አናቢዎቹ

0
30

ንቦች ስነ ምሕዳርን ከማስተካከል ባለፈ ለሰው ልጆች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ይሰጣሉ፤ በንፋስ አማካኝነት ርክበ ብናኝ (Pollination) ለማድረግ የማይችሉ ዕፅዋት እና አዝዕርት በንቦች አማካኝነት የወንዴ እና የሴቴ ፅጌን በማገናኘት ለዕፅዋት ሕልውና መቀጠል እንዲሁም አዝዕርት ፍሬ እንዲያፈሩ ትልቁን ሚና ይጫወታሉ። ይህ ደግሞ ንቦች ማር ከማዘጋጀት ባሻገር የሰው ልጅ በሕይወት እንዲኖር አይተኬ ሚናን እንደሚጫወቱ ያመላክታል።

ማር ባለው ተፈጥሯዊ ይዘት ከምግብነት እስከ መድኃኒትነት በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል:: በአማራ ክልል ከጥቅምት ወር ጀምሮ ማር የሚቆረጥበት ወይም የማር ምርት በስፋት የሚሰበሰብበት ወቅት ነው:: ጥራት እና ብዛት ያለው የማር ምርት ለማግኘት ደግሞ በጥንቃቄ እና በትጋት መሥራት እንደሚያስፈልግ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ንብ አናቢዎች ሐሳባቸውን በስልክ አጋርተውናል። ታታሪነታችንም እንደ ንቦች ሊሆን ይገባል ነው ያሉን::

ሐሳባቸውን ለበኩር ካጋሩን ንብ አናቢዎች መካከል በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ድባይታ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ስለሺ አረጋ አንዱ ናቸው። አቶ ስለሺ ማር በማምረት ሥራ ላይ ተሰማርተው መሥራታቸው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ እንዳስቻላቸው አጫውተውናል:: ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በንብ ማነብ እንደተሰማሩም ነግረውናል።

ወደ ሥራዉ ከመግባታቸው በፊት የቀን ሥራ እየሠሩ ነበር የሚተዳደሩት፤ የሚያገኙት ገንዘብም የዕለት ፍጆታን እንኳን  እንደማይሸፍን የተናገሩት አቶ ስለሺ ለኑሯቸውም ፈተና እንደነበር አስታውሰዋል። ንብ ማነብን ከጀመሩ በኋላ ግን ውጤት እንዳስመዘገቡ ጠቁመዋል፤ ሁሉም ሥራ ጥንካሬን እና ብርታትን ይጠይቃል የሚሉት አቶ ስለሺ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀን ሥራ ሠርተው ባገኟት 30 ብር ነበር አንድ ቀፎ ንብ በመግዛት የንብ ማነብ ሥራውን የጀመሩት። የመጀመሪያውን ምርትም 400 ብር እንደሸጡ ነው የገለጹት።

እንዲህ እንዲያ እያሉ የመጡበት መንገድ ተቃንቶ በአሁኑ ወቅትም 150 ዘመናዊ፣ 100 ባሕላዊ እና 20 የሽግግር የንብ ቀፎ ባለቤት ሆነዋል:: ከአንድ የንብ ቀፎም ከ35 እስከ 40 ኪሎ ግራም ማር ያገኛሉ:: በቀጣይ ሥራውን የማስፋፋት ሐሳብ እንዳላቸውም ነግረውናል።

አቶ ስለሺ እንደነገሩን ከባሕላዊ ወደ ዘመናዊ ንብ ማነብ መሸጋገራቸው የተሻለ የማር ምርት አስገኝቶላቸዋል፤ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ማር በመሸጥ ገቢም ያገኛሉ።

ከማር በተጨማሪም ከንቦች የሚገኝ ሰም እና ሌሎች ጥቅሞች እንዳሉ ጠቅሰዋል። በገጠር ይኖሩ የነበሩትን አራት ልጆቻቸውን ማር ሸጠው በሚያገኙት ገቢ በከተማ ደረጃውን የጠበቀ ቤት ሠርተው ልጆቻቸውን እያስተማሩ መሆኑንም ከበኩር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የሚያመርቱትን ማር ጥራቱን ጠብቀው ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡ የሚናሩት አቶ ስለሺ ማሩም ከተቆረጠ በኋላ በማጣራት ሰሙን በመለየት ለየብቻ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ነው የገለጹት::

አቶ ስለሺ እንደተናገሩት ጎንደር፣ ሆለታ፣ ጎርጎራ እና ጅማ ድረስ ሄደው ተሞክሮ ቀስመዋል፤ በጅማ ከተማ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን በመሳተፍም ተሞክሮን አግኝተዋል።

ሌላው በስልክ ሐሳቡን ያጋራን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደምቢያ ዳርና ጋውርና ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ሙሉቀን መልካሙ ነው። ከዐሥር ዓመታት በላይ የተሻገረው የንብ ማነብ ሥራው ውጤት አስገኝቶለታል፤ በከተማ የተሻለ ቤት ሠርቷል፣ የእህል ወፍጮ እንዲገዛም አስችሎታል።

ወጣት ሙሉቀን ንብ ማነብ የሙሉ ጊዜ ሥራው ነው፤ ከአንድ ዛፍ ላይ ሰፍሮ ባገኘው የንብ መንጋ ተነስቶ ዛሬ ላይ የ200 ባሕላዊ ቀፎ ባለቤት ሆኗል።

ወጣቱ ለበኩር በስልክ እንደተናገረው ባለፈው ዓመት (2017 ዓ.ም) ከማር ምርት ሽያጭ 300 ሺህ ብር ገቢ አግኝቷል። ዘንድሮ ደግሞ ከ400 ሺህ ብር በላይ የማር ምርት ለማግኘት እየተጋ ነው። የንብ ቀፎውን በአግባቡ በማጠን እና በፅዳት መያዙ ደግሞ ውጤታማ አድርጎታል፤ ለሌሎችም አርዓያ ሆኗል።

ወጣት ሙሉቀን እሱ በሚያንብበት አካባቢ ዙሪያውን ንቦች ሊቀስሙት የሚችሉትን አትክልቶችን (ዕፅዋቶችን) አልምቷል። ይህም በመጠንም ሆነ በጥራት የተሻለ የማር ምርት እንዲያገኝ ረድቶታል።

የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ የንብ እና ሐር ልማት ከፍተኛ ባለሙያ ሙሐመድ ጌታሁን ለበኩር እንደተናገሩት አማራ ክልል በኢትዮጵያ ከፍተኛ የማር ምርት ከሚገኝባቸው ክልሎች አንዱ ነው። ክልሉ በሁሉም አካባቢ ለንብ እርባታ ተስማሚ ስነ ምህዳር አለው።

ከፍተኛ ባለሙያው እንዳሉት ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ የማር ምርት የአማራ ክልል 23 በመቶ ያህሉን ድርሻ በማበርከት ቀዳሚ ነው ብለዋል።

ክልሉ ለንብ ሃብት ልማት ሥራ ምቹ የሆነ የአየር ንብረት እና የተለያዩ የቀሰም ዕፅዋቶች ያሉበት አካባቢ በመሆኑ የማር ምርት አቅሙ እጅግ ከፍተኛ ነው። ከተለያዩ የእጽዋት  አበባዎች የተለያየ ጣዕም እና ቀለም ያለው ማር ይመረታል። ለአብነትም ከ800 በላይ የሚሆኑ ለንብ ቀሰም የሚያገለግሉ ዕፅዋቶች እንዳሉ አመላክተዋል። አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሕብር ንብ (የንብ መንጋ) (በባሕላዊ፣ በዘመናዊ እና በሽግግር ቀፎ) እንዳለም አክለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት 30 ሺህ ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ 29 ሺህ ቶን መመረቱን ያነሱት ከፍተኛ ባለሙያው በ2018 በጀት ዓመት 33 ሺህ 333 ቶን ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ታኅሳስ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 23 ሺህ 700 ቶን የማር ምርት ተመርቷል። ማር በዓመት ሁለት ጊዜ በመኸር እና በበልግ የሚቆረጥ (የሚመረት) እንደሆነም አመላክተዋል።

የንብ ማነቢያ እና ምርት ማቀነባበሪያ ግብዓት አቅርቦትን በማሻሻል የማር ምርትን (በመጠን እና በጥራት) ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም ገልፀዋል። ለዚህም ከድጋፍ ባለፈ ሥልጠና እና የግንዛቤ ፈጠራ ለአናቢዎች እንደተሰጠ ጠቁመዋል።

በክልሉ 82 በመቶው የማር ምርት በባሕላዊ ቀፎ ነው የሚመረተው፤ በዘመናዊ መንገድ የሚመረተው 18 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው።

በመሆኑም ዘመናዊ እና የሽግግር ቀፎዎችን ለማስፋት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ ሙሐመድ ነግረውናል። የክህሎት እና የዕውቀት ክፍተት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅርቦት እና ተደራሽነት በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶች ናቸው።

በዘርፉ ለተሰማሩ ግለሰቦች የተሻሻሉ ዘመናዊ ቀፎዎችን በማቅረብ በመጠን እና በጥራት የማር ምርትን እንዲያመርቱ እየተደረገ ያለውን መልካም ጅምርም አንስተዋል::

አግባብነት የሌለው የፀረ አረም እና ፀረ ተባይ ርጭት በንቦች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሙሐመድ ይህን ችግር ለመፍታት ግንዛቤ እና የምክር አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል። በቅርቡ የፀደቀው አዋጅ እና መመሪያ ተግባራዊ ሲደረግ ችግሩ እንደሚፈታም ጠቁመዋል።

ፀረ አረም እና ፀረ ተባይ አይረጭ አይባልም ያሉት ባለሙያው ንቦችን እንዳይጎዳ ሰብል አምራቹ እና አናቢው ተናበው እና ተመካክረው በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን ክልሉ ከፍተኛ የማር ምርት አቅም ቢኖረውም የግብርና ኬሚካሎች (ፀረ-ተባይ) ርጭት፣ የዘመናዊ ቀፎ አቅርቦት እጥረት እና የገበያ ትስስር ችግር አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ወይም ለትላልቅ ፋብሪካዎች ለማቅረብ ያለው ዕድል ውስን መሆን ዘርፉን ፈትነውታል።

ችግሩን ለመፍታትም ባዛሮችን በማዘጋጀት ከኤክስፖርተሮች (ለውጪ ገበያ አቅራቢ ነጋዴዎች) ጋር የማሥተሳሰር ሥራ እየተከናወነ ነው። ከማሕበራት እና ከንግድ ቢሮ ጋር የገበያ ትሥሥር እንዲፈጠርላቸው እየተሠራ ነው።

እንደ አቶ ሙሐመድ ማብራሪያ የአማራ ክልል ማር ከፍተኛ ጥራት ያለው በመሆኑ በገበያ ላይ ተፈላጊ ነው። ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ ገበያ በማቅረብም (ማር እና ሰም) የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ጉልህ ድርሻ አለው።

ማር አምራቾች ጥራት ያለው ምርት ለተጠቃሚ ለማቅረብ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እና ትክክለኛውን የአቆራረጥ ዘዴ መከተል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል::

 

መረጃ

ንብ ለማነብ መደረግ የሚገባቸው ነጥቦች

ንብ የማነብ ቦታ ሲወሰን ለንብ ቀሰምነት ጠቃሚ የሆኑ በተለያዩ ወቅቶች የሚያብቡ እፅዋቶች በአካባቢው ማልማት።

መሬቱ  ረግረጋማ ያልሆነ እና በጎርፍ የማይጠቃ።

በማነቢያ አካባቢ ውኃ መኖሩን ማረጋገጥ።

ቆሻሻ ከሚጠራቀምበት ቦታ እና ከመኖሪያ አካባቢ የራቀ።

የፀረ አረም እና የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት በብዛት የማይካሄድበት።

ኬሚካል ከሚያተኑ (ከሚለቁ) ፋብሪካዎች የራቀ።

ጉንዳን እና መሰል የንብ ጠላቶች የማያጠቃው ቦታ መሆን እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የታህሣስ 13  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here