መልካም ትዳር የግለሰቦች ደስታ ብቻ ሳይሆን የሀገር ህልውና መሰረት ነው። ቤተሰብ የህብረተሰብ የመጨረሻውና ትንሹ አሃድ ነው ይባላል። ቤተሰብ የሀገር ፋብሪካ ነው። ዜጎች፣ መሪዎች፣ ሰራተኞች እና አሳቢዎች የሚቀረጹበት የመጀመሪያው ተቋም ቤተሰብ ነው። የዚህ ተቋም ጥንካሬ ደግሞ የተመሰረተው በባልና ሚስት መካከል በሚኖረው ጤናማ ግንኙነት ወይም መልካም ትዳር ላይ ነው።
ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙት ግሬይ ቻፕማን “ዘ ፋይቭ ላቭ ላንጉዌጅስ” ( አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች) በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አንድ ወሳኝ ፅንሰ ሀሳብ አስተዋውቀዋል። እሱም “የፍቅር ማጠራቀሚያ” (Love Tank) ነው። አንድ መኪና ያለ ነዳጅ እንደማይሄድ ሁሉ፣ ትዳርም ባልና ሚስት እርስ በእርሳቸው በየጊዜው ፍቅርን ካልሞሉበት ሊቀጥል አይችልም።
ቻፕማን እንደሚሉት ባልና ሚስት የትዳር አጋራቸውን የፍቅር ቋንቋዎች (ማበረታቻ፣ የአብሮነት ጊዜ፣ ስጦታ፣ የአገልግሎት ድርጊት፣ ወይም አካላዊ ንክኪ) ለይተው ሲያውቁና ሲተገብሩ፣ በቤቱ ውስጥ ያለው ስሜታዊ የአየር ንብረት ይቀየራል።
ወላጆች እርስ በእርስ ሲዋደዱና የፍቅር ታንካቸው ሲሞላ፣ ልጆች ደህንነት ይሰማቸዋል። በፍቅር የተሞላ ቤት ውስጥ የሚያድጉ ልጆች በራስ መተማመናቸው ከፍ ያለ ነው። የቻፕማን ፍልስፍና እንደሚያሳየው፣ የተሞላ የፍቅር ታንክ ያላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅርን ለማካፈል አቅም አላቸው። መልካም ትዳር የልጆችን ስነ-ልቦናዊ ደህንነት ጠብቆ ያሳድጋል። ባዶ የሆነ ወላጅ ለልጁ የሚሰጠው ነገር የለውም። የፍቅር ቋንቋን መረዳት ማለት የሌላውን ሰው ፍላጎት ማወቅ ማለት ነው። ይህ ክህሎት በቤተሰብ ውስጥ መቻቻልን ያሰፍናል። በውጤቱም ግጭትን የመፍታት ብቃትን ያጎለብታል።
በቻፕማን መርህ መሰረት በፍቅር የተገነባ ቤተሰብ፣ በስነ-ልቦና ያልተጎዳ ዜጋን ለሀገር ያስረክባል። በልጅነታቸው በቂ ፍቅር ያገኙ ዜጎች ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ለሌሎች ርህራሄ (Empathy) ያላቸው፣ ወንጀል ለመስራት የማያስቡ እና አምራች ዜጎች ይሆናሉ። “የአገልግሎት ድርጊት” (Acts of Service) አንዱ የፍቅር ቋንቋ ነው። ይህንን በትዳራቸው የተለማመዱ ጥንዶች፣ ለሀገራቸውም በማገልገል ባህል የታነፁ ይሆናሉ።
ጆን ግሬይ “ሜን አር ፍሮም ማርስ፣ ዉሜን አር ፍሮም ቬነስ” (ወንዶች ከማርስ ሴቶች ከቬነስ) በሚለው መጽሐፋቸው የወንዶችና የሴቶች ስነ ልቦናዊ አፈጣጠር ይለያያል። “ወንዶች ከማርስ ሴቶች ከቬነስ” የመጡ ያህል ይለያያሉ ይላሉ። ወንዶች ችግር ሲገጥማቸው ወደ “ዋሻቸው” (ብቻቸውን መሆን) ይገባሉ። ዝምታን ይመርጣሉ፤ ሴቶች ደግሞ በመናገር ስሜታቸውን መግለጽ ይፈልጋሉ።
ይህንን ልዩነት አለመረዳት ለብዙ ትዳሮች መፍረስ ምክንያት ነው። ጆን ግሬይ እንደሚሉት ልዩነትን አምኖ መቀበል ትዳርን ያረጋጋል። ባል ሚስቱ ስታወራ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ማዳመጥ እንዳለበት፣ ሚስት ደግሞ ባል ሲጨናነቅ ለተወሰነ ጊዜ ብቻውን መሆን እንዳለበት ሲረዱ፣ በቤተሰብ ውስጥ መከባበር ይሰፍናል። ልዩነትን ማክበር የፍቺን መጠን ይቀንሳል። ፍቺ ለቤተሰብ በተለይም ለልጆች ትልቅ ቀውስ ነው። የተረጋጋ ትዳር ለልጆች የአእምሮ ሰላምን ይሰጣል።
ልዩነትን የማስተናገድ ባህል በመልካም ትዳር ውስጥ ይፈጠራል። ይህ የጆን ግሬይ ሀሳብ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ የሆነ ትምህርት አለው። በትዳር ውስጥ የፆታ ልዩነትን አክብሮ መኖር የቻለ ሰው፣ በሀገር ደረጃ የብሄር፣ የሃይማኖት ወይም የፖለቲካ ልዩነቶችን አክብሮ የመኖር አቅም ይኖረዋል። ትዳር ልዩነትን አቻችሎ የመኖር ትንሹ ላቦራቶሪ ነው።
ጆን ግሬይ ወንዶች ዋጋ እንዳላቸው ሲሰማቸው (መደነቅን)፣ ሴቶች ደግሞ እንደተደመጡና እንደተወደዱ ሲሰማቸው በስራቸው ላይ ውጤታማ እንደሚሆኑ ይገልጻሉ። ሰላማዊ ትዳር ያለው ሰው በስራ ቦታው ላይ ትኩረቱ አይበተንም፤ ፈጠራው ይጨምራል። ይህ ደግሞ በቀጥታ የሀገርን ኢኮኖሚ ያሳድጋል።
ከቻፕማን እና ከግሬይ ሀሳቦች ባሻገር የተለያዩ የማህበራዊ ሳይንስ ጥናቶች መልካም ትዳር ለሀገር ያለውን ፋይዳ በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የተረጋጋ ትዳር ያላቸው ቤተሰቦች ከነጠላ ወላጆች ወይም ከተፋቱ ቤተሰቦች የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ይገነባሉ። ሁለት ሰዎች በጋራ ሲሰሩና ሲያቅዱ፣ ሀብት የማፍራት አቅማቸው ይጨምራል። ድህነትን በቤተሰብ ደረጃ ማሸነፍ ማለት በሀገር ደረጃ ድህነትን መቀነስ ማለት ነው። መልካም ትዳር የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ አካል ነው።
ጤናማ ትዳር ያላቸው ሰዎች በጭንቀት፣ በደም ግፊት እና በልብ ህመም የመጠቃት እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን የህክምና ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ ማለት ሀገር ለዜጎች ጤና የምታወጣውን በጀት ይቀንሳል ማለት ነው። በአሜሪካ የተደረጉ የሶስዮሎጂ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከአባትና እናት ጋር በፍቅር ያደጉ ልጆች በወንጀል የመሳተፍ፣ ትምህርት የማቋረጥ እና በሱስ የመጠመድ እድላቸው እጅግ ዝቅተኛ ነው። መልካም ትዳር የወንጀል መከላከያ ተቋም ነው። እስር ቤቶችን ከመገንባት ይልቅ ጤናማ ትዳሮችን መገንባት ለሀገር የሚያተርፈው መንገድ ነው።
ሀገር ማለት መሬት ሳይሆን ሰው ነው። የነገ ሀገር ተረካቢዎች ዛሬ በየቤቱ ያሉ ህፃናት ናቸው። ግሬይ ቻፕማን “ፍቅር ምርጫ ነው” ይላሉ። ወላጆች እርስ በእርስ ለመዋደድ ሲመርጡ፣ ልጆች ይህንን የምርጫ ጥበብ ይማራሉ። ኃላፊነት የሚሰማው፣ ቃል ኪዳኑን የሚያከብር እና ለሌሎች የሚኖር ዜጋ የሚፈጠረው በመልካም ትዳር ውስጥ ነው።
የግሬይ ቻፕማን “አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች” እርስ በእርስ መግባባትንና ስሜታዊ ፍላጎትን ማሟላትን ሲያስተምሩን፣ የጆን ግሬይ “ወንዶች ከማርስ ሴቶች ከቬነስ” ደግሞ ተፈጥሮአዊ ልዩነቶችን አክብሮ መኖርን ያስገነዝቡናል። እነዚህ ሁለት ምሰሶዎች ተደምረው መልካም ትዳርን ይፈጥራሉ።
መልካም ትዳር ለቤተሰብ የደስታ ምንጭ፣ ለልጆች የሰላም ጥላ ነው። ወደ ሀገር ደረጃ ስናሳድገው ደግሞ፤ መልካም ትዳር ምርታማ ዜጋን፣ የተረጋጋ ማህበረሰብን እና ጠንካራ ኢኮኖሚን ይፈጥራል። ሀገርን ለመለወጥ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ትኩረቱን ቤተሰብ ላይ ማድረግ የሚኖርበት ለዚህ ነው። ምክንያቱም የፈራረሰ ትዳር የበዛበት ሀገር፣ የፈራረሰ ማህበረሰብ እና የደከመች ሀገር ከመሆን አይድንም። ትዳርን መጠበቅ ሀገርን መጠበቅ ነው።
ለትዳር አጋራችን የምናሳየው ፍቅር፣ የምንሰጠው ክብር እና የምናደርገው እንክብካቤ፣ በግል ህይወታችን ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን እጣ ፈንታ ላይም አሻራ አለው። ጤናማ ትዳር የሀገር ህልውና ዋስትና ነው። የዛሬ ልጆች ነገ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ማን ያውቃል? የዛሬ መሪዎች እንዴት እንዳደጉ መመርመር ምናልባትም ኢትዮጵያ በትዳር ላይ ብትሰራ ኖሮ ግጭት ቀለበት ውስጥ ደጋግማ ባልገባች ነበር እንድንል ያደርገናል። የሀገር ሰላም ምንጩ ትዳር ነው። ቤተሰብ ነው። እሱን ማጥራት ሀገርን ካቀረቀረችበት ማቃናት ነው።
ማረፊያ
አማርኛ ቅኔ
ኧረ እናንተ ሰዎች የት ነው አገራችሁ ፤
በማፈር በማፈር ትጫወታላችሁ፡፡
ሠም ፡- እናንተ ሰዎች ለምን በመተፋፈር በመሰቀቅ ትጫወታላችሁ?
ወርቅ ፡- እናንተም እነሱም ማቾች ስትሆኑ ለምን ዐፈር በሚሆነው በሰው ትጫወታላችሁ?
-አማርኛ ቅኔ ከነመፍቻው ፍሥሐ አጥላው
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


