በአሜሪካ ካሮላይና ግዛት በብሉፍተን ፓርክ ጐዳና ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ስር ዘላ የገባችን ድመት አሽከርካሪው አቁሞ መመታት አለመመታቷን ለማወቅ ፈልጐ ሊያገኛት ባለመቻሉ በአቅራቢያው በሚገኝ የእሳት አደጋ ማጥፊያ ጣቢያ ገብቶ እንዲረዱት መጠየቁን ዩፒአይ ድረ ገጽ በታህሳስ ወር መግቢያ አስነብቧል::
የብሉፍተን ታወንሺኘ የእሳት አደጋ መካላከያ መምሪያ በማህበራዊ ሚዲያ እንዳሰፈረው አሽከርካሪው ድንገት ዘላ የገባችበትን ድመት መመታት አለመመታቷን ለማየት ሲቆም የድመቷን ድምፅ እንጂ ያለችበትን ቦታ ማግኘት አልቻለም:: በድጋሚ ፈልገው አጥተዋት ማሽከርከር ሲጀምር የድመቷን ጩኸት ይሰማል፤ ይሄኔ በነበረበት ቦታ አቁሞ ከረዳቱ ጋር እርዳታ የሚያገኙበትን ቦታ ያፈላልጋሉ::
አሽከርካሪው እና አብሮት የነበረው ልጁ“ብረንት ቸርች” ጐዳና ወደ ሚገኘው 30ኛው የእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያ ያመራሉ:: በግቢው ውስጥ ገብተው ተሽከርካሪያቸውን በማቆም አጋጣሚውን ላገኛቸው የጣቢያው ሰራተኞች ያስረዳሉ::
የገጠማቸውን ሁኔታ ከሰሙት አንዱም ፈቃደኛ ሆኖ ለፍለጋው የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ይዞ ተሽከርካሪው ስር ይገባል::
የእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያው ከፍተኛ መካኒክ ታየለር ዌሊያም በሰውኛ “ሚያው” እያለ ድመቷ መልሳ እንድትጮህ ያደርጋል- ያለችበትን በውል ለመገንዘብ::
መካኒኩ ድመቷ ያለችበትን ጥግ ከለየ በኋላም ለፍለጋው ያመቸው ዘንድ የተወሰኑ የተሽከርካሪውን ክፍሎች ፈታትቶ ወደ ተፈላጊዋ መቃረቡን ያበስራቸዋል:: በህይወት መትረፏን ለናፈቁት አባት እና ልጅ::
በመጨረሻም ተሽከርካሪው ስር በፈቃደኝነት በገባው መካኒክ ፍለጋ ህይዎት የማትረፍ ጥረቱ ሰመሮ ድመቷን ተጣብቃ ከተወተፈችበት ማውጣቱን እና በአቅራቢያው በሚገኝ የእንስሳት መጠለያ ማስገባቱን አብቅቷል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


