አግባብ በትኩረት መሥራት ግዴታው ነው፤ ለስኬቱም ርብርብን ይጠይቃል።

በሀገራችን በርካታ ጥናቶች ይካሄዳሉ፤ ሀገርን የሚያሻግሩ ውጤቶችም በጥናቶቹ ይመላከታሉ፤ ይሁን እንጂ ከመደርደሪያ(ከሸልፍ) ወይም ከጠረጴዛ ማድመቂያነት ሲሻገሩ   አይስተዋልም፤ ተግባር የራቃቸው ናቸው። “ይህ ጥናት ግን እንደተለመደው ተጠንቶ ጠረጴዛ ላይ የሚቀመጥ አይደለም። ለትግባራዊነቱ ሁላችንም ቁርጠኞች ነን!” ብለዋል። በዩኒቨርሲቲው  ማዕከል ለመክፈት ታሳቢ መደረጉ፣ ክልሉ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኑ፣ ከማን ምን እንደሚጠበቅ መለየቱ የጥናቱን ውጤት ለመተግበር መልካም አጋጣሚዎች ስለመሆናቸው አንስተዋል።

በመጨረሻም “ውጤቱን ይዘናል። ይህም ማን ላይ ምን መሥራት እንዳለብን ያመለክተናል። በዚህ አግባብ መሥራት ግዴታም ሞራላዊ ኃላፊነትም ነው” በማለት ነው ዶክተር ረዳ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ  ጥሪ ያቀረቡት።

“የጥናቱ ውጤት የወደፊታችንን እጣ ፋንታ ይወስናል” ያሉት ደግሞ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማሕበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ናቸው፤ “ለዚህም ሕጻናት ላይ መሥራት ሀገርን መሥራት ነው” ብለዋል። ይህን መነሻ በማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ስለመኖራቸውም አንስተዋል።

ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች  ትኩረት መደረጉ፣ ለመምህራን በተለያዩ ደረጃዎች ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸው፣ ከወላጆች ጋር በቅርበት መሥራት እና የተማሪዎች ምገባ ደግሞ ከተጀመሩት መልካም ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ዶክተር ሙሉነሽ እንዳሉት በተያዘው የትምህርት ዘመን አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመገብ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።

በክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊነቱም በተያዘው በጀት ዓመት ጀምሯል፤ የሕጻናት ጉዳይ ደግሞ በአሻጋሪ ዕቅዱ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ዶክተር ሙሉነሽ አመላክተዋል።

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የታህሣስ  6  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here