ሙስና ጠንክሮ መሥራትን የሚኮንን፣ ሳይሠሩ መብላትን የሚያጀግን፣ የአጋርነትን ሞራል የሚሰብር፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እና አጠቃላይ ዘላቂ ልማትን የሚገታ ነው። ሙስና በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ሀጢያት፣ በዓለማዊ ሕጎች ደግሞ ወንጀል የሆነ፣ በማህበረሰቡ ቀደምት ወግ እና ባሕሎችም የተነወረ እና የተወገዘ ተግባር ሲሆን በአስነዋሪ መገለጫነቱም ይታወቃል። ሙስና በጥቂት ግለሰቦች የተበላሸ ተግባር ብዙኃኑን የሚበክል ድርጊት ነው።
የሙስና መገለጫዎች ውስብስብ እና አያሌ ቢሆኑም በጥቂቱ ሙስና ኢ–ፍትሐዊነት፣ የግል ጥቅም አሳዳጅነት፣ ሥርዓተ ነውረኝነት፣ የአድልዎ እና የሞራል ዝቅጠት፣ ሳይለፉ እና ሳይሠሩ መክበርን መፈለግ፣ ወንጀልን እና ብልሹ ተግባራትን ወደ ሌሎች እንዲጋባ እና ተተኪዎች እንዲለማመዱት የሚያደርግ የሃገርን እና የትውልድን ዕድገት እና ተስፋ የሚያጨልም ዳፋውም ለሁሉም ዜጋ የሚተርፍ ጽዩፍ ተግባር ነዉ።
‘’ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል‘’ በሚል አባባል ሙሰኞችን በተረትና ምሳሌዎቻችን ማድነቅ እና ማበረታታት ሙስናን ለመግታት በሚደረግ ጉዞ እንደ እንቅፋትም ጭምር ነው፡፡
ሙስና በዓለማችን እና በሃገራችን በአሁኑ ሰዓት በእጅጉ ተስፋፍቶና መገለጫዎቹንም እየቀያየረ በመንግሥትም ይሁን በግል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ መደበኛ የሆነውን አገልግሎት ለማግኘት የእጅ መንሻ መስጠት እየተለመደ እና ባሕል እየሆነ የመምጣቱ ጉዳይ ያሳስባል፤ ስጋትንም ፈጥራል።
ሙስና ሀገር በሰላም እጦት፣ በፍትሕ መጓደል፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በስደት እና በኢኮኖሚያዊ ብክነት ውስጥ እንድታልፍ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ይህ ተግባር ይበልጥ ተስፋፍቶ የከፋ ችግር እንዳያስከትል ሙስናን መቃወም የሁላችንም ተግባር እና ኃላፊነት ሊሆን ይገባዋል።
ሙስና በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ከተጽዕኖው ለመውጣት ትውልድን በሥነ ምግባር መገንባት ጉዳይ ለነገ የማይባል ተግባር ነው። ለዚህም “ትውልድን በሥነ ምግባር፣ ተቋምን በአሠራር” በሚል መሪ መልዕክት ታስቦ የዋለው የዘንድሮው የጸረ ሙስና ቀን መሪ መልዕክት ያሳያል። ይህም ሙስናን (ሌብነትን) በዘላቂነት ለማስወገድ ቀዳሚው ጉዳይ የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ መሆኑን አጽንኦት የሚሰጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ወላጅ ልጆቹ የራሳቸው ያልሆነን ጥቅም የማይፈልጉ እንዲሆኑ አድርጎ የማሳደግ ግዴታ እንዳለበት የሚጠቁምም ነው፡፡
ለተቋም ሪፎርም ትኩረት በመስጠት እና በማዘመን አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እየተሰጡ ያሉበት የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት ሙስናን ለማስቀረት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ተገልጋዮች ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ተገልጋዩ እርካታ እንዲያገኝ ከማድረጋቸውም ባለፈ ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ ሙስናን ለመቀነስ ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖራቸዋል፡፡
በመሆኑም ብልሹ አሠራሮችን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ይረዳ ዘንድ ተቋማት ለሕዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ሁሉም ተቋማት የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሠራርን በመተግበር ሙስናን በማስቀረት እና ዘመናዊነትን በመላበስ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
በኲር የታህሣስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


