ጣልቃ ገብነት ሀገራትን እያፈራረሰ ነው

0
149

ሀገራት በሌላ ሀገር ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡት በበርካታ ምክንያቶች ነው:: በደኅንነት ፍላጎት ማለትም የጎረቤት ሀገር መፍረስ በራሳቸው ደኅንነት ላይ አደጋ እንዳይፈጥር፣ ሽብርተኝነትን  ለመከላከል እና መሰል ምክንያቶችን በማንሳት ጣልቃ ይገባሉ:: ሌላው ክልላዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ የኃይል እና ተፅዕኖ የማስፋፋት ፍላጎት መኖር ነው:: በተጨማሪም ኢኮኖሚና ሀብት ለማካበት ሲሉ ጣልቃ ይገባሉ:: ለነዳጅ፣ ወርቅ፣ ጋዝ፣ የንግድ መንገዶችን በመዘርጋት የመሣሪያ ንግድ ለማጧጧፍ፣ ፖለቲካዊ እና በርዕዮተ ዓለም ምክንያት በማስቀመጥ ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸውን መንግሥታት መደገፍ እና የተቃዋሚ ሀሳቦችን ለመከላከል በሚልም ጣልቃ ይገባሉ::

በዚህም ምክንያት በርካታ ሀገራት ፈራርሰዋል፤ በርካታ ዜጎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል:: በአሁኑ ወቅትም በሀገራት ጣልቃ ገብነት ምከንያት የጦርነት ሰለባ እየሆኑ ነው፤ አደጋም አንዣቦባቸዋል::

በሀገራት ጣልቃ ገብነት ምክንያት ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው ሀገራት መካከል ሱዳን፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታን እና ኢራቅ ይገኙበታል::

 

ሱዳን

የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር ሀሰን ኣል-በሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ወታደራዊ መንግሥት ነው በትረ ስልጣኑን የያዘው:: ይህን ተከትሎም የስልጣን ሽኩቻ ተፈጥሮ ሀገሪቱን ለዳግም ጦርነት ዳርጓታል::

በጎረቤት ሀገር ሱዳን ላይ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በምንመለከትበት ጊዜ የሱዳን ጦር ሠራዊትን (SAF) ግብጽ ስትደግፍ የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉን ደግሞ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች (ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ) እና ሌሎች ሀገራት ይደግፉታል::

የጦርነቱ መነሻ የሥልጣን ሽኩቻ ቢሆንም ሌሎች ሀገራት የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ጣልቃ ገብተዋል:: ለወርቅ ንግድ እና ክልላዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ባላት ፍላጎት  የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን  በገንዘብ፣ በጦር መሣሪያ እና ሎጂስቲክ ድጋፍ አድርጋለታለች:: በሊቢያ የሀፍታር ኃይሎችም (በሊቢያ የሚገኝ አንደኛው ታጣቂ ቡድን) የድንበር ግንኙነት ተፅዕኖ ገፍቷቸው የጦር መሣሪያና ተዋጊ ወታደሮችን ድጋፍ አድርጓል::  የሩሲያው ዋግነር (Wagner) ቡድን ከፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ ጋር የወርቅ ንግድ ለመፈጸም የጦር መሣሪያ እና የምክር ድጋፍ (በተዘዋዋሪ) ሰጥቷል::

ግብፅ ደግሞ የሱዳን ሠራዊትን (SAF) ከዓባይ ውኃ ደኅንነት ጋር በማያያዝ የሠራዊት ስልጠና እና የፖለቲካ ድጋፍ አድርጋለች::

 

ሊቢያ

እ.አ.አ በ2011 በተካሄደው የሊቢያ የርስ በርስ ጦርነት እንግሊዝ፣ አሜሪካ እና ፈረንሳይ (በተባበሩት መንግሥታት ፈቃድ) በሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ አየር ኃይል በኩል ድብደባ ፈጽመውባታል::

በወቅቱ የሊቢያ መሪ የነበሩት ሙአመር ጋዳፊን በሚቃወሙ የምዕራባዊያን ሀገራት አማካኝነት ተቃዋሚ ቡድኖች የጦር መሳሪያ፣ የሥልጠና እና መረጃ (intelligence) እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ዕውቅና በማግኘታቸው ወደ ታጣቂ ኃይል ተውጠዋል::

የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የጋዳፊ መንግሥት በፍጥነት እንዲፈርስ አድርጓል:: ይሁንና ከጋዳፊ መወገድ በኋላ ሊቢያ ልትረጋጋ አልቻለችም:: ቋሚ መንግሥት ለመመሥረት  የተደረገው ጥረትም ፍሬ አላፈራም:: በየሰፈሩ አንጃዎች ተፈጥረው ሰዎች የሚታገቱባት እና በሃብት ተንደላቀው ይኖሩ የነበሩ ዜጎቿ በድህነት አረንቋ የሚማቅቁባት ሀገር ሆናለች::

በወቅቱ መጀመሪያ ላይ የኔቶ ዓላማ ንጹሐንን መጠበቅ የሚል ነበር:: ውሎ ሲያድር ግን ጋዳፊን ከሥልጣናቸው ማስወገድ ሆነ::  ይህም የጋዳፊ መንግሥት መውደቅን በቀጥታ አስከትሏል::

ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ቱርክ እና ሩሲያ በሊቢያ የርስበርስ ጦርነት ጣልቃ ገብተው ለሚደግፉት ኃይል የጦር መሣሪያ እና ስልጠና እንደሰጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ::

 

የመን

በየመን ከጎርጎሮሳዊያኑ 2011 በኋላ የተቋቋመው መንግሥት ደካማ ነበር:: ሃውቲዎች (ዛይዲ ሺዓ) በሰሜን የመን ለዘመናት መገለል ደርሶባቸው እንደኖሩ ይናገራሉ:: በዚህም ምክንያት አማጺ ቡድን ፈጥረዋል:: የተገደበውን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶቻቸውን ለማስመለስም ነፍጥ አንግበው ከገዢው መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ ገቡ:: በተጨማሪም ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና የነዳጅ እጥረት የመናዊያንን ወደ አመፅ መርቷቸዋል:: ሆኖም ዓለም አቀፍ ፍላጎቶች ሀገሪቱን ወደ ከፋ ጦርነት ውስጥ አስገብቷታል::

ኢራን በፖለቲካና በወታደራዊ ቁሳቁሶች ለሃውቲዎች ድጋፍ እንደምታደርግ ይነገራል:: በሌላ በኩል ሳዑዲ አረቢያ ሃውቲዎችን የኢራን ወኪል አድርጋ ስለምትመለከታቸው እ.አ.አ በ2015 በየመን መንግሥት ግብዣ በጦርነቱ ተሳትፋለች:: አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ መሣሪያ ስለሚሸጡ ሰላም እንዳይመጣ፣ ግጭቱ እንዳይቆም እንደሚያበረታቱም ይነገራል:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ቀይ ባሕር ላይ በሚጓዙ መርከቦች ላይ ሃውቲዎች ጥቃት አደረሱ በሚል አሜሪካ የመንን መደብደቧ የሚታወስ ነው::

በሀገራት ጣልቃ ገብነት እየወደመች የምትገኘው የመን ታዲያ አሁንም በወታደራዊ ቡድኖች እየታመሰች ትገኛለች፤ ይህም ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እጦት ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ነው ተንታኞች የሚናገሩት:: የቀይ ባሕር አካባቢ የሰላም እጦት የመን ውስጥ ባሉ ታጣቂ ቡድኖች ጥቃት ምክንያት መሆኑን ልብ ይሏል::

 

ሶሪያ

በሶሪያ ጦርነት እና አለመረጋጋት አሁንም ድረስ ብዙ ዓለም አቀፍ ኃይሎች በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብተዋል:: የሶሪያ መንግሥትን የደገፉ ሀገራት ለአብነትም ሩሲያ እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ በባሽር አልአሳድ መንግሥት ጥያቄ የአየር ጥቃት ፈጽማለች፣ ወታደሮችን እና የጦር መሣሪያዎችንም ልካለች፤ በመጨረሻም የበሻር ኣል-አሳድ መንግሥትንም አድናለች:: የኋላ ኋላ በሽር አል አሳድ ከስልጣን ሲወገድ ደግሞ ወደ ሀገሯ ወስዳዋለች:: በተመሳሳይ ኢራንም ሶሪያን እንደ ክልላዊ አጋር ትመለከታለች::

በሌላ በኩል የበሻር ኣል- አሳድ መንግሥትን የተቃወሙ ሀገራትም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሶሪያ ጦርነት ተሳታፊ ነበሩ:: ለአብነትም አሜሪካ አይ ኤስ ላይ የአየር ጥቃት በመፈጸም የኩርድ (SDF/YPG) ኃይሎችን ደግፋለች። በምሥራቅ ሶሪያም ወታደሮቿ ይገኛሉ።

ቱርክ በሰሜን ሶሪያ ቀጥታ ጦር በመሳተፍ የኩርድ ኃይሎችን ለመከላከል አንዳንድ የተቃዋሚ ቡድኖችን ደግፋለች:: ሳዑዲ አረቢያም ለተቃዋሚ ቡድኖች ፖለቲካዊና የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች::  ኳታርም የአሳድ መንግሥትን ለሚቃወሙ ኃይሎች ድጋፍ አድርጋለች::

ሌሎች ጣልቃ የገቡ ኃይሎችን በምንመለከትበት ጊዜም እስራኤል በሶሪያ ውስጥ በኢራን የሚደከገፈውን የሄዝቦላህ ዒላማዎችን ለመምታት በሚል ሶሪያን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስትደበድብ ቆይታለች።  ይህም በቀጥታ በጦርነቱ ባትሳተፍም ሀገሪቱን በማውደም እና በማፈራረስ ተፅዕኖ አሳድራለች። ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ጀርመን በአይ ኤስ አይ ኤስ (ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራ ቡድን) ላይ የአየር ጥቃት ከአሜሪካ ጋር በትብብር ፈጽመዋል::

 

አፍጋኒስታን

ሌላው በተደጋጋሚ የውጭ ኃይል ተፅዕኖ የታየው በአፍጋኒስታን ውስጥ ነው::  በየዘመኑም የውጭ ኃይሎች የተለያዩ ቡድኖችን ደግፈዋል:: ይህም የአፍጋኒስታን ውስጣዊ ግጭት እንዳይፈታ አድርጎታል:: ጦርነቱ እንዲረዝም እና በእያንዳንዱ ዘመን አዲስ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል::

የአፍጋኒስታን ጦርነት የውስጥ ችግር ብቻ ሳይሆን ተደጋጋሚ የውጭ ጣልቃ ገብነት ያራዘመው ግጭት ነው::

እ.አ.አ ከ1979 እስከ 1989 ባለው ጊዜ በአፍጋኒስታን የሶቪየት ሕብረት ጣልቃ ገብነት ነበር:: ሶቪየት ሕብረት የአፍጋኒስታንን የኮሚኒስት መንግሥትን ለመደገፍ ነበር አፍጋኒስታን የገባችው::

የሶቭየት ሕብረትን መግባት ያልወደዱት ምዕራባዊያን በተለይ አሜሪካ እንዲሁም የአፍጋኒስታን ጎረቤቶች ፓኪስታን እና ሳዑዲ አረቢያ የሙጃሂዲን ኃይሎች (ተቃዋሚ ኃይሎች) አቋቋሙ:: ጦርነቱ 10 ዓመታት ቆይቶ ሶቪየት ሕብረት በ1989 አፍጋኒስታንን ለቃ ወጥታለች:: በውጤቱም ሀገሪቱ ስትፈራርስ ማዕከላዊ መንግሥቱም ደካማ ሆኖ ቀጥሏል::

እ.አ.አ ከ2001 እስከ 2021 በነበረው ጦርነትም የአሜሪካ እና የኔቶ ጣልቃ ገብነት የታየበት ነበር:: አሜሪካ እ.አ.አ በ2011 የሽብር ጥቃት ከደረሰባት በኋላ በአፍጋኒስታን ላይ ጥቃት አድርሳለች:: ጥቃቱን የፈጸመችውም አል- ቃዒዳን ለማጥፋት በሚል ነበር::

የሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶም ለ20 ዓመታት የወታደራዊና የፖለቲካ ድጋፍ አድርጓል:: በ2021 እ.አ.አ የውጭ ኃይሎች ከወጡ በኋላ ታሊባን እንደገና ስልጣን ያዘ:: በሀገሪቱ በነበረው ጦርነት እና የውጭ ጣልቃ ገብነት ብዙ ሕይወት ጠፍቷል፤ መንግሥታዊ መዋቅሮችም አልተጠናከሩም:: በዚህም የሀገሪቱ ዜጎች በስቆቃ እንዲኖሩ ሆነዋል::

በአጠቃላይ ዓለማችን በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች እየታመሰች ትገኛለች፤ በአሁኑ ወቅትም በርካታ ሀገራት በጦርነት ውስጥ ይገኛሉ:: ሀገራት ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ደግሞ  በሀገራት የሚካሄዱ ጦርነቶችን አባብሰውታል::

 

የመረጃ ምንጮቻችን አልጀዚራ፣ ቢቢሲ እና አናዶሉ ናቸው::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የታህሣስ  20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here