አይረሴው መስዋዕትነት!

0
176

–     ጀኔራል ተሾመ ተሰማ እና ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ  በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ።

የወደብ አልባነታችን ጉዳይ ሲነሳ ቁጭት ከሚያድርባቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል የዚህ ፅሑፍ አዘጋጁ አንዱ ነኝ። ምክንያቱም የህይወት መስዋዕትነት ባልከፍልም በቀይባህር ዳርቻ ለሃገሬ ክብር ዘብ ቆሜ ነበር። ከተለያዩ የዓለም ሃገራት ተነስተው ወደ አሰብ ወደብ የሚጓዙ፤ ከአሰብ ወደብ ተነስተው ወደተለያዩ አቅጣጫዎች የሚገሰግሱ መርከቦች በዘመኑ ነፃ አውጭ ነን በሚሉ እና መንግሥት ወንበዴዎች በሚላቸው ኃይሎች እንዳይጠቁ በአነስተኛዋ የወደብ ስፍራ ፂኦ ግንባር /አሁን በኤርትራ የተካለለች/፣ ቀይባህር ዳርቻ በተጠንቀቅ ዘብ የቆመው 141ኛ እግረኛ ብርጌድ ሁለተኛ ሻለቃ አባል በመሆን እስከ 1981 ዓ.ም መጨረሻ እኔም እዚያው ነበርሁ። ለ54ተኛ ዙር የመኮንንነት ስልጠና ወደ ሁርሶ የጦር መኮንኖች አካዳሚ በማቅናቴ ነበር እኔና ቀይባህር የተነጣጠልነው። ትዝታው ግን ዛሬም ድረስ በቁጭት አብሮኝ ዘልቋል።

በዚህ እትም የታሪክ አምድ ደግሞ ሁኔታው ፈቅዶ ስለ ባህር በር ሲሉ በጀግንነት ስለተሰዉ ኢትዮጵያዊ ጀግኖች  የታሪክ መዛግብትን አጣቅሼ ከብዙ በጥቂቱ አነሳሳለሁ። “ሞት የተፈረደባቸው 17ሺህ የኢትዮጵያ ሠራዊት አይ ምፅዋ!” በሚል በታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ፣ በ1997 ዓ.ም ለህትመት የበቃውን የታሪካችንን መፅሐፍ ለዚህ ፅሑፍ ዋነኛ ምንጭ አድርጌ ተጠቅሜያለሁ።

ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሃገር ከሆነች የአባይን ውሃ ገድባ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት ታደርጋለች ብላ የሰጋችው ግብፅ ኢትዮጵያ ሰላም እንዳይኖራት የማድረግ ሴራን በተለያዬ መንገድ ስትፈፅም ቆይታለች፤ አሁንም ድረስ ከዚህ ድርጊቷ አልተቆጠበችም። በተለይም በመንግሥታቱ ማህበር /League of Nation/ የኤርትራን-ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን መዋሃዷን ለሚቃወሙ የኤርትራ አማፂ ቡድን ስልጠና በመስጠት እንዲደራጅ አድርጋዋለች።

ግብፅ ኤርትራ-ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሃድ በ1952 ዓ.ም ሲወሰን ድጋፍ ካደረጉ  የመንግሥታቱ አባል ሃገራት መካከል አንዷ ነበረች። ድጋፏ ግን ኢትዮጵያን ለመጥቀም አስባ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በኤርትራ በኩል የተለያዩ ግጭቶች ሲነሱ ድጋፍ በመስጠት፤ የኢትዮጵያን ሰላም የማሳጣት ሴራዋን ማስፈፀሚያ ለማድረግ ነበር። በዚህም የተነሳ ውህደቱን በመቃወም ለአመፅ የተነሳውን ጀብሃ ማሰልጠን እና መደገፍ ጀመረች።

በኤርትራ የጀመረው አመፅ አድማሱን እያሰፋ ቀጠለ። ኢትዮጵያም ከልማት ይልቅ በጦርነት እንድትጠመድ ሆነች።

የ1966ቱን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ የኤርትራ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ፤ የለውጡ መሪ ሻለቃ (በወቅቱ ማዕረግ) መንግሥቱ ኃይለማርያም እና የኤርትራው ተወላጅ አማን አምዶ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ጀምረው ነበር። ነገር ግን ወዲያውኑ በተፈጠረ “የሥልጣን ሽኩቻ” ምክንያት አማን አምዶን ተገደሉ፤ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታም መፍትሄ ሳያስገኝ ተቋጨ።

የኤርትራ ትግል 1967 ዓ.ም ከጀብሃ እጅ ወጥቶ ወደ ሻዕቢያ ተሸጋገረ። ከመቼውም ጊዜ በላይ ኤርትራውያን ወደ ግንባሮች ተቀላቀሉ። የእርስ በርስ ጦርነቱም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል አድማሱን አስፍቶ ቀጠለ።

ኢትዮጵያ በወቅቱ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ብትሆንም፤ ወደብ አልባ ግን አልነበረችም። የአሰብ እና ምፅዋ ወደቦች ባለቤት ነበረች። ይህ ግን ግብፅን እና አንዳንድ የአረብ ሃገራትን አላስደሰተም። በዚህ ምክንያት አማፂያንን በመደገፍ ኢትዮጵያ ሰላም እንዲርቃት የውጪ ሃይሎች በእጅ አዙር ጦርነቱን ተግተው ደግፈዋል፤ በዋናነት ታሪካዊ ጠላታችን- ግብፅ።

በኢትዮጵያ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት እና በሻዕቢያ ሃይሎች መካከል የነበረው የሶስት አስርት ዓመታት ፍጥጫ በማያወላዳ ሁኔታ ለሻዕቢያ በሚያመች መልክ የተቀየረው ከአፋአቤት ጦርነት በኋላ ነው። ሻዕቢያ በ1980 ዓ.ም አፍአቤት ላይ ያገኘው ድል ለምፅዋ መያዝ በር ከፍቷል።

የካቲት 1982 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሠራዊት እና በሻዕቢያ መካከል በቀይ ባህር አውራጃ፣ በምፅዋ ግንባር ከባድ ውጊያ ተካሂዷል። አስር ቀንና ሌሊት የፈጀ ሲሆን አይረሴ የወቅቱ ጀግና ኢትዮጵያዊያንን እና ድንቅ መስዋዕትነትንም በተግባር አሳይቷል።

በዚህ አይረሴ የምፅዋ ውጊያ፤ የወቅቱ የ6ኛ ነበልባል ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ፣ የ3ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ፣ የ6ኛ ክፍለ ጦር ፖለቲካ መምሪያ ኃላፊ ሻምበል ሸዋን ታዬ ዓለሙ ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል፤ በጠላት እጅ ከመማረክ ይልቅ ሞትን መርጠው ልክ እንደ አፄ ቴወድሮስ፤ አነሱም ምፅዋ ላይ ራሳቸውን ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ ሰውተዋል።

የኢትዮጵያውያን ጠንካራ ሃገራዊ ፍቅር በታየበት የምፅዋ ተጋድሎ ከ17ሺህ በላይ የወቅቱ ሃገር መከላከያ ሠራዊት የህይወት መስዋዕትነት፣ የአካል ጉዳት እና በአስገዳጅ ምርኮም ዘግናኝ ስቃይ ተቀብሎበታል። የዚህ አይሬሴ የጀግንነት ተጋድሎ ፊታውራሪ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ናቸው። የእኒህን ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የምፅዋ ጀግና ሙሉ ታሪክ በሌላ ጌዜ ይዘን የምንቀርብ መሆኑን እንገልፃለን። ለዛሬ ያልነው በዚሁ ተቋጨ፤ ቸር ይግጠመን።

ሳምንቱ በታሪክ

ኮከቡ አረፈ

የኢትዮጵያ በሔራዊ ቡድን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ እግር ኳስ ተጫዋች እና አሰልጣኝ የነበረው ኮከቡ መንግሥቱ ወርቁ ታህሳስ 7 ቀን 2003 ዓ.ም  በ70 ዓመቱ አረፈ። መንግሥቱ ወርቁ በስድስት የአፍሪካ ዋንጫዎች የፍጻሜ ግጥሚያዎች የተሳተፈ ሲሆን፣ በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ግብፅን 4 ለ 2 አሸንፋ ዋንጫ እንድታገኝ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረና በዚሁ በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሦስት ግቦችን በማስቆጠሩም የኮከብ ግብ አግቢነት ክብር አግኝቷል፡፡

መንግሥቱ ወርቁ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ በመጫወት በማንኛውም የሀገራችን ተጫዋቾች ያልተደፈሩ ክብረወሰኖች ባለቤት ነው። መንግሥቱ፣ ለሀገሩ በተሰለፈባቸው 98 ጨዋታዎች 61 ግብ በማስቆጠር የብሔራዊ ቡድኑ ባለክብረወሰን ለመሆን የቻለ ነው::የእግር ኳስ ህይወቱን በወርቃማው ዘመን ያሳየው መንግሥቱ ሀገራችን በአፍሪካ ዋንጫ ያላት ታሪክ ደማቅ እንዲሆን ካደረጉት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው::ምንጭ፡- “መንግስቱ ወርቁ የእግር ኳስ ዕንቁ” በዶክተር ሰሎሞን በርሄ

 

ኮፊ አናን ተሾሙ

ጋናዊው ኮፊ አናን ታህሳስ 8 1988 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሾሙ፡፡

እስከ ፈረንጆቹ 2006 ድረስ በዋና ጸሐፊነት አገልግለዋል፡፡ በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ኮፊ አናን ባደረባቸው ህመም በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓመት በሞት ተለይተዋል ሲል የዘ ኢልደርስ  መረጃ ያሳያል።

 

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የታህሣስ  6  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here