የ13 ወር ባለጸጋዋ ሀገራችን ዓመቱን ሙሉ የሚጎበኙ መዳረሻዎች ባለቤትም ናት፤ ከታኅሳስ ጀምሮ ያሉ ሦስት ወራት ደግሞ በተለይ ለአማራ ክልል ልዩ ገጽታ አላቸው:: የልደት (ገና፣ ጥምቀት፣ የአገው ፈረሰኞች፣ አስተሪዮ፣ የመርቆሪዮስ በዓላት ደግሞ የእነዚህ ወራት ልዩ መገለጫዎች ናቸው።
ቱሪዝም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የ10 በመቶ ወይም የ10 ነጥብ ዘጠኝ ትሪሊዮን ዶላር አበርክቶ እንዳለው የዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ካውንስል እ.አ.አ 2024 መረጃ ያመላክታል።
ከፍተኛ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል፤ ለአብነትም እ.አ.አ በ2024 ብቻ ለ357 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ምክንያት መሆኑን መረጃው ጠቁሟል::
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ቱሪዝም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ ድርሻ እንዳለው አስታውቋል::
የአማራ ክልልም በቱሪዝም ዘርፍ ለሀገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ካሉ ክልሎች መካከል በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው:: ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ፣ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሃብቶች መገኛ እና ሁሉንም አይነት የቱሪዝም ዘርፎች የያዘ ክልል ነው:: ሃይማኖታዊ በዓላት እና ባሕላዊ ክዋኔዎች ደግሞ ዋናዎቹ የቱሪዝም ጸጋዎች ናቸው::
ከታኅሳስ 29 ቀን ጀምሮ በድምቀት የሚከበሩት ሃይማኖታዊ በዓላት እና ባሕላዊ ክዋኔዎች ከግለሰብ እስከ መንግሥታዊ ተቋማት ድረስ በጉጉት የሚናፈቁ ሁነቶች ናቸው:: ለዚህም ከክልል ጀምሮ የበዓሉ ቀጥተኛ ባለቤት የሆኑ አካባቢዎች ቅድመ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል::
በታኅሳስ ወር ከሚደምቁት ከተሞች መካከል ላልይበላ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፤ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናቱ፣ የቀሳውስቱ የቤዛ ኩሉ ዓለም ዝማሜ፣ አጠቃላይ የበዓሉ ሃይማታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች ደግሞ የከተማዋ የድምቀት ማዕከላት ናቸው::
በከተማዋ የላልይበላ ሆቴሎች ማኅበር የቦርድ አባል አቶ አበበ ደምሳሽ የልደት (የገና) በዓል ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል:: ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ጀምሮ በሰሜኑ ጦርነት እና አሁንም ድረስ የቀጠለው ግጭት ላልይበላ በሰላሟ ጊዜ ታስተናግድ የነበረውን እንግዳ እንድታጣ አድርገዋት መቆየቷን አስታውሰዋል::
አቶ አበበ እንዳሉት የላልይበላ ሆቴሎች እና ማኅበረሰብ መሠረታቸው ጎብኚዎች ናቸው:: ይሁን እንጂ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶች በመቀነሳቸው ከተማዋ ተጎጂ ሆናለች:: ይህም ብዙ ሆቴሎች ሥራ እንዲያቆሙ በማድረጉ የፈጠሩት የሥራ ዕድልም እንዲቆም ማድረጉን ነው ያስታወሱት::
ከ50 በላይ ሆቴሎች በከተማዋ መኖራቸውን ያስታወቁት አቶ አበበ፣ አብዛኛዎቹ ለገና በዓል የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት:: በሆቴሎች አገልግሎት ማቆም ምክንያት የተቋረጠው የሥራ ዕድል እንደሚመለስም ተስፋ ያረጉት አቶ አበበ ሌሎች ዘርፎችም እንዲነቃቁ ያግዛል ብለዋል::
የቅዱስ ላልይበላና አካባቢው ቱሪስት አስጎብኚ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ እስታሉ ቀለሙ ከኮቪድ 19 መከሰት በኋላ ያጋጠመው የሰላም እጦት የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳው አስታውሰዋል:: ቱሪዝም በተለይ ለላልይበላ እና አካባቢው ማኅበረሰብ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን በማንሳት በዘርፉ የደረሰው ጉዳት ደግሞ ማኅበረሰቡን ለከፋ ችግር እንደዳረገው ነው የጠቆሙት::
ወቅታዊ የጸጥታ ችግሩ መፍትሔ አግኝቶ እና ቱሪዝሙ አገግሞ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት እንዲመለስ አስጎብኚ ማኅበሩ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል:: የጎብኚዎች ፍሰት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአንጻራዊነት እየተሻሻለ መምጣቱንም አስታውሰዋል::
ላልይበላ ከ160 የሚበልጡ አስጎብኚዎች ያሉባት የጎብኚዎች መዳረሻ ናት ያሉት አቶ እስታሉ፣ ማኅበሩም ልደትን በላልይበላ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል:: ከከተማዋ ውጭ በርካታ የመስህብ ሀብቶች መኖራቸውን ያነሱት ሰብሳቢው፣ ማኅበሩ ደግሞ የእንግዶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል ብለዋል::
መንግሥት እና ብዙኃን መገናኛዎች አካባቢው ለጎብኚዎች ዝግጁ እና የሰላም ሁኔታውም በአንጻራዊነት የተሻለ መሆኑን እንዲያሳውቁ ጠይቀዋል::
የላልይበላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሳይ ወዳጄ በላልይበላ የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በድምቀት ለማክበር የመስተንግዶ፣ የጤና፣ የሰላም እና ሌሎች ዐቢይ እና ንኡሳን ኮሚቴዎችን በማዋቀር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል:: እንግዶች የሚያርፉባቸውን ቦታዎች የማመቻቸት፣ የፅዳት፣ የውኃ እና የመብራት ተቋማትን ዝግጁ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል:: ሕዝቡም እንግዶችን ተቀብሎ እግር አጥቦ እና ስሞ ያለውን አካፍሎ ማስተናገድ የቆዬ ባሕሉ መሆኑን በማንሳት ዘንድሮም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል::
ሌላው በጥር ወር ከሚደምቁት ከተሞች መካል ጎንደር በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፤ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የሚመጡ ጎብኚዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ ዓለም አቀፍ ቅርስ አሥተዳደሪ ጌታሁን ስዩም አስታውቀዋል::
ጎንደር ከተማን ከሌላው ጊዜያት ለየት የሚያደርጋት የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የአብያተ መንግሥታቱ ጥገና መጠናቀቁ ነውም ብለዋል:: ይህም ከተማዋን ልዩ ገጽታ አጎናጽፏታል ነው ያሉት:: ይህም የጥምቀት በዓልን ተንተርሶ የሚመጡ ጎብኚዎችን በአግባቡ በማስተናገድ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል::
በ2018 ዓ.ም 19 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን በመሳብ 15 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበበ እምቢያለ አስታውቀዋል:: አሁናዊ የቱሪዝም ፍሰቱ መሻሻል እየታየበት መሆኑንም በማንሳት ለአብነትም በሩብ ዓመቱ ብቻ (ከሀምሌ 01/2017 – መስከረም 30/2018) ሦስት ሚሊዮን ጎብኚዎች የክልሉን የመስህብ ሀብቶች መዳረሻቸው እንዳደረጉት ጠቁመዋል::
ልደትን በላልይበላ ጀምሮ እስከ የካቲት አጋማሽ የሚከበሩ በዓላትን ለመታደም ክልሉን መዳረሻቸው ለሚያደርጉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተሻለ መንገድ ለማስተናገድ ተጨማሪ የማረፊያ ቦታ ማዘጋጀትን ጨምሮ የተሻለ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል::
ብዙ ጎብኚዎች ይመጣሉ በሚል አዲስ የዋጋ ተመን ማውጣት ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው አቶ አበበ አስታውቀዋል:: ሆቴሎችን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች እና ለእንግዶች ታስበው የተከፈቱ ተቋማት በመደበኛው መሸጫ ዋጋ ብቻ ምርቶቻቸውን እንዲያቀርቡ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል::
በክልሉ ከ400 በላይ አስጎብኚዎች ይገኛሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፣ እንግዶችን በአግባቡ ተቀብለው ማስጎብኘት እንደሚኖርባቸው ተናገግረዋል:: ለአገልግሎት የሚከፈለውም ቢሮው ባወጣው ተመን መሠረት እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት::
የጥምቀት በዓል የክልሉን የመስህብ ቦታዎች በሰፊው ለማስጎብኘት ዕድል ከሚፈጥሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ዋናው ነው:: በዓሉ በሁሉም አካባቢዎች ቢከበርም በጎንደር፣ በባሕር ዳር እና በሰሜን ሸዋ ዞን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኢራንቡቲ በልዩ ድምቀት ይከበራል:: በዓሉን በሰላም በማክበር ቱሪዝሙ እንዲነቃቃ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደ ሥራ መገባቱን አቶ አበበ ገልጸዋል::
ከሁለት ሚሊዮን በላይ እንግዶች ጥምቀትን በጎንደር ያከብራሉ ተብሎ እንደሚታሰብ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል:: በዓሉ ከአጼ ቴዎድሮስ የልደት ቀን (ጥር 06 ቀን) ጀምሮ በልዩ ልዩ ሁነቶች የሚደምቅ ሲሆን ይህም የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ትልቅ አቅም እንደሚሆን ነው ያስታወቁት:: ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች እና ሎጂዎች እንዲሁም ምሽት ቤቶች የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወኑ ናቸው::
ከጥምቀት ቀጥሎም የቃና ዘገሊላ በባሕር ዳር ይከበራል:: ከጥር 14 ቀን ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በጣና ሃይቅ ላይ የታንኳ ቀዘፋ ውድድር እንደሚካሄድም ጠቁመዋል:: ከዚህ በተጨማሪም በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የግዮን በዓል በድምቀት ይከበራል:: የአስተሪዮ ማርያም ክብረ በዓልም በምሥራቅ ጎጃም ዞን መርጡለማርያም፣ በሰሜን ጎንደር ደረስጌ ማርያም እና በደቡብ ወሎ ግሸን ደብረ ከርቤ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ስለመደረጉ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል::
የአገው ፈረሰኞች፣ የመርቆሪዮስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል (የፈረስ ጉግስን ጨምሮ)፣ የካቲት አጋማሽ ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ያሆላሎ ጨዋታ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት በትኩረት የሚከበሩ በዓላት ናቸው::
የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በክልሉ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን በመታደም ክልሉ ያለውን አስደናቂ የመስህብ ሀብት ለመጎብኘት በክልሉ ያሉት አራት የአየር ማረፊያዎች (ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ላልይበላ እና ኮምቦልቻ) መልካም አጋጣሚ አድርገው አንስተዋል::
ልደትን በላልይበላ እና ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናድ በመደበኛው የአየር ትራንስፖርት በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ በረራዎች እንዲኖሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል::
የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ከተሠሩ ሥራዎች ባለፈ የማኅበረሰቡ ውብ የእንግዳ አቀባበል ልዩ ትርጉም እንደሚኖረው በማንሳት ይህንንም ማጠናከር እንደሚገባ ነው የተናገሩት::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


