ግዙፉ የአፍሪካ ድግስ የአፍሪካ ዋንጫ ትናንት ተጀምሯል። እ.አ.አ. በ2022 በኳታር ዓለም ዋንጫ ታሪክ የሠራችው እና ለአፍሪካ እግር ኳስ አዲስ ተስፋ የሆነችው ሞሮኮ ይህንን ታላቅ አህጉራዊ ድግስ እያስተናገደች ትገኛለች። 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከመደበኛ የእግር ኳስ ውድድርነት አልፎ አፍሪካ በዓለም አደባባይ ያላትን ገጽታ የምትቀይርበት ታላቅ መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህ ውድድር ከዚህ ቀደም በአህጉሪቱ ካየናቸው ውድድሮች በውድድር የጊዜ ሰሌዳ ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ፣ በተሳታፊዎች ስብጥር እና በፖለቲካዊ ትርጉሙ እጅግ የተለየ መሆኑ የዓለምን ትኩረት ስቧል። የካዛብላንካ፣ የራባት፣ የታንጂር እና የማራካሽ ስታዲየሞች ቀለማቸውን አድሰው አፍሪካውያን ወንድሞቻቸውን እጆቻቸውን ዘርግተው ተቀብለዋል።
አፍሪካ ዋንጫን በለመድነው የጥር እና የካቲት ወር ወይም ደግሞ በቅርብ ዓመታት በተሞከረው የሰኔ እና ሀምሌ ወር ከመመልከት ይልቅ ዘንድሮ የምንመለከተው ከገና እና ከአውሮፓውያን አዲስ ዓመት በዓላት ጋር የተያያዘ ነው። ይህ የጊዜ ለውጥ የመጣው ፊፋ በአሜሪካ፣ካናዳና እና ሜክሲኮ የሚያሰናዳው አዲሱ እና ግዙፉ የክለቦች ዓለም ዋንጫ በሰኔ ወር 2025 የሚደረግ በመሆኑ ነው። አፍሪካውያን ተጫዋቾች ያለ እረፍት ውድድሮችን እንዳያከናውኑ እና የአውሮፓ ክለቦች ተጫዋቾችን ለመልቀቅ እንዳያቅማሙ በማሰብ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ውድድሩን ወደ አውሮፓውያኑ የክረምቱ ወቅት አሸጋግሮታል።
አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሊጎች ለክረምት እረፍት (Winter Break) በሚዘጉበት ወቅት መደረጉ የዓለም እግር ኳስ ቤተሰብ ትኩረት ሙሉ በሙሉ በሞሮኮ ስታዲየሞች ላይ እንዲሆን ታላቅ እድል ይፈጥራል። ከዚህም ባሻገር ተጫዋቾች የረጅም የውድድር ዘመን ድካም ሳይጫጫናቸው በከፍተኛ የአካል ብቃት ላይ እያሉ የሚሳተፉበት በመሆኑ የዘንድሮው ውድድር በቴክኒክ እና በፍጥነት እጅግ የላቀ ተመልካችን ሳቢ እና ማራኪ እንደሚሆን ይገመታል።
ሞሮኮ ይህንን ውድድር እያስተናገደች ያለችው ከፖርቹጋል እና ስፔን ጋር በመሆን ለምታዘጋጀው የ2030 የዓለም ዋንጫ እንደ አንድ ትልቅ የብቃት መመዘኛ በመቁጠር ነው። እናም ዝግጅቷ ከአፍሪካ ደረጃ የዘለለ እና ከአውሮፓ እኩል የሚስተካከል መሆኑን በመክፈቻው ዕለት ተመልክተናል። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ደጋፊዎች እና ተጫዋቾች ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ለመሸጋገር አድካሚ የአውቶቡስ ወይም ውድ የአውሮፕላን ጉዞ አይጠብቅባቸውም። በሰዓት ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የሚምዘገዘገው እና አፍሪካ በኩራት የምትጠራው አል ቡራቅ የተሰኘው ፈጣን ባቡር ታንጂርን ከካዛብላንካ፣ ራባትን ከማራካሽ በደቂቃዎች በማገናኘት የመጓጓዣን ችግር ቀርፏል። በ2021 እ.አ.አ ካሜሩን እና በ2023 እ.አ.አ ኮትዲቫር ባስተናገዱት ውድድሮች ላይ ይስተዋሉ የነበሩት የትራንስፖርት መስተጓጎሎች በሞሮኮ መቀረፋቸውን የካፍ ኦላየን መረጃ ያስነብባል። ስታዲየሞቹም ቢሆኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ፣ ለተመልካች ምቹ ወንበሮች ያሏቸው እና ከአውሮፓ እኩል የቪዲዮ ረዳት ዳኝነት እና የግብ መስመር ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው መሆናቸው ውድድሩን በአውሮፓዊ ጥራት አስቀምጦታል። የሜዳዎቹ (Pitches) ጥራት በተለይ ኳስን መሰረት አድርገው ለሚጫወቱ (Possession-based) ቡድኖች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። ይህም የአፍሪካን እግር ኳስ ከጉልበት ወደ ታክቲክ እና ጥበብ የተቀላቀለበት ጨዋታ እንዲሸጋገር ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል።
በሜዳ ላይ በሚኖረው ፉክክር ረገድም የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የኃይል ሚዛን መቀያየርን የሚያሳይ አዳዲስ ክስተቶችን ይዞ ይመጣል የሚል እምነት አሳድሯል። የምዕራብ አፍሪካ ኃያላን የሆኑት ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ኮትዲቫርን የመሳሰሉ በሄራዊ ቡድኖች ጠንካራ ቡድን ቢገነቡም የሰሜን አፍሪካ ቡድኖችም በአየር ንብረቱ ተጠቃሚ በመሆን ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም በኳታር ዓለም ዋንጫ እስከ ግማሽ ፍጻሜ የተጓዘችው አስተናጋጇ ሀገር ሞሮኮ ይህን ዋንጫ ካላሳካች ወርቃማ ትውልዷ እንደከሸፈ ሊቆጠርባት ይችላል። አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጊ እንደ አሽራፍ ሃኪሚ፣ ሃኪም ዚየች እና ያሲን ቦኖ ያሉ ዓለም አቀፍ ኮከቦች እ.አ.አ ከ1976 በኋላ የጠፋውን የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ራባት ቤተመንግሥት ለመመለስ በትክሻቸው ላይ ትልቅ ጫና ተሸክመዋል። ሞሮኮ እንደ አዘጋጅነቷ ብቻ ሳይሆን እንደ አህጉሩ የልዕለ ኃያልነት ምልክትነቷ ዋንጫውን በቤቷ የማስቀረት ከፍተኛ ጫና እንደሚጠብቃት የካፍ ኦንላይን መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል ይህ ውድድር ለብዙ የአፍሪካ እግር ኳስ ንጉሦች “የመጨረሻው የዳንስ መድረክ” (The Last Dance) ሊሆን ይችላል። ግብጻዊው ኮከብ ሞሃመድ ሳላህ እና ሴኔጋላዊው ኮከብ ሳዲዮ ማኔ ምናልባትም ይህ የመጨረሻው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎአቸው ሊሆን ስለሚችል ህይወታቸውን ሰጥተው አጥንታቸውን ከስክሰው እንደሚጫወቱ ይጠበቃል። በተለይ ሞሃመድ ሳላህ በግል ክብሩ እና በክለብ ደረጃ ሁሉንም ቢያሳካም የአፍሪካ ዋንጫን አለማሳካቱ የሚፈጥርበት ቁጭት በሞሮኮ ሜዳዎች ላይ ሊታይ ይችላል።
ሌላው የአዳዲስ ሀገራት ብቅ ማለት እና የትናንሽ ቡድኖች ማደግ የዚህ ውድድር ሌላኛው አዲስ መልክ ነው። በማጣሪያ ጨዋታዎች እንደተመለከትነው በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ውጤትን በቅድሚያ መገመት ከባድ እየሆነ መጥቷል። እንደ ሞሪታኒያ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ጋምቢያ እና ሌሴቶ ያሉ ሀገራት የሚያሳዩት የተደራጀ የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለታላላቅ ቡድኖች የራስ ምታት መሆኑ አይቀርም። የምሥራቅ አፍሪካ እና የደቡብ አፍሪካ ቀጠና ሀገራት (COSAFA) ከምዕራብ አፍሪካውያን የበላይነት ለመላቀቅ የሚያደርጉት ትግልም በጉጉት ይጠበቃል።
የአየር ንብረቱ ሁኔታም የውድድሩን መልክ ከሚቀይሩት ምክንያቶች አንዱ ነው። አሁን ወቅቱ በሞሮኮ የክረምት ወራት ነው። ይህ ማለት የሙቀት መጠኑ ዝቅተኛ ነው፤ አልፎ አልፎም ዝናብም ሊኖር ይችላል። ይህ የአየር ሁኔታ በተለይ ከሰሃራ በታች ለሚመጡ እና ከፍተኛ ሙቀት ለለመዱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል። በሌላ በኩል ግን ቀዝቃዛው አየር ለጨዋታው ፍጥነት (Tempo) መጨመር አስተዋጽኦ ያደርጋል። በሞቃት አየር ውስጥ እንደሚታየው ተጫዋቾች ቶሎ ስለማይደክሙ ጨዋታዎች በ90 ደቂቃ ወይም በ120 ደቂቃ በተመሳሳይ ፍጥነት እና ጉልበት ሊቀጥሉ ይችላሉ። ይህ ሁኔታ ለአውሮፓ ሊግ ተጫዋቾች የሚመች ሲሆን የውድድሩን የቴክኒክ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው የካፍ ኦንላይን መረጃ ያስነብባል።
ውድድሩ ከእግር ኳስ አውድ ውጭ ትልቅ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ትርጉም አለው። ሞሮኮ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋን ለማነቃቃት እና የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ መዲና መሆኗን ለማረጋገጥ እየሰራች ነው። መንግሥቷ ለስፖርታዊ መሰረተ ልማት ያወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሀገሪቱ ያላትን ለስላሳ ኃይል (Soft Power) ለመገንባት ያለመ ነው። በውድድሩ ወቅት የሚጠበቀው በሚሊዮን የሚቆጠር የቱሪስት ፍሰት እና የቴሌቪዥን ተመልካች ቁጥር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ሆኖም ከወዲሁ የተስተዋለው የሆቴል እና የአገልግሎት ዋጋ ንረት ለአፍሪካ እግር ኳስ ደጋፊ ውድድሩን እስከመጨረሻው በቦታው ተገኝቶ ለመከታተል እንቅፋት ይሆናል የሚል ስጋት ፈጥሯል። ያም ሆነ ይህ ግን አፍሪካ እንዲህ ያለ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ውድድር ማዘጋጀቷ አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተቀባይነት ከፍ ያደርገዋል የሚል እምነት አሳድሯል።
በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 24 ሀገራት እየተሳተፉ ሲሆን ሞሮኮ፣ኮትዲቫር፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ እና ግብጽ ዋንጫውን ያነሳሉ ተብለው ሰፊ ግምት የተሰጣቸው ሀገራት ናቸው። ይህን ውድድር ግብጽ ሰባት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ባለክብረወሰን ናት። በሞሮኮ የሚካሄደው የ2025/26 የአፍሪካ ዋንጫ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን አሸናፊዋ አፍሪካ እንደሆነች የሚያመላክቱ ብዙ እውነታዎች አሉ።
ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም እስከ ስታዲየም ውበት፣ ከከዋክብት ብዛት እና ጥራት እስከ ታክቲክ ጥልቀት፣ ከትራንስፖርት ምቾት እስከ ደጋፊዎች ድባብ ድረስ ያለው ነገር ሁሉ የአህጉሪቱን እግር ኳስ እድገት የሚያሳይ ነው። ውድድሩ ከታህሳስ 12 እስከ ጥር 10 2018 ዓ.ም በተከታታይ ይደረጋል። ዓለም አፍሪካን በአዲስ ዓይን፣ በአዲስ ብርሃን ይመለከታታል። አፍሪካ ለዓለም እግር ኳስ ያበረከተችውን ስጦታ የምታከብርበት እና የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ የምታበስርበት ደማቅ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ በታሪክ መዝገብም ይሰፍራል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


