ሐረር ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ 525 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት:: ከተማዋ ከመካ፣ መዲና እና ከእየሩሳሌም ቀጥሎ አራተኛዋ ቅድስት ከተማ እንደሆነችም ድረ ገፆች አስነብበዋል::
በከተማዋ ውስጥ የሚገኘው 48 ሄክታር ክልልን የሚያጥረው የጀጐል ግንብም በ16ኛው ክፍለ ዘመን ነው የተገነባው:: ግንቡ አምስት ሜትር ቁመት እና ሦስት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ተለክቷል:: ግንቡ ከተማዋን ከወራሪዎች ለመከላከል ከ13ኛው እስከ 16 ኛው ክፍለ ዘመን መካከል እንደተገነባም ነው የሚታነው:: በተጠቀሰው ዘመን ከተማዋ ራሷን ችላ የምትተዳደር ነበረች፤ በዙሪያዋ ለሚገኙ የጠረፍ እና የደጋማ ግዛት ኗሪዎች የንግድ ማእከል ሆናም አገልግላለች::
በከተማዋ 82 መስጊዶች ማለትም የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ቤተ እምነቶች ይገኙባታል:: ወደ ሀረሪ ወይም የአደሬዎች ብሄረሰብ መኖሪያ ወደ ሆነው የከተማዋ እምብርት ለመግባት አምስት በሮች አሏት:: 1ኛው ሸዋ በር፣ 2ኛው ቡዳ በር፣ 3ኛው ኤረር በር፣ 4ኛው ሰንጋ በር እና 5ኛው ፈላና በር ሲሆኑ በ1889 ዓ.ም በራስ መኮንን በስተምእራብ የተገነባው በስድስተኛነት ተጨምሮ ዋና መግቢያ በር ሆኗል::
በጀጐል ውስጥ የሚኖሩት ሀረሪዎች በአላባበስ፣ አጋጌያጥ፣ በቤት አሰራር፣ በመጠቀሚያ ቁሳቁስ ወ.ዘ.ተ የራሳቸው የሆነ መገለጫ መለያ ባህል አላቸው::
በ2006 እ.አ.አ የሀረሪዎች መኖሪያዋ ጀጐል በዓለም አቀፍ የአካባቢ ሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል:: በግንቡ ውስጥ ያሉት በድንጋይ “ግንብ” የተሰሩ መኖሪያ ቤቶች፣ ጣባብ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የገበያ ቦታዎች እና የሽመና ወይም የጥልፍ መስሪያ እና የጌጣጌጥ አንጣሪ እና መሸጫ ሱቆች በመስህብነት ተጠቃሽ ናቸው:: ጐብኚዎች በጀጐል ውስጥ ገብተው ለመንቀሳቀስ አስጐብኚ መያዝ ግድ ይላቸዋል::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ቪዚት ኢትዮጵያ፣ ሙዚዬም ኦፍ ወንደር፣ ሀረር ኮሙዩኒኬሽን እና ዩኔስኮ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


