ሁለተኛውን የጣሊያን ወረራ ለመመከት አምባላጌ ላይ በተደረገው ውጊያ ሁለት ወንድሞቹን አጥቷል፤ እነዚህ ወንድሞቹ የወረጃርሶ ፊታውራሪዎች እና የጦር መሪዎች ነበሩ:: በወቅቱ የ16 ዓመት ታዳጊ ወጣት ነበር:: አባቱን ቀደም ብሎ በተፈጥሮ ሞት አጥቶ ነበር እና ሀዘኑ እጥፍ ድርብ ነበር:: ነገር ግን ልጅነቱ እና ሀዘኑ ታሪክ ከመስራት አላገዱትም- አቢቹን:: ተንኮል፣ ግብዝነትና ቅናት በወለዱት ከንቱ አስተሳሰብ ቅንጣት ያህል ቦታ ያልተሰጠው ምስኪን ጀግና! አብቹ በቼኮዝሎቫኪያዊው ጸሐፊ እና የራስ ካሳ ኃይሉ የጦር አማካሪ አዶልፍ ፓርለሳክ እንደሚከተለው ተተርኮለታል::
አብቹ የተወለደው በ1912 ዓ.ም ነው፤ ቦታው ደግሞ የዛሬው ሰሜን ሸዋ (ኦሮሚያ ክልል) ወረጃርሶ ወረዳ:: አባቱ የወረጃርሶ ጦር መሪ ነበሩ:: በጣሊያን ወረራ ዋዜማ ላይ በተፈጥሮ ህመም ሞቱና ዘመድ አዝማድ አልቅሶላቸው በወጉ ተቀበሩ:: አባት ሲሞት ልጅ በአባቱ እግር ተተክቶ ኃላፊነቱን መወጣት የቆየ ልማድ ነበረና የጃርሶን ጦር የአብቹ ሁለት ወንድሞች እንዲመሩት ይደረጋል:: የሰላሌና የበጌምድርን ጦር በበላይነት የሚመሩት ራስ ካሳ ቢሆኑም የጃርሶ ጦር መሪዎች የሚታዘዙት ግን ለራስ ካሳ ልጅ ደጃዝማች አበራ ነበር:: በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን ሀገራችንን መውረሩ እንደተሰማ ዘገራቸውን በቁጣ ከነቀነቁ እውነተኛ ኢትዮጵያን መሃል የአብቹ እና ወንድሞቹ ተጠቃሽ ሆኑ::
አብቹ ከወንድሞቹ ጋር ይዝመት እንጂ የደጃዝማች አበራና የእሱ ፍቅር ለጉድ ነው:: አብቹ አዕምሮው ብሩህ ጉብል ነው:: እድሜውና ድርጊቱ በፍፁም ሊገናኙ የሚችሉ አይመስሉም:: ከሰላሌ የተንቀሳቀሰው ጦር የቻለ ስንቁን በፈረስ፣ በበቅሎና በአህያ ጭኖ፤ ያልቻለ ደግሞ በትከሻው ተሸክሞ ለሰባት ወራት በእግሩ ሲኳትን ከቆየ በኋላ ለጦርነት የተፈጠረ ከሚመስለው የትግራይ ተራራማ ግዛት አምባላጌ ደረሰ:: የአንበሳው አሉላ አባነጋ የትውልድ ቦታ ከሆነው ቆላ ተምቤን በመውረድም አምባራዶም ከተባለ ቦታ ላይ ከወራሪው ኃይል ጋር የሞት ሽረት ትግል አካሄደ:: በውጊያው ላይ እጅግ በርካታ የፋሽስት መንጋ አንገቶችን እንደ ጐመን የቀነጠሱ ጀግኖች የሀገራቸውንና የወገናቸውን ቀጣይ ውርደት ሳያዩ በክብር ወደቁ:: ከእነዚህ አንበሶች መሃል የአብቹ ወንድሞች ይገኙበታል:: አንደኛው ወንድሙ ይማረክ ወይም ይሙት እርግጡ ያልታወቀ ሲሆን የሌላኛውን ወንድሙን አስከሬን ግን ከአንዲት ዋርካ ዛፍ ስር ቀብሮ እርሙን ተወጣ:: ከወንድሙ መቃብር አጠገብ ካለች አንዲት ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ሌት ከቀን ይተክዝ ጀመር:: እህል ውሃ ሳይቀምስ ለሁለት ቀናት በመቆየቱም ደጃዝማች አበራን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ገጠመው::
የሚያደርገው ቢያጣ ሽማግሌዎችንና ሌሎች አማካሪዎቹን ሰብስቦ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጊዜ የፈጀ ውይይት ተካሄደ:: መጨረሻ ላይ አንድ የጃርሶ ጦር አባል “እኔ አሳምነዋለሁ፤ እህል ውኃ እንዲቀምስም አደርጋለሁ” ብሎ ኃላፊነቱን ወሰደ:: በምን ዘዴ እንዳሳመነው ባይታወቅም እውነትም አብቹ ሁለት ቀንና ሁለት ሌት ብቻውን ከተቀመጠበት ድንጋይ ላይ ተነስቶ ከጦሩ ጋር ተቀላቀለ:: ግን እህል የሚቀምሰው ጥያቄው ከተመለሰለት ብቻ መሆኑን አስገነዘበ:: ጥያቄውም “200 ወጣቶች ይሰጡኝና ወንድሜን ከጣሊያን ምርኮ ነፃ ላውጣው” የሚል ነው:: የጃርሶን ጦርም አጐቱ ቀኛማች ገለታ እና ቀኛዝማች ሼህ ሁሴን አባወርቁ እንዲመሩት ፈቀደ::
የደጃዝማቹን ፈቃድ ሲያገኝ የአብቹ ደስታ ወሰን አልነበረውም:: እንዲያውም ያንን የልጅነት አዕምሮውን ክፉኛ የበጠበጠውን ሀዘኑን እርግፍ አርጐ ትቶ በሚገርም ደስታ ቀየረው:: የቀሩትን ሦስት በሬዎች አርዶም ጦሩን ሲጋብዝ፣ ሲዘፍንና ሲያዘፍን አመሸ:: ሊነጋጋ ሲል የተመረጡለትን 200 ያህል ወጣቶች አስከትሎ በሞቀ ቀረርቶና ፉከራ ወደ ጣሊያን ምሽግ ገሰገሰ:: ከዚያን ቀን ጀምሮ “አብቹን አየሁ” የሚል ጠፋ::
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የአብቹ ዝና በትግራይ ሰማይና ምድር ብቻ ሳይሆን በሮማ ከተማ ጭምር በመናኘቱ እጅግ በርካታ ወጣቶች አለቆቻቸውን፤ ማለትም ራስ ካሳን፣ ራስ ሥዩም መንገሻንና ደጃዝማች አበራን በመክዳት ከእሱ ጦር ጋር ይቀላቀሉ ጀመር:: በአብቹ የሚመራው ጦር ጠላቱ ላይ ጥቃት የሚፈፅመው ጠላት ባላሰበው አሳቻ ስፍራና ሰዓት በመሆኑ ነፍሰ በላዎቹን ፋሽስቶች ብርክ ያስይዛቸው ጀመር:: ከጣሊያን በሚማርከው ትጥቅና ስንቅ የአብቹ ክንድ እየፈረጠመ፤ እግረ መንገዱንም በጣሊያኖችና አሽቃባጮቻቸው ላይ የሚፈፅመው ቅጣት እየጠነከረ በመሄዱ ጣሊያኖች በመርዝ ጋዝ ህዝቡን ያሰቃዩት ጀመር:: በዚህ የተነሳ አብቹ በወገኖቹም በጠላቱም እጅግ ተሳዳጅ ሆነ::
ንጉሡም ሆኑ ራሶች “ልጁን እሰሩት!” የሚል ቀጭን ትእዛዝ ለበታች ሹሞቻቸው በተደጋጋሚ ቢያስተላልፉም አብቹ የእሳት አሎሎ ሆነ:: እንዲያውም ከትግራይ በጄኔራል ተስፋ ጽዮን፣ ከኤርትራ በጄኔራል ሃብቶም፣ ከጐጃም በጄኔራል ጋሹ፣ አንዲሁም ከሰላሌ በጄኔራል ወርቁ የሚመራ አንድ አንድ በድምሩ አራት ባታሊዮን ጦር ተቀላቀለውና በንጉሡም ሆነ በፋሽስት ጠላቶቹ ዘንድ ቁጥር አንድ ስጋት እየሆነ መጣ:: “የልጁ ሠራዊት በዚህ በኩል አለፈ” ከተባለ ምድረ ፋሽስትና ባንዳ እንደ ቄጠማ እየራደ የሚይዝ የሚለቀውን ማጣት የየእለት ተግባሩ ሆነና አረፈው:: የአብቹን እጅ በቀላሉ መያዝ አልሆንለት ያለው ደጃዝማች አበራ፤ አንድ ቀን የተሻለ ዘዴ ተጠቀመና ተሳካለት:: እሱም “አበራ በጠና ታሟልና በነፍሱ ድረስ ብላችሁ ንገሩት:: በእኔ የሚጨክን አንጀት የለውም” የሚል መልእክት በታማኝ ወዳጁ አማካይነት ለአብቹ እንዲደርሰው ማድረግ ነበር::
መልእክቱ ሲደርሰው እውነትም አብቹ መዋል ማደር አልቻለም:: ድንገት ከደጃዝማች አበራ ዋሻ ዘው ሲል ደጃዝማቹም ሆነ አብረውት የነበሩ መኳንንትና አሽከሮች ልክ መብረቅ የወረደባቸው ያህል ክው ብለው ቀሩ:: ከጥቂት የመረጋጋት ጊዜ በኋላ ደጃዝማች አበራ በአይን ጥቅሻ ለአሽከሩ የሆነ ምልክት ሰጠው – “እሰሩት” የሚል ነው መልእክቱ:: የደጃዝማቹ አሽከር ተጨማሪ አሽከሮችን ለመጥራት ከድንኳን በፍጥነት ቢወጣም በሌላ ኃይል እየተነዳ በምርኮኛ መልክ ሁለት እጁን ወደላይ ሰቅሎ ሲመለስ ጊዜ አልፈጀበትም:: በዚህ ጊዜ “ኮሌኔል ኮኖቫሎቭ” የተባለ ሰው (ዋሻው ውስጥ ከነበሩት አንዱ እና የራስ ስዩም መንገሻ የጦር አማካሪ) ደንግጦ “ምርኮኞች ሆንን ማለት ነው?” ብሎ አብቹን ሲጠይቀው አብቹ የተሟላ ህሊና ያለውን ሰው አንጀት የሚያላውስ መልስ ይሰጣል:: እንዲህ ሲልም ይጠይቃል፡-“ደጃዝማች ገና ከሰላሌ ስንነሳ ታማኝነቴን በምኒልክ ስም ቃል የገባሁት ላንተ እንጂ ለሽማግሌዎች (ራስ ሥዩምንና ራስ ካሣን ማለቱ ነው) ወይም ለንጉሡ አይደለም:: እኔ ንጉሥ አይደለሁም፤ ተራ ወታደር እንጂ:: እና እኔ ሁለት ሦስት ወር ደሴ ተጐልቼ (ቆላ ተምቤን፣ አምባራዶምና አቢአዲ አካባቢ ዘግናኝ ጦርነቶች ሲካሄዱ ንጉሡ ደሴ ሆነው “ተከላከሉ እንጂ አትዋጉ” ሲሉ ስለነበር ያንን በአሽሙር ለመግለጽ ፈልጐ ነው፤ ይህ ውሳኔ በቀጥታ ኢትዮጵያ ጦር ያገኘውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የጣሊያንን ጦር እንዳያሸንፍ ዋናኛ ምክንያት ተደርጎ ይቀመጣል) ጣሊያኖች እጄን እስኪይዙኝ አልጠብቅም:: ላንተ ግን አሁንም በምኒልክ ስም፣ በምኒልክ አምላክ በድጋሚ ቃሌን እሰጣለሁ:: ላንተ እሞታለሁ:: ተመለስ! ላልኸው ግን የት ነው የምመለሰው? ምንስ መመለሻ ቤት አለኝና? …አለና የደጃዝማች አበራን ዋሻ ለቅቆ ወጣ::
አቢቹ ከዚያ የት እንደሄደ የሚታወቅ ነገር የለም:: ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ወታደሮቹን በትግራይ በረሃዎች እያዟዟረ ጣሊያኖችንና ባንዳዎችን ድባቅ መምታቱን ቀጠለ:: አቢአዲ አለ ሲባል አምባ አራዶም፤ አምባራዶም ታየ ሲባል መቀሌ፣ መቀሌ አለ ሲባል ማይጨው እየተወረወረ እንኳን ጠላቱን ወዳጆቹን እነደጃዝማች አበራን እና ሁለቱን ራሶች፣ እንዲሁም ንጉሠ ነገሥቱን ግራ አጋባቸው::
የመጨረሻው የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ማይጨው ላይ በመሆኑ በራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ከሚመራው ጦር በቀር የሦስቱ ራሶች (ራስ ሥዩም መንገሻ፣ ራስ ሙሉጌታ ይገዙና ራስ ካሣ ኃይሉ) ጦር አንድ ቦታ ላይ በመቀናጀት ጠላትን ቀጥቶ ዳግማዊ አድዋን በማይጨው ለመድገም ተወስኗል:: አብቹም ሆነ በእሱ የሚመሩት አንበሶች መንገድ ላይ የሚገጥማቸውን መሰናክል ሁሉ በከፍተኛ ወኔ እየተጋፈጡ ማይጨው ደረሱ::
ከፊት ነፍሰበላው የጣሊያን ጦር ከኋላ ደግሞ መንጋ የባንዳ ግባሶ የጥይት በረዶ እያዘነበባቸው ከሰው የተፈጠሩና በሞት የሚረቱ ሳይመስሉ ግዳጃቸውን ተአምር በሚመስል ሁኔታ ተወጡ:: ከጣሊያን ምሽግም እየዘለሉ ገቡና የተወለደበትን ቀን ያስቆጥሩት ጀመር:: ግና ምን ይሆናል ከወገን በኩል ምንም አይነት አጋዥ ኃይል ማግኘት አልቻሉም:: ስለሆነም ጄኔራል ተስፋ ጽዮንና ጄኔራል ጋሹ የተባሉትን ምርጥ አዛዦችንና በርካታ አባሎቻቸውን በሞት አጥተው ወደ ሰላሌ መመለስ ግድ ሆነባቸው:: ሰላሌ ከመጡ በኋላ ከደጃዝማች አበራና ከሌሎች ወዶ ዘማች ፈረንጆች ጋር ተሰነባብተው ወደ ጃርሶ አመሩ::
አቢቹ ወደ ጃርሶ ሲሄድ ከደጃዝማች አበራ ለእናቱ የሚሰጥ ደብዳቤ ተቀብሎ ነበር:: የደብዳቤውን ይዘት አዶልፍ ፓርለሳክ ሲገምት ሁለት ልጆቿን ላጣችው እናት ማጽናኛ እና የልጆቿን ጀግንነት የሚገልጽ ሊሆን ይችላል ብሏል:: ሁለት ልጆቿን ያጣችው እናት በጀግናው ልጇ አቢቹ እንደምትጽናና ጥርጥር የለውም:: ከዚህ በኋላ ያለው የአቢቹ ታሪክ እምብዛም የሚታወቅ አይደለም:: ከላይ የቀረበው ታሪክም ቼኮስላቫኪያዊው አዶልፍ ፓርለሳክ በቦታው ተገኝቶ የታዘበውን ከከተበው የተወሰደ ነው::
ሳምንቱ በታሪክ
የጃንሆይ አጎት ሞት
የጃንሆይ አጎት ደጃች ወልደ ሥላሴ ታህሳስ 13 ቀን 1922 ዓ.ም ለመንግሥት ሥራ ወደ ደሴ ተጉዘው ነበር። በአውሮፕላን በመመለስ ላይ እያሉ ግን አደጋ ተፈጥሮ ቀበቶ ሳያስሩ ቆመው ሲፎክሩ አይሮፕላኑ ሲያርፍ ራሳቸውን በኃይል ስለመታቸው ከተሳፋሪዎቹ መካከል እሳቸው ብቻ በአደጋው ሞቱ።
ስለሆነም በአይሮፕላን አደጋ በመሞት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እኒሁ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ አጎት የራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ወንድም
ደጃች ወልደ ሥላሴ መሆናቸው በታሪክ መመዝገቡን የሰዋሰው መረጃ ያመላክታል።
የሊቢያ ነጻነት
የቀድሞዋ የኢጣልያ ቅኝ ግዛት የነበረችው ሊቢያ ታህሳስ 14 ቀን 1944 ዓ.ም ሉዐላዊ ነፃ ሀገር መሆኗ ታወጀ፤ ቀዳማዊ ኢድሪስም
የሀገሪቱ ንጉሥ ሆኑ።
ንጉሥ ኢድሪስ ከፈረንጆቹ 1951 እስከ 1963 ሊቢያን መርተዋል::
የሀገሪቱ መንግሥትም የተባበሩት የሊቢያ ስርወ መንግሥት ይባል ነበር:: በኋላ የሊቢያ ሥርወ መንግሥት ብቻ ተባለ::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


