77 ዓመታትን ያስቆጠረው የሰብዓዊ መብቶች የቃልኪዳን ሰነድ የጸደቀው በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር ታህሣሥ 10 ቀን 1948 በተባበሩት መንግ|ሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ነበር:: የጸደቀበት ቀንም በየዓመቱ የሰብዓዊ መብቶች ቀን ተብሎ ይከበራል:: ሰብዊ መብቶች በፓሪስ ጉባኤ ሲፀድቁ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠበቁ የእያንዳንዱን ግለሰብ መብትንና ነፃነትን የሚገልፁ 30 አንቀጾች ተካተውበት ነበር::
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የሕግ ክፍል ባለሙያ አቶ ደመቀ ይብሬ ለበኩር ጋዜጣ በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ የሰብዓዊ መብቶች ጅማሮ ከሃይማኖቶች አስተምህሮ እና ከጥንታዊ የሐሙራቢ ደንቦች የመነጩ መሆናቸውን መረጃዎችን ዋቢ አድርገው አስረድተዋል:: ከ6ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደ ማግና ካርታ እና የአሜሪካ የመብቶች ረቂቅ (U.S Bill of Rights) ያሉ የተለያየ ይዘት ያላቸው የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች እንደነበሩ ያነሱት ባለሙያው የሰብዓዊ መብት እንደ አንድ አጀንዳ (ጉዳይ) ራሱን ችሎ መቆም የቻለው ግን ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ስለመሆኑ አንስተዋል::
በአውሮፓ የአናሳ መብቶችን ለመጠበቅ በሚደረግ ጥረት በሀገራት መካከል ተከታታይ ግጭቶች ይደረጉ ነበር:: በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ጣልቃ ገብነት እንዲኖርና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ሥርዓት እንዲዘረጋ አስገድዷል::
የሰብዓዊ መብቶች ምንነት
የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት “ሰብዓዊ” ማለት ሰውን የሚያመላክት ሲሆን “መብት” የሚለው ደግሞ የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተጎናጸፈው ትክክለኛ፣ ሞራላዊ እና በሕግ ዕውቅና ያለውን የይገባኛል ጥያቄን የሚመለከት ነው:: ጽንሰ ሃሳቡ በዋናነት የሚያጠነጥነው የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ በተፈጥሮ የታደላቸው መሠረታዊና ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ ከተፈጥሮ የመነጩ መብቶች ባለቤት ስለመሆኑ ነው የሚያስገነዝበው::
የሰብዓዊ መብቶች ባሕሪያት
ሰብዓዊ መብቶች ሰዎች በተፈጥሮ ያገኟቸው የማይተላለፉ፣ የማይሸጡና የማይለወጡ መብቶች ናቸው:: እንዲሁም በማንኛውም የመንግሥት አካል ወይም በማንኛውም ሰው የሚሰጡ ሳይሆን የሰው ልጅ በተፈጥሮ የሚያገኛቸው በመሆኑ ተፈጥሮአዊ ናቸው::
አቶ ደመቀ እንዳስገነዘቡት ሰብዓዊ መብቶች በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰብዓዊ ፍጡራን ተመሳሳይ ክብርና ዕውቅና የሚሰጡ መብቶች ናቸው:: ለሁሉም የሰው ልጆች እኩል ተፈጻሚነት ያላቸው እና ከሰው ልጅ ጋር በሕይወት ዘመኑ አብረው የሚዘልቁ መብቶች ናቸው::
ሰብዓዊ መብቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው ከማንም ሰው ላይ ሊገፈፉ ወይም ሊገረሰሱ አይችሉም:: ሰብዓዊ መብቶች እርስ በእርስ የተደጋገፉ እና የተያያዙ በመሆናቸው በሰብዓዊ መብቶች ውስጥ ተዘርዝረው የሚገኙ ሁሉም መብቶች በአንድነት መከበር እና ዕውቅና ማግኘት አለባቸው:: መሠረታዊ በመሆናቸውም የእነዚህ መብቶች አለመከበር የሰው ልጆች ክብርና ሕይዎት ትርጉም አልባ ይሆናል ማለት ነው::
ሰብዓዊ መብቶች ለሰዎች በግል ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊከበሩላቸው የሚችሉ ሲሆን እነዚህን መብቶች የግል መብቶች(individual rights) ወይም የጋራ መብቶች (group rights) በማለት ማየት ይቻላል:: ለአብነትም በሕይወት የመኖር፣ የግል ነፃነት፣ የአካል ደኅንነት፣ ከኢሰብዓዊ አያያዝና ከባርነት የመጠበቅ፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የሥራ እና ትምህርት የመማር፣ የጤና አገልግሎት እና ደረጃውን የጠበቀ ኑሮ የመኖር መብቶች ሰዎች በግላቸው ሊከበሩላቸው የሚገቡ መብቶች ሲሆኑ ንፅህናውን በጠበቀ አከባቢ የመኖር፣ የባሕላዊ፣ ፖሊቲካዊ እና የኢኮኖሚያዊ ዕድገት መብቶች ደግሞ ሰዎች በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ በመኖራቸው እንደ ማሕበረሰብ አባል ሊያገኟቸው የሚችሉ የጋራ መብቶች ናቸው:: እነዚህም ሰዎች ባሕላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና ሃይማኖታቸውን በጋራ ለማንፀባረቅ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ናቸው::
የሰብዓዊ መብት ትውልዶች (generations of human rights)
አቶ ደመቀ እንዳብራሩት ሰብዓዊ መብቶች በሦስት ትውልዶች ውስጥ አልፈዋል:: የመጀመሪያው በአብዛኛው የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች እንዳይጣሱ የሚከላከሉና በ17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ ዘመናት በእንግሊዛዊያኑ የፖለቲካ ፈላስፎች (ቶማስ ሆብስ፣ ጆን ሎክ እና ሚል) የዳበሩ ናቸው:: በአጠቃላይ የባለመብቱ ነፃነት ውስጥ ጣልቃ ገብነትን የሚከላከሉ ናቸው:: ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ተደርጎ የሚጠቀሰው ሕግ አውጪው የመናገር ነጻነትን እንዳይገድብ የከለከለው የአሜሪካ የመጀመሪያው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ነው::
ሁለተኛው የሰብዓዊ መብቶች ትውልድ ደግሞ በዋናነት አዎንታዊ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ባሕላዊ መብቶችን የሚመለከት ሲሆን የትምህርት፣ የምግብ፣ የሕክምና መብቶች ይገኙበታል።
ሦስተኛው የሰብዓዊ መብቶች ትውልድ ደግሞ በዋናነት የሚያተኩረው የቡድን መብቶች ላይ ነው። በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች የቃል ኪዳን ሰነድ አንቀጽ 28 ላይ “እያንዳንዱ ሰው በዚህ የቃል ኪዳን ሰነድ የተጠበቁት መብቶቹ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያስችል የማሕበራዊና የዓለም አቀፋዊ ደኅንነት (ሰላም) መብት አለው” በሚል ተቀምጧል። እነዚህ የጋራ መብቶች የማሕበራዊና የኢኮኖሚያዊ ዕድገት መብቶችን፣ እንዲሁም ከምድር እና ከጠፈር ሀብቶችን የመጠቀምና የመሳተፍ መብቶችን፣ ሳይንሳዊና ቴክኒካዊ የሆኑ መረጃዎችን የማግኘት መብትን ያካትታሉ። በተለይም ለሦስተኛው ዓለም ሀገራት ጠቃሚ ናቸው።
በተጨማሪም ጤናማ የመኖሪያ አካባቢ፣ ሰላምና በአደጋዎች ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ የማግኘት መብቶችንም ያካተቱ ናቸው:: ባለሙያው ስለመብቶች ምንነት ካስገነዘቡ በኋላ “መብቶቻችንን ለይተን አውቀን በሕጋዊ መንገድ ማስከበር፣ የሌሎችን መብት ደግሞ ማክበር የኛ ፈንታ ነው” ብለዋል የሕግ ባለሙያው አቶ ደመቀ::
ሰብዓዊ መብቶች እና የመንግሥታት ኃላፊነት የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት ሀገራት ለሰብዓዊ መብቶች ተፈፃሚነት ከፍተኛ ሚና እና ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን ኃላፊነታቸውን ወይም ያለባቸውን ግዴታ በአጠቃላይ በሦስት አስቀምጠዋቸዋል።
የመጀመሪያው ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር ግዴታ (obligation to respect) ነው:: መንግሥታት በሰብዓዊ መብቶች ተጠቃሚነት ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ (refrain from interfering with the enjoyment of the right) እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው::
ሁለተኛው ሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅ ወይም የማስከበር ግዴታ (obligation to protect) ነው። ይህም መንግሥት ሌሎች ሰዎች በሰዎች የሰብዓዊ መብት ተጠቃሚነት ጣልቃ እንዳይገቡ የመጠበቅ ወይም የመከላከል ግዴታ (prevent others from interfering with the enjoyment of the right) እንዳለበት የሚያሳይ ነው::
ሦስተኛው ደግሞ ሰብዓዊ መብቶችን የማሟላት (obligation to fulfill) ሲሆን መንግሥታት የኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ባሕላዊ መብቶችን ተፈፃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ እንዳለባቸው ያመላክታል::
ሰብዓዊ መብቶች የሰው ልጆች ሰው በመሆናቸው ብቻ ያገኟቸው መብቶች በመሆናቸው ሳይሸራረፉ ሊከበሩ ግድ ይላል:: በመሆኑም ለመብቶቹ መከበር መንግሥትም እነዚህን መብቶች የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ዕውቅና እና ተቀባይነት የሚጀምረው የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ በሆነው በኢ.ፊ.ዴ.ሪ. ሕገ-መንግሥት ነው:: በኢፌዴሪ ሕገ – መንግሥት በርካታ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ተካተዋል። ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በመፈረም የሀገሪቱ ሕግ አካል አድርጋለች:: በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት እና ነጻነት ድንጋጌዎች ሀገሪቱ ፈርማ ካጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ መተርጎም እንዳለባቸው በሕገ – መንግሥቱ ተደንግጓል:: እንዲሁም በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌደራል እና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚ እና የዳኝነት አካሎች በሕገ መንግሥቱ የተካተቱ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የማክበር እና የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸዉ በግልጽ ተደንግጓል::
ዩ ኤስ ኒውስ /www.usnews.com/ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው በተለያዩ ዓለም አቀፍ አመልካቾች እና ሪፖርቶች ላይ በመመስረት፣ በርካታ የኖርዲክ(ኖርዌይ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ስዊዲን፣ አይስላንድ) እና የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ሰብዓዊ መብቶችን በመጠበቅ እና በመተግበር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ:: ለአብነትም አይስላንድ፣ ዴንማርክ እና ኢስቶኒያ የሰብዓዊ መብቶች እና የሕግ የበላይነት አፈፃፀማቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው ድረ ገጹ የጠቀሰው::
በተጨማሪም ኖርዌይ፣ ፊላንድ፣ እና ስዊዘርላንድም በሰብዓዊ እና በዴሞክራሲ መብቶች አተገባበራቸው የተሻሉ የሚባሉ ሀገራት ናቸው:: አብዛኛዎቹ የአፍሪካ(ሱዳን፣ኤርትሪያ ..)እና የእስያ ሀገራት(ኖርዝ ኮሪያ፣ ቻይና…) ደግሞ በሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ዙሪያ ደካማ እንደሆኑ ሂዩማን ራይትስዎች ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል::
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች እነማን ናቸው?
ኢትዲፌንደር(www.ethdefenders.org) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው “የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች” ተብለው የሚገለጹት በግል ማንነታቸው፣ ባሕሪ ወይም የማንነታቸው መገለጫ በሆኑ የወል መጠሪያዎች ሳይሆን በሰላማዊ መንገዶች ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበርና ለማስጠበቅ በሚያደርጓቸው ጉልህ ተግባራት ወይም ሥራዎች ብቻ የተመሠረተ ነው::
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ተብለው የሚጠቀሱትም እንደ ጠበቃ፣ ጋዜጠኛ፣ ፖሊስ፣ የማሕበረሰብ አንቂ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ወይም መብት ባለሙያ፣ የሕክምና ባለሙያ እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የማሕበረሰቡ አባላት ወይም ማንኛውም ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋፅኦ የሚያደረጉ ግለሰቦች፤ እንዲሁም እንደ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅት ወይም የሠራተኛ ማሕበራት ሊሆኑ ይችላሉ።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


