በኢትዮጵያ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መዘርጋት ነዋሪዎች የመታወቅ መብታቸው እንዲረጋገጥ፣ ሌሎች መብቶችን የመጠቀም ዕድሎችን ለማስፋት፣ በአገልግሎት ሰጪ እና ተቀባይ መካከል በሚኖር ግንኙነት ላይ እምነት ለማዳበር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና የተሳለጠ የአሠራር ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ ዲጅታል መታወቂያን በተመለከተ በነጋሪት ጋዜጣ (አዋጅ ቁጥር 1284/ 2015) ሰፍሯል፡፡ በዘመናዊ መንገድ ሀገራዊ ልማትን በአግባቡ ለማቀድ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግር ለመፍጠር፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ፣ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ እና የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ድግግሞሽን ለማስቀረት እና አካታችነትን ለማጎልበትም ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነም በአዋጁ ሰፍሯል፡፡
በኢትዮጵያም ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያን ልማትን በማሳለጥ፣ ማጭበርበርን በማስቀረት እና ሥራን በማፋጠን የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በመረዳት ሥርዓቱን መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የዲጂታል መታወቂያን በአዋጅ ቁጥር 1284/2015 አፅድቆታል፡፡
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ማግኘት የሚችሉት እነማን ናቸው?
ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ እንዲሁም በዜግነት ኢትዮጵያዊ ሆነም አልሆነም በሀገሪቱ ነዋሪ እስከሆነ ድረስ የመኖሪያ ወይም የሥራ ፈቃዱን በማሳየት አገልግሎቱ ይፈቅድለታል፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘትም አካላዊ (ባዮሜትሪክ) እና አካባቢያዊ (ዲሞግራፊክ) መረጃዎችን በመስጠት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት እንዳለው በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የትሬኒንግ ዲፓርትመንት ሱፐርቫይዘር አቶ ሃሌሉያ ዘላለም ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያውን ለማግኘት ከ33 አይነት የመታወቂያ አማራጮች አንዱን በማቅረብ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ፡፡ የባንክ ደብተር፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ የመንጃ ፈቃድ ደብተር፣ የተማሪዎች መታወቂያን ጨምሮ ፎቶ ግራፋቸው ያለበት እነርሱን የሚገልጹ ሰነዶች በማቅረብ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህ የተደረገው መታወቂያው አካታች በመሆኑ ሁሉም የሀገሪቱን ነዋሪ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡
ግለሰቦች ከ33 አይነት መታወቂያዎች አንዱም ከሌላቸው ደግሞ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ያለው ሰው ምስክር በማቅረብ በሁሉም ባንኮች እና ቴሌኮሙዩኒኬሽን መታወቂያውን ማግኘት ይቻላል፡፡
ከዕድሜ አኳያም ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት በሥነ ሕዝብ (ዲሞግራፊ) መረጃ ብቻ የምዝገባ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ የዲሞግራፊክ መረጃ የሚባሉትም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ስም፣ የአባት ስም፣ የአያት ስም፣ ዜግነት፣ የትውልድ ቀን፣ ወር እና ዓመት፣ ፆታ እና መኖሪያ አድራሻ ሲሆኑ እንደ አስፈላጊነቱም ስልክ ቁጥር፣ የኢሜይል አድራሻ እና ፖስታ አድራሻንም ሊያካትት ይችላል፡፡
ከአምስት ዓመት በላይ ያሉ ልጆች ደግሞ በሥነ ሕዝብ እና አካላዊ (ባዮሜትሪክ) መረጃዎችን በመውስድ ይሰጣቸዋል፡፡ አካላዊ መረጃዎች (ባዮሜትሪክ) የሚሰበሰቡት ደግሞ በጣት አሻራ፣ በዐይን ብሌን እና በፊት ገፅታ ነው፡፡
ጠቀሜታውስ?
ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ በሀገር እና ሕዝብ ላይ በሀሰተኛ መረጃ የሚደርስ ማጭበርበን እንደሚያስቀር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሕር ዳር ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ደመወዝ በሪሁን ለአሚኮ በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ከዚህ በፊት አንድ ሰው አንድ መሆኑን ለማረጋገጥ ወይም የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት በርካታ ሰነዶችን ለማቅረብ የሚያደርገውን ውጣ ውረድ ይቀንሳል፡፡
ከባንኮች ብድር ለማግኘት በሚደረግ የማጣራት ሂደትም ይደርስ የነበረን እንግልት በማስቀረት አገልግሎትን ያፋጥናል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ባንክ ላይ በአገልግሎት ሰጪዎች እና ተቀባዮች መካከል መተማመንን ይፈጥራል፡፡ ይህም ማለት አገልግሎት ሰጪው መታወቂያውን ለማን እንደሠራ እንዲሁም አገልግሎቱን ያገኘውም ከማን እንደሆነ በመረዳት በባንክ በኩል የተለያዩ መታወቂያዎችን ከተለያዩ ቦታዎች በማውጣት በግለሰቦችም ሆነ በሀገር ይፈጠር የነበረውን ስጋት ያስቀራል፡፡
ከገቢዎች፣ ከመሬት፣ ከካርታ እና ፕላን፣ ከገንዘብ ጋር ተያይዘው ይፈጠሩ የነበሩ ችግሮችንም እንደሚያስቀር አቶ ሃሌሉያ ጠቁመዋል፡፡
ግብርና ሚኒሥትርም የግብርና አገልግሎትን ለማሳለጥ ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ጋር እንዲተሳሰር ማድረጉን በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ በበጀት ዓመቱ 12 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በሀገር አቀፍ ደረጃ መታወቂያ እንደሚያገኙ ያመላከተው መረጃው በዚህም በተለይ የብድር ሥርዓቱን ከዲጂታል መታወቂያው ጋር በማስተሳሰር የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ዕውን ለማድረግ ሚናው የጎላ ነው፡፡ ምዝገባው በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ የሚከናወን እንደሆነም ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።
በትምህርት ሥርዓቱም ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ከማጭበርበር ጋር ተያይዞ ሕፃናት አድገው በትልልቅ ተቋማት ሲያገለግሉ ወይም ትምህርት ላይ እያሉ የውጪ የትምህርት ዕድል ሲያገኙ የሥም እና የትውልድ ቀን ሥህተት እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ከሌሎች የሚለየው
በአዋጅ ቁጥር 1284/2015 አንቀፅ 5 ላይ እንደተመለከተው የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ዓላማ ነዋሪዎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሲንቀሳቀሱ በቀላሉ የመታወቅ መብታቸው እንዲረጋገጥ በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች አከባበር እና ለመልካም አስተዳደር መሻሻል አስተዋፅኦ ማድረግ፣ አገልግሎት ማግኘት የሚፈልጉ ግለሰቦችን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ነው፡፡ በአገልግሎት ሰጪ እና አገልግሎት ተቀባይ መካከል እምነት እንዲጎለብት ማድረግ፣ ሕገ ወጥ ተግባራትን መከላከል፣ ሀገር አቀፍ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን በማደራጀት ሀገራዊ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና ዕቅዶች ሲቀረጹ እና የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ድግግሞሽን ማስቀረት፣ በዚህም የሀብት ብክነትን መቀነስ እና አካታችነትን ማጎልበት የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት ለሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ላልሆኑ አካላት የመረጃ ምንጭ ሆኖ ማገልገል እና አገልግሎት ተኮር የሆኑ የመታወቂያ ሥርዓቶች ወደ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት እንዲሸጋገሩ ማጠናከር ያስችላል፡፡
ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሌሎች የመታወቂያ ሥርዓቶችን እያጠናከረ እና ራሱንም ችሎ ማናቸውንም አገልግሎቶች ለማግኘት የሚያስችል የመታወቂያ አይነት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
እንደ አቶ ሃሌሉያ ማብራሪያ የቀበሌ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የትምህርት ቤት መታወቂያዎች የአገልግሎት መታወቂያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ መንጃ ፈቃድ የያዘ አሽከርካሪ መኪና ለማንቀሳቀስ ብቁ ነው የሚለውን ለማረጋገጥ ነው፤ የቀበሌ መታወቂያም በተመሰሳይ የቀበሌው ነዋሪ መሆንን ነው የሚያረጋግጠው፡፡
ይህን ተከትሎም መንጃ ፈቃድ የተጠየቀ አሽከርካሪ ፈቃዱን ሲጠየቅ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያውን ብቻውን ማቅረቡ የሚያረጋግጠው ማንነቱን እንጂ ሙያዊ የማሽከርከር ብቃቱን ባለመሆኑ ሁለቱንም ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡
በአጠቃላይ ፋይዳ መታወቂያ አንድ ሰው አንድ መሆኑ የሚረጋገጥበት ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የተመዘገቡ ዜጎች የፋይዳ ቁጥር የሚባለውን ባለ 12 እና 16 አሀዝ (ዲጂት) መለያ ቁጥር በካርድ፣ በወረቀት ወይም በስልክ በማሳየት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሥርዓት ነው፡፡
ሥልጣን ባለው አካል የተሰጠን ብሔረዊ ዲጂታል መታወቂያን እንደ ሕጋዊ መታወቂያ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነ ወይም ማንነትን ብቻ በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ (በአዋጅ ቁጥር 1284/2015 አንቀጽ 19 ላይ የተመለከተውን የመተባበር ግዴታ የተላለፈ ማንኛውም ሰው) ከዐሥር ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ እንደሚቀጣ መደንገጉን ልብ ይሏል፡፡
መረጃ
ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያን ከሌሎች ልዩ የሚያደርጉት መገለጫዎች አሉት፡፡ አንድ ሰው አንድ መሆኑ የሚረጋገጥበት ሲሆን ዜጎች የፋይዳ ቁጥር የሚባለውን ባለ 12 እና 16 አሀዝ /ዲጂት/ መለያ ቁጥር በካርድ፣ በወረቀት ወይም በስልክ በማሳየት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሥርዓት ነው፡፡
እንደ ሀገር ካለው ሕዝብ 40 በመቶው ራሱን የሚገልጽበት ምንም አይነት መረጃ ወይም ማስረጃ /መታወቂያ/ የለውም፡፡ ይህን አሳሳቢ ጉዳይ ግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ 33 ማስረጃዎችን (የቀበሌ መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የመኪና ባለቤትነት ማረጋገጫ /ሊብሬ/፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ …) በማቅረብ መመዝገብ የሚቻልበት ሥርዓት ነው፡፡
ማስረጃዎች የሌላቸው በአብዛኛዎች ጐዳና ተዳዳሪዎች፣ በተለያዩ ማዕከላት የሚኖሩ አቅመ ደካሞች፣ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕፃናት… ፋይዳ መታወቂያ ያላቸውን ሰዎች ምስክር በማድረግ፣ ባሉበት ተቋም ወይም እነዚህን ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ ወይም አገልግሎት ለመስጠት ከተቋቋመ መስሪያ ቤት ጋር በመናበብ መታወቂያውን የሚያገኙበት ሥርዓት ነው፡፡
(ሙሉ ዓብይ )
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


