ማህበረሰብን የተከለች

0
12

ሃገራችን ኢትዮጵያ በርካታ አለማቀፋዊ እና አህጉራዊ ህጎችንና ደንቦችን እገዛባቸዋለሁ፣  እጠቀምባቸዋለሁ እንዲሁም እተገብራቸዋለሁ በሚልና በህጎቹ በመስማማት የፈረመቻቸው አያሌ ደንቦችና ህጎች አሏት። ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸዉ ህጎች መካከልም የሴቶች መብት አንዱ ነው። ይሁንና እነዚህን  ህጎችና ደንቦችን በማስፈጸም እና በማስተግበር በኩል ክፍተት እንዳለ በተለያየ ጊዜ የሚነሱ በርካታ ማሳያወች አሉ።

ብዙዎች ሴትነትን ከፍቅር፣ ከጥበብ፣ ከብልሃትና ልዕልና ጋር አቆራኝተውታል። ስለሴቶች አበርክቶ እና ሁለገብ ሚና በተመለከተ ዶ/ር ይሁኔ አየለ ‘’እናት’’ በሚለዉ መጽሃፋቸዉ ውስጥ “ሴትነት ጀግና እና ብልህ፣ የቤተሰብ መሰረት፣ የደስታና  የእልልታ  ምንጭ፣ እናት፣ ቃል ኪዳንና ክብር ጠባቂ፣ ሴት ልጅ ባለብዙ ጸጋዎች ከጸጋዎቿ መካከልም ጀግንነት እና ብልሃት ይጠቀሳሉ። ሴት ልጅ ባህልን ፈጥራ የማኅበራዊ ማስተሳሰሪያ ገመዶችን ገምዳ አስተሳስራ ማኅበረሰብን የተከለች ሥርዓት ናት በማለት አስፍረዋል።  … ቤተሰብ የአንድ ማኅበረሰብ የመጀመሪያ ተቋም ነው። የተቋሙ ባለሥልጣን (እመቤት) ደግሞ ሴት ናት። ያቺ ሴት እናት ናት። ቤተሰብ የስብዕና መሰረት የሚባለውም እናትን ምሰሶ አድርጎ ነው’’ በማለት የሴትን ዋጋ እና በሀገርና በማህበረሰብ ውስጥ ያላትን ዋጋ አስፍረውታል ።

ከነዚህ መገለጫወች የምንረዳው ሴቶች የማህበረሰቡ መሰረቶች መሆናቸውን ነው:: ይህን ጉዳይ የሚያጠናክርልን ደግሞ በሴቶች መብት ዙሪያ የተደነገጉና እንዲከበሩ የወጡ ህጎች መኖራቸው ነው:: በዛሬው ጽሁፍ የሴቶችን መብት ለመጠበቅ የተደነገጉት ህጎች   ምንምን ይዘቶች እንዳላቸው እናያለን::

በእነዚህ ህጎች ምንነት፣ አተገባበርና የአፈጻጸም ክፍተት ዙሪያ በአሚኮ የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ክፍል ከፍተኛ የህግ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ፍቅር በለጠ ጋር ቆይታ አድርገናል።

በተባበሩት መንግስታት እና በአህጉራዊ የሰብአዊ መብት ስርዓቶች ውስጥ ሴቶችን በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ ቡድን ውስጥ በመመደብ በልዩ ሁኔታ ጥበቃ ተሰጥቷቸው ይገኛል:: ለሴቶች መብት እውቅና የሰጡ ስምምነቶች በሁለት እንደሚከፈሉ  ከፍተኛ የህግ ባለሙያ  ወ/ሮ ፍቅር በለጠ  ይገልጻሉ:: እነሱም ጠቅላላ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እና በልዩ ሁኔታ በሴቶች ላይ የተደረጉ ስምምነቶች  በመባል በሁለት ተከፍለዋል።

ባለሙያዋ እንዳብራሩት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR ,1948)  በሰብዓዊ መብት መግለጫው ላይ እንደደነገገው ማንኛውም ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት፣ በብሔር ወይም በማህበራዊ አመጣጥ፣ በንብረት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ልዩነት ሳይደረግ በአዋጁ ውስጥ የተገለጹትን ሁሉንም መብቶችና ነጻነቶች የማግኘት መብት እንዳለው ያስቀምጣል:: በመሆኑም ሴቶች እንደማንኛውም ሰው ፆታን መሰረት ባደረገ መልኩ ልዩነት ሳይደረግባቸው የሰብዓዊ መብቶች ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው መገንዘብ ይቻላል በማለት አብራርተዋል::

እንደ ወ/ሮ ፍቅር ገለጻ በተመሳሳይም አለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (ICCPR,1966) እና አለም አቀፍ የኢኮኖሚዊ፣ የማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ስምምነት (ICESCR,1966) የስምምነቶቹ አባል የሆኑ ሀገራት በስምምነቶቹ የተዘረዘሩትን ሁሉንም የሲቪል እና የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ለማስከበር የወንዶች እና የሴቶችን እኩል መብት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ እና ተገቢ እርምጃዎችን (ህጋዊ፣ አስተዳደራዊ እና የፖሊሲ) እንዲወስዱ ያስገድዳል ብለዋል::

በሴቶች ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ልዩነት ወይም አድልኦ ለማስወገድ የወጣ  ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች (The Convention on the Elimination of All Forms of Discrimination against Women (CEDAW) 1979) በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛዉም አይነት የሃይል ተግባራትን ወይም ጥቃትን ለማስወገድ የወጣ መግለጫ (Declaration on the Elimination of Violence Against Women (DEVAW), 1993) እንዳሉ የጠቆሙት የህግ ባለሙያዋ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በበርካታ ድርጊቶች ይገለጻሉ። ጥቃት በማንኛውንም ሰው፣ በየትኛውም ስፍራ በማንም ሰው ላይ ሊፈጸም ይችላል:: ጥቃቱም በቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በስራ ቦታ ፣ በመንገድ እና በማንኛዉም ቦታ ሊፈጸም ይችላል::  ከጥቃቶች መካከል ዋና ዋናወቹ ‘’በስራ ቦታ፣ በትምህርት ተቋማት እና በቤት ውስጥ  የሚፈጸሙ   ኢኮኖሚያዊ ጥቃት  ፣ አካላዊ ጥቃት፣ ወሲባዊ ጥቃት ፣ ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጥቃት ተጠቃሾች ሲሆኑ፣  በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ምክንያት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ማናቸውም የጤና፣ የስነ-ልቦና እና የኢኮኖሚያዊ መብታቸው ላይ ተፅኖና ጉዳት የሚደርሱ ጥቃቶች ፣ ስቃይ የሚያስከትል የሚችል ማንኛውንም ድርጊት ፣ በግል ሕይወት ውስጥ የሚከሰት ማስፈራራት፣ ማስገደድ ወይም የዘፈቀደ የነጻነት መንፈግ እና  በእርጉዝ ሴቶች  የጽንስ ማቋረጥ ጥቃቶችን ያጠቃልላል“

ሀገራት ጾታዊ ትንኮሳና ሌሎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን  ለመከላከል ሁሉን አቀፍ የህግ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ባህላዊ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ከፍተኛ ባለሙያዋ አውስተዋል:: ከአለማቀፉ ስምምነት መግለጫወች ባለፈም በአፍሪካም ጉዳዩ ትኩረት እንደተሰጠው የሚያወሱ ቻርተሮች እንደሚጠቁሙ ባለሙያዋ ጠቁመዉ  ይህም የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብት ቻርተር (ACHPR, 1981) ይባላል::

በመሆኑም አፍሪካውያን ሴቶች በአፍሪካ የሴቶች መብት ቻርተር ፕሮቶኮል (Protocol to the African Charter on the Rights of Women in Africa) መሰረት ሴቶች የመከበር መብት እንዳላቸው፣ በጋብቻ ውስጥ የእኩልነት መብት እና ልጅ ለመውለድ የመወሰን መብት እንዳላቸው እና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ችግርም በማካተት ለሴቶች መብት ጥበቃ ትኩረት እንደሚሰጥ ተቀምጣል ::

ከዚህ በተጨማሪም በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል፣ ለመቅጣት እና ለማጥፋት የወጣ የኢንተር አሜሪካን ኮንቬንሽን (Inter-American Convention on the Prevention, Punishment and Eradication of Violence Against Women) ያለ ሲሆን በኮንቬንሽኑ እንደተደነገገው ጥቃት የአንዲትን ሴት “የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የባህል መብቶቿን በነጻ እና ሙሉ በሙሉ እንዳትጠቀም” እንደሚከለክላት በመገንዘብ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ለመቅጣት እና ለማጥፋት አወንታዊ እርምጃዎች እንዲወስዱ እና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ወይም መድሎዎች የሚያስከትሉትን ማህበራዊ እና ባህላዊ ጉዳዮችን ለመፍታት መንግስታት እርምጃዎችን በደረጃ እንዲወስዱ ግዴታ ጥሏል በማለት ባለሙያዋ አብራርተዋል።

ወደ ሃገራችን ስንመጣ ደግሞ የሴቶች መብት በኢትዮጵያ የህግ ስርዓት ያለው ስፍራ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንመለከታለን:: ኢትዮጵያ     የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ከማቋቋም ጀምሮ የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት መግለጫ(UDHR) ላይ በቀዳሚነት ከተሳተፉና ከፈረሙ ሃገራት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት  ትገኛለች::

ኢትየጵያ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ስምምነት፣ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አይነት ልዩነት ለማስወገድ የተደረገውን ስምምነት የፈረመች ሲሆን እ.ኤ.አ ሀምሌ 1980 ዓ.ም አለም አቀፉን በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሏዊ ልዩነት ለማስወገድ የወጣውን ስምምነት በመፈረም የሴቶችን መብት የሚያስከብሩ የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቃይታለች:: ከነዚህም መካከል በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ መንግስት ስለሴቶች መብት እውቅና እና ጥበቃ ያደረጉ ድንጋጌዎችን ስንመለከት በአንቀፅ 34 እና 35 ስር ወንዶች እና ሴቶች በጋብቻ አፈፃፀም፣ በጋብቻ ዘመንና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት እንዳላቸው ያስቀመጠ ሲሆን በፍቺ ጊዜም የልጆች መብትና ጥቅም እንዲከበር የሚያደርጉ ድንጋጌዎች እንደሚደነግጉ ያስቀምጣል:: ከዚህ በተጨማሪም የተሻሻለውን የፌደራል የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/92 ለሴቶች መብት ጥበቃ ካደረጉ ድንጋጌዎች ውስጥ በጋብቻ ወቅት ሁለቱም ተጋቢዎች ጋብቻን ለመመስረት ነፃ ፍቃዳቸውን መስጠት እንዳለባቸውና የተጋቢዎች እድሜ ለሁለቱም 18 ዓመት መሆኑ ተጋቢዎች የኑሮ ጫናን በእኩል ሀላፊነት እንዲጋሩ የሚያስችላቸው መሆኑንም ታሳቢ  ያደረገ ነው::

ሌላው በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 49/1 ስር እንደተደነገገው ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር፣ መተጋገዝ እና መደጋገፍ አለባቸው:: ይህም ሴቶች ተገቢውን ክብር የማግኘት መብት እንዳላቸው አመላካች ነው በማለት ባለሙያዋ አብራርተዋል::

ከነዚህ መብቶች እና መመሪያወች በተጨማሪም ሴቶች ከሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች መካከል በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መቀጠር አንዱ መብታቸው ስለመሆኑ የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 እና የአብክመ መንግስት ሰራተኞች አዋጅ 253/2010 የመንግስት ሠራተኛ ሴቶችን በስራ ላይ ያላቸውን መብትና ግዴታ የተመለከቱ ድንጋጌዎች አካቷል::

ለምሳሌ ሴት ሠራተኞች በእርግዝናቸው ጊዜ የህክምና ምርመራ ለማድረግ እና ሀኪም ፈቃድ ሲያዝላቸው ደሞዝ የሚከፈልበት ፈቃድ የማግኘት መብት አላቸው:: እንዲሁም በግል መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሴቶችን መብት የሚያስጠብቁ ድንጋጌዎች በአአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ውስጥ ተካተው እንደሚገኙ ባለሙያዋ አብራርተዋል:: ከዚህ በተጨማሪም በ1986 ዓ.ም ብሄራዊ የሴቶች ጉዳይ ፖሊሲ የወጣ መሆኑን  እና ፖሊሲው በሀገራችን በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ሴቶች ከባህልና ልማድ እንዲሁም በሌሎች ተደራራቢ ምክንያቶች ያለባቸውን ጫና እውቅና በመስጠት በቀጣይ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ መዘርጋት እንደሚገባዉ መሰረት ጥሏል በማለት የህግ ባለሙያዋ አውስተዋል::

ሴቶች በቅጥር ፣ በደረጃ እድገት፣ በዝውውር፣ በድልድል፣ በትምህርትና ሥልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው::

ነፍሰ ጡር የሆነችን የመንግሥት ሠራተኛ በቅጥር ወይም በደረጃ ዕድገት ከተመደበችበት የሥራ መደብ ወደ ሌላ የሥራ መደብ መድቦ ማሰራት የተከለከለ ስለመሆኑ፤ ሆኖም ለራሷ ጤንነት ወይም ለፅንሱ አደገኛ መሆኑ በሕክምና ማስረጃ ሲረጋገጥ ተስማሚ ወደ ሆነ የሥራ መደብ ወይም የሥራ ቦታ ተመድባ እንድትሰራ መደረግ እንዳለበት መመሪያው እንደሚያዝ ባለሙያዋ አውስተዋል::

በመሆኑም መላው ማህበረሰብ እነዚህ ህጎች እንዲከበሩ እና እንዲተገበሩ በማድረግ ሴቶች ከሚደርስባቸዉ አድልኦ፣ መገለል እና ጥቃት በማስቀረት እና ለመብታቸው በመታገል ለእህቶቻችን፣ ለእናቶቻችን እና ለልጆቻችን ብለን ህጉን እናስከብር:: ሴት የቤትና የሀገር መሰረት ናት ካልን ሴትን ማክበርና መብቷን ማስጠበቅ ሀገርን መስራት ነውና::

መረጃ

የኤሌክትሮኒክ ንግድ ዓይነቶች

ከንግድ ድርጅት ወደ ንግድ ደርጅት (Business to Business)

ይህ ግንኙነት በሁለት ንግድ ድርጅቶች መካከል የሚደረጉ ትልልቅ ግብይቶችን የሚመለከት ነው።

ከንግድ ድርጅት ወደ ሸማቾች (Business to Consumer)፡-

በንግድ ድርጅቶች እና በሸማቾች መካከል የሚደረግ ግብይት ነው።

ከንግድ ድርጅት ወደ መንግሥት (Business to Government)፡-

በድርጅቶች እና በመንግሥት አካላት መካከል የሚደረግ ግብይት ነው።

ከሸማች ወደ ሸማች (Consumer to Consumer)፡-

በግለሰብ ሸማቾች መካከል የሚደረጉ ግብይቶችን የሚመለከት ነው።

ከሸማቾች ወደ ንግድ ደርጅት (Consumer to Business)፡-

እያንዳንዱ ሸማች ምርቶቹን ወይም አገልግሎቶችን ለንግድ ድርጅቶች የሚሸጥበትን ግብይቶችን ያካትታል።

(ብርቱካን አትንኩት)

በኲር የታህሣስ  6  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here