በ1928 ዓ.ም በጅጅጋ ከተማ የተወለዱት ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካገኙ በኋላ በአሜሪካ ሀገር ከሚገኘው ጆን ሆብኪንስ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
ከሀገረ አሜሪካ እንደተመለሱም በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (የቀድሞ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) በኃላፊነት ማገልገል ጀምሩ። በዚህ ጊዜ ነበር የኢትዮጵያን ባዮፓቶሎጂ ተቋም ያቋቋሙት፤ ተቋሙም እስከ 1969 ዓ.ም አገልግሎት ሲሠጥ ቆይቷል። ይሄንን አገልግሎታቸውን ታሳቢ በማድረግ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በስማቸው ዶክተር አክሊሉ ለማ ፓቶባዮሎጂ ማዕከልን ሰይሞላቸዋል።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የወንዝ ውኃ ተጠቃሚ በነበረበት ወቅት ህብረተሰቡ በብዛት በቢልሃርዚያ በሽታ ይጠቃ ነበር። ቢልሃርዝያ ሺስቶሶማ በሚባሉ የደም ወስፋቶች ደም ውስጥ በመገኘት የሚመጣ የሰው በሽታ ነው። በሽታው ሰውን የሚይዘው ሰርኬርያ የሚባሉት ትሎች ሰው ሲዋኝ ወይም በባዶ እግሩ ውኃው ውስጥ ሲሄድ ቆዳን በመብሳት ወደ ሰውነት ስለሚገቡ ነው።
በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ልክ እንደሳሙና በሰፊው ለልብስ ማጠቢያነት የሚያገለግለው እንዶድ አብዛኛውን ጊዜ በወንዝ ዳርቻዎች ይበቅላል፤ ከተክሉ የሚገኘው ጭማቂ ወይም ፍሬው ለቢልሃርዝያ በሽታ የሚዳርገውን ተውሳክ የሚያስጠልለውን ቀንድ አውጣ ስለሚገድል ለመድኃኒትነት ያገለግላል፤ ፕሮፌሰር አክሊሉ ለሥራ ጉብኝት ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በሚዘዋወሩ ጊዜ ሰዎች በእንዶድ የሚያጥቡበት አካባቢ ብዙ ቀንድ አውጣዎች ሞተው በማየታቸው እንደመነሻ ሃሳብ በመውሰድ ከዶክተር ለገሠ ወልደዮሐንስ ጋር በመተባበር ለ30 ዓመታት ምርምር አካሄዱ። ቀንዳውጣን መግደል የሚችል “እንዶድ 44” የተባለ ማጥፊያ መድሀኒትም ለማግኘት ቻሉ።
ፕሮፌሠር ኣክሊሉ ለማ እንዶድ ቀንድ አውጣዎችን መግደል ስለሚችል፤ በሽታውን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ስለደረሱበት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ፕሮፌሰር አክሊሉ ስለ እንዶድ ጥቅምና የውኃ ትላትል መግደል ችሎታ በማግኘታቸው በ 1966 ዓ.ም እና በ 1986 ዓ.ም ከባልደረቦቻቸው ጋር የአሜሪካ የፈጠራ ባለቤትነት አግኝተዋል፤ የእንዶድ ማዕከልም አቋቁመዋል።
ስለ እንዶድ ምርምር ለብዙ ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስላደረጉት ኣስተዋጽዖ ሽልማት በ1981 ዓ.ም ከስዊድን ሀገር ተሰጥቷቸዋል።
ልጆች፣ በዓለማችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዲማቅቁ የሚያደርጉ በሽታዎችን፣ በሺህዎች የሚቆጠሩትን እንደዘበት የሚያረግፉ ተውሳኮችን ለመርታት ሳይንሳዊ ምርምር ወሳኝ ድርሻ አለው። ምርትን ለማሳደግ፣ የምድር እና የጠፈርን ውስጠ-ምሥጢር ለመበርበር፤ የሕብረተሰብን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሳይንስ አስተዋፅዖ እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም።
ለሀገራችን ኢትዮጽያ በ 1960ዎቹ አካባቢ የሳይንስ አካዳሚ ያስፈልጋታል በሚል የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚን ከጠነሰሱት ጠንካራ ሰዎች መካከል ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ አንዱ ናቸው። ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ መጋቢት 27 ቀን 1990 ዓ.ም በሀገረ አሜሪካ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፤ አስክሬናቸውም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በክብር አርፏል።
ምንጭ፡- ሰዋሰው፡፡
ተረት
ሚጡ
ሚጡ ትንሽ ልጅ ናት:: አራት ዓመቷ ነው:: ትምህርት ቤት መሄድ አልጀመረችም፤ በቤተሰቦቿ ግቢ ውስጥ ስትጫወት ትውላለች፡ ፡ ቤተሰቦቿ በሌሉ ቀን ሚጡ በግቢው ውስጥ እየተዘዋወረች አበቦችን ትጐበኛለች::
ከዕለታት አንድ ቀን ሚጡ በአበቦች ላይ የሚበሩ እንግዳ አካላት አየች:: እነዚህ ውብ አካላት ምን ይሆኑ ብላ ራሷን ጠየቀች:: ቀስ ብላም ወደ እነርሱ ተጠጋች፤ “ሆድዬ ስምሽ ማነው ከወዴት ነው ወደኛ ግቢ የመጣሽው?” ብላ ሚጡ አካሏን ጠየቀቻት:: “ስሜ ቢራቢሮ ይባላል:: የመጣሁት ከሩቅ ሀገር ነው:: የእናንተ ግቢ ደስ ሰላለኝ ነው ጐራ ብዬ የጐበኘሁት” ስትል በራሪዋ መለሰች:: “በጣም ታምሪያለሽ:: የኛ ግቢ አበቦችን በውበት ትበልጫለሽ፤ እስከመቼ ድረስ እዚህ ግቢ ትቆያለሽ?” ብላ ጠየቀቻት::
“ለነገሩ እቸኩላለሁ፤ ብዙ ሥራ አለብኝ፤ የግቢውን አበባ ጐብኝቼ እንደጨረስኩ መሄዴ አይቀርም። ደሞ ሌላ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ” አለች ቢራቢሮ:: “እባክሽ አትሂጂ ከእኔ ጋር እዚሁ እንጫወታለን:: ልዩ ልዩ አበቦች እንዲተከሉልሽ ለወላጆቼ እነግራቸዋለሁ:: ስላንቺ ውበትና ጥሩነትም አጫውታቸዋለሁ:: ደግሞም ጓደኛ ስለሌለኝ ጓደኛሞች እንሆናለን:: ቢራቢሮዬ ውድድ አደርግሻለሁ እሺ” “ጥያቄሽ መልካም ነበር፤ ብላቴናዎች ሁሉ ይወዱናል:: አብረናቸው እንድንሆን ይጠይቁናል። በዚህ ግቢ ብዙም አልቆይም፤ ይቅርታ ስለዚህ ግቢያችሁ በአበባ እስካጌጠ ድረስ ተመልሼ መምጣቴ አይቀርም” ብላ ቢራቢሮ ከጓደኞቿ ጋር ሆና ወደ ሌላ ግቢ በረረች:: ሚጡ ግን ድንገት ያገኘቻት ውብ ጓደኛዋ በመሄዷ አዘነች:: ነገር ግን ጓደኛዋን ዳግም እንደምታገኛት ስታስብ ተጽናናች::
ምንጭ፡-ከመዘገቡ ወልደገብርኤል የማር ወለላ ጣፋጭ ሀገራዊ የህፃናት ተረቶች ማሞ ቂሎና ሌሎችም መጽሐፍ የተወሰደ
ይሞክሩ
አንድ ሳምንት ስንት ሰዓታት አሉት?
ሲወለድ አረንጓዴ ሆኖ በእርጅና የሚቀላ ምንድን ነው?
ቆቧን አውልቆ አንገቷን እንቅ አድርጎ ሲይዟት የዓለምን ታሪክ የምትናገር ምንድን ናት?
መልስ
168
በርበሬ
እስክርቢቶ
ነገር በምሳሌ
- “ለሀምሳ ጋን አንድ አለሎ” -ጥራትና ብቃት ከሌለ ብዛት ብቻውን ዋጋ የለውም ማለት ነው፡፡
“ለሰው ቢነግሩት ለሰው” -ምስጢርህ ካንተ ከወጣ ለሌላም ይዳረሳል ማለት ነው።
“ተመርምሮ ይገኛል ቁም ነገር”
– በመመርመር ጠቃሚ ነገር ይገኛል ማለት ነው፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


