ቱሪዝምን በማነቃቃት ሀገርን ማሳደግ ይገባል!

0
23

ቱሪዝም  የስራ እድል ፈጠራን በማበረታታት በርካታ ወጣቶች አካባቢያቸውን ሳይለቁ ልዩ ልዩ የፈጠራ ስራወቻቸውን እና ባህላዊ መገለጫወቻቸውን እየሰሩ ለገበያ በማቅረብ ገቢ እንዲፈጥሩ በማስቻል ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድራሉ፡፡ በዚህም የምጣኔ ሀብታቸውን ያሳድጋሉ፣ ባህላቸውንና መገለጫወቻቸውንም ያስተዋውቃሉ። ይህም እደ ጥበባትን፣ ልማዶችን፣ ወጎችንና ባህልን ባሉበት ተጠብቀው እንዲቆዩ በማድረግ ማህበራዊ ግንኙነቶች እና የባህል ልውውጦች እንዲበራከቱ እንዲጎለብቱ ያግዛል።

ቱሪዝም ከምጣኔሃብታዊ ጠቀሜታው ባሻገርም በሰወች፣ በባህል እና በወጎች መካከል ያለውን ትስስር ያጠናክራል፡፡ በተለያዩ ባህሎች መካከል እንደ ድልድይ በመሆንም ያገለግላል። ቱሪዝም ብዝሃነትንም ያበለጽጋል በማህበራዊ እና ማህበራዊ እድገት ውስጥ አወንታዊ ተጽእኖ በመፍጠር በኩል ድርሻዉ ከፍ ያለ ነው።

ቱሪዝም ህዝባዊ እና ማህበራዊ መስተጋብርን  በመፍጠር እና የባህል ትውውቅ እንዲኖር በማድረግም ለምጣኔ ሃብታዊ እድገት ከፍተኛ አበርክቶ አለው። በዚህ ዘርፍም በርካታ የአለም ሃገራት ዘርፉን ዋነኛ የምጣኔ ሃብት ጀርባቸው ያደረጉ በመኖራቸው እና ጠቀሜታው በመጉላቱ ጭስ አልባዉ ኢንዱስትሪ እስከመባል ድረስ የደረሰ ዘርፍ ነው። በቱሪዝም በርካታ ሃገራት ተጠቃሚ እየሆኑ ሲሆን በሃገራችንም ተስፋ የተጣለበት ዘርፍ በመሆኑ ዘርፉን ልንጠቀምበት ያስፈልጋል።

የአማራ ክልል በቱሪዝም ሀብቱ ፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ የመስህብ ሃብቱ ለክልሉ ብሎም ለሃገራችን የሚያበረክተው አስተዋጾው የጎላ ነው።ክልሉ በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ የመስብ ሃብቶችን አቅፎ የያዘ በመሆኑ እነዚህን ሃብቶች በአግባቡ በመጠቀም ኢኮኖሚውን ማሳደግ ያስፈልጋል።

ክልሉ በበርካታ የመስህብ ቦታዎች፣ ሃማኖታዊ ክብረ በዓላት፣ ባህላዊ ክዋኔዎችና ሁነቶች ያሉት፣ ለጎብኝዎች   ምቹ የአየር ንብረት፣ ውብና እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ያለበት ክልል መሆኑን እንግዶች የሚመሰክሩለት በመሆኑ ይህንን ሃብት አስከብሮና አስጠብቆ በማስቀጠል ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ማግኘት ያስፈልጋል። ይሁን እንጅ ክልሉ ከዘርፉ ማግጘነት  የሚገባውን ጥቅም በልኩ እያገኘ አይደለም፡፡

በዚህ ቁጭት የገባው የክልሉ መንግስትም ለዘርፉ ታላቅ ትኩረት በመስጠት በክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ እስትራቴጅክ እቅድ ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉን በማካተት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል። ከዘርፉ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘትም መዳረሻ ቦታዎችን ምቹ ማድረግ፣ የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ፣ ለእንግዶች ምቹ የሆነ አቀባበል በማድረግና የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም በመልካም መስተንግዶ ተቀብሎ በመሸኘት ዘርፉን ማሳደግ ያስፈልጋል።

በመሆኑም የፊታችን ታህሳስ 29 ልደትን በላልይበላ ከሚከበረው በዓል ጀምሮ በቀጣይ ወራት በተከታታይ በሚከበሩ በዓላትን ለመታደም ክልሉን መዳረሻቸው ለሚያደርጉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በመልካም መስተንግዶ ተቀብሎ ለመሸኘት ክልሉ ከወዲሁ በቂ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ የቱሪዝም ሀብታችን እንዲጠበቅና የሚገኘው ገቢ እንዲያድግና ከዘርፉም ተገቢውን ጥቅም እንዲገኝ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

 

በኲር የታህሣስ 13  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here