ምን ተረከብን? ምንስ እናስረክብ?

0
158

አቶ ጌትነት ሙላት ይባላሉ፤ ነዋሪነታቸው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ  በሚገኝ የገጠር ቀበሌ ነው፡፡ በ70ዎቹ መጨረሻ የዕድሜ ክልል ከሚገኙት አዛውንት ጋር የተገናኘነው ዘመድ ጥየቃ ወደ ባሕር ዳር ከተማ በእንግድነት በመጡበት ወቅት ነው፡፡ ስለ ሽምግልና (አስታራቂነት) ሐሳብ አነሳንላቸው። “እሱማ ጥርሴን የነቀልኩበት ነው” በማለት በርካቶችን ስለማስታረቃቸው አጭር ምላሽ ሰጡን።

“ሀገራችን እኮ የፍትሕ ምሳሌ ነበረች፤ የበደለ እና የተበደለ ያለማንም የጸጥታ አካል እጀባ በአካባቢያቸው ወደሚኖሩ ሽማግሌዎች (አስታራቂ)) ዘንድ ሄደው  ፍትሕን ፍለጋ  የሚያንኳኩባት፣ በእራፊ ጨርቅም እጅ ለእጅ ተቆራኝተው አብረው እየበሉ እና እየጠጡ፣ አብረውም እያደሩ ወደ ፍትሕ አካል የሚሄዱ ለእውነተኛ ፍትሕ የቆሙ ዜጎች ሀገር ነበረች” ሲሉ ነበር ሐሳባቸውን ያጠናከሩልን፡፡ ለሐሳቡ መነሻ የሆነን ደግሞ በሀገራችን በተለይም በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት ለምን ከሽማግሌ በላይ ሆነ? የሚለው ነበር፡፡

አዛውንቱ እንዳሉት ግጭት ሁልጊዜም የሚኖር እና የሚቀጥል ነው፤ በአሁኑ ወቅት ትልቁ ፈተና ግን የችግር መፍቻ ሀገር በቀል ሥርዓቶቻችን መዳከማቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በሀገራችን ያለውን ግጭት ነው ማሳያ አድርገው ያነሱት፡፡

“የነገር ጠማማ በሽማግሌ ይታረቃል፣ ሰማይ ቢቀደድ በሀገር ሽማግሌ ይሰፋል፣ ድሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ” የሚሉ ሀገርኛ አባባሎች ኢትዮጵያዊ መሠረት ያላቸው ለፍትሕ ያለንን ቦታ አመላካቾች ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ የሽምግልና ሥርዓታችን ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሀገር አቀፍ ምክክር በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፤ በምክክሩም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡ ሐሳባቸውን የሰጡን ተሳታፊዎች “በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በርካታ የችግር አፈታት ሥርዓት ላላት ሀገራችን አይመጥንም፤ ከሽማግሌ በላይ መሆን አልነበረበትም” ብለዋል፡፡

አቶ መሐመድ የሱፍ የሐረር ከተማ አስተዳደር የሀገር ሽማግሌዎች ሊቀመንበር ናቸው፤ ሽምግልና እና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ያነሱት አቶ መሐመድ፤ “የሀገር ሽማግሌዎች በየዘመናቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍትሔ በመስጠት ባለውለታ ናቸው፤ ሽምግልና (ማስታረቅ) ደግሞ እውነት ላይ በመቆም ችግሮችን የሚፈታ ዕሴታችን ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የተከሰቱ ግጭቶች እንዳሳሰባቸው እና እንዳሳዘናቸው የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው፤ ችግሮች ሁሉ ግን ከሽማግሌዎች አቅም በላይ መሆን እንደማይችሉ ጠቁመዋል፡፡

“የተከበረች ሀገርን ተረክበናል፤ እኛ ደግሞ ለነገዎቹ ከነሙሉ ክብሯ የማስረከብ ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን” ነው ያሉት፡፡

“በተለይ በከተሞች ለሽማግሌዎች ታዛዥ ጠፍቷል! ሽማግሌ የማያከብር ትውልድም እየተፈጠረ ነው!” ያሉን ደግሞ ከአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ጫኔ መንገሻ ናቸው። “ቢሆንም ግን ችግርን ለመፍታት አሁንም ሁነኛው መፍትሔ ሽምግልና ነው” ብለዋል።

አቶ ጫኔ እንዳሉት በተለይ የፍትሕ ሥርዓት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ዋናው የችግር መፍቻ ዘዴ ነው፡፡ ያለአንዳች ክፍያ የሚደረግ ሀገራዊ ግዴታን የመወጣት ተግባር መሆኑን በማንሳትም ይህም የኢትዮጵያዊነት ልዩ መገለጫ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡ “በአሁኑ ወቅት ከገባንበት ቀውስ ለመውጣት የሀገር ሽማግሌዎች ከባድ ኃላፊነት አለብን፤ መስዋዕትነት ቢያስከፍልም ከችግር የምንወጣበት ሁነኛ መንገድ ነው” ብለዋል፡፡

“እንኳን እኛ ግመሎቻችንም ስለ ሰላም ይዘምራሉ” ሲሉ ሐሳባቸውን የጀመሩልን ደግሞ ከአፋር ክልል የመጡት የሀገር ሽማግሌ  አሕመድ ያሲን ናቸው። ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ በሽምግልና እንደሚያምኑ አቶ አሕመድ ተናግረዋል፤ የአፋርን ተሞክሮ መነሻ አድርገው እንደተናገሩት ማንኛውም ችግር ሲፈጠር በቅድሚያ ወደ ሽምግልና ነው የሚኬደው። ላጠፋ ቅጣት፣ ለተበደለ ደግሞ ካሳ ይሰጣል። “ወጣቱም ይህን ዕሴት መውረስ አለበት” ብለዋል።

“ምን ተረከብን? ምንስ እናስረክብ?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ አሕመድ፤ “የቀደሙት ኢትዮጵያዊያን ሀገራችንን  ከነክብሯ አስረክበውናል፣ እኛ ደግሞ ለነገው ትውልድ የተከበረች ሀገርን የማስረከብ አደራ አለብን” ነው ያሉት።

ሌሎች የምክክሩ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌዎች ከፖለቲካ፣ ከዘር እና ከሃይማኖት ገለልተኛ በመሆን እና እውነት ላይ በመቆም የሚነሱ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባቸው ጠይቀዋል።

የሽምግልና ሥርዓት የሀገር አንድነትን በማጠናከር በተለይ በየአካባቢው የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት ሚናው የላቀ መሆኑንም አንስተዋል።

በኢፌዴሪ የሰላም ሚኒሥቴር እና በአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ትብብር “ማኅበራዊ ሃብቶቻችን ለዘላቂ ሰላም እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን’’ በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው በዚሁ  ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒሥቴር ሚኒሥትር አቶ አሕመድ እድሪስ፣ የአማራ ክልል ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ በርካታ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) ግጭት በግለሰቦችም ሆነ በቡድን መካከል ሊፈጠር  የሚችል ክስተት መሆኑን ጠቁመዋል፤ “ግጭቶችን በሀገር ሽማግሌ መፍታት ለዘመናት የዘለቀ የኢትዮጵያውያን የመልካም ዕሴት መገለጫ ነው” ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተከሰተው ችግር በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ የሀገር  ሽማግሌዎች ሚና  የላቀ እንደነበር ነው የገለጹት። ክልሉ ወደ ተሟላ ሰላም እንዲመለስ  የሀገር ሽማግሌዎች የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

“ባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች የማኅበራዊ ዋስትና መሠረቶች ናቸው” ያሉት ደግሞ የሰላም ሚኒሥቴር ሚኒሥትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)  ናቸው። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሟላ ሰላምን እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሀገር ሽማግሌዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ያጋጠማትን ችግር የኢትዮጵያ ዕሴት በሆነው የግጭት አፈታት ዘዴ እየፈታች  የመጣች ናት” ያሉት ዶክተር ከይረዲን፤ ነፍጥ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ሰላማዊ አማራጭን እንዲከተሉ ጠይቀዋል። ለዚህ ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል። መንግሥትም የሚነሱ ማናቸውንም ችግሮች በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ “የክልሉ ሕዝብ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ምክክርን እንደ ትልቅ ባሕል አድርጎ ዛሬ ላይ ደርሷል” ብለዋል፤ የበደለን ወቅሶ፣ የተበደለን ክሶ ይቅር መባባል የክልሉ ባሕል እንደሆነም ነው የገለጹት። የትኛውም ችግር ከሀገር ሽማግሌ አቅም በላይ እንደማይሆንም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት የተከሰተውን ችግር ለመፍታት የሀገር  ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ እንደ ነበር ያነሱት ዋና አፈ ጉባዔዋ የሀሳብ ልዩነቶችን እና የሚነሱ ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሰላም ሚኒሥቴር ሚኒሥትር መሐመድ እድሪስ “የሀገር ሽማግሌዎች የሀገር እና የአብሮነት ምልክቶች፣ ችግሮችን በመፍታትም ሀገርን አሻጋሪዎች ናቸው” በማለት የሀገርን ሰላም አጽንቶ በማቆየት ያላቸውን ሚና ገልፀዋል።

ሀገር የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት መሆኗን ያነሱት ሚኒሥትሩ በዘመናት ጉዞ የሚፈጠሩ ፈተናዎችን በመጋፈጥ፣ ችግሮችንም በማሸነፍ መሻገር የተቻለው አብሮነትን በማጽናት እና ሀገር በቀል መላ በመዘየድ መሆኑን ተናግረዋል።

ልዩነት በማኅበረሰብ ውስጥ የማይቀር  መሆኑን በማንሳትም ልዩነቶችን በምክክር መፍታት ደግሞ የኢትዮጵያውያን ባሕል ነው ብለዋል።

ይሁንና አሁን ላይ ነባር ሀገር በቀል ዕሴቶች እየተሸረሸሩ ስለመሆናቸው  በምክክሩ ተነስቷል። “ይህም ባለፉት ዓመታት ሀገራችን በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል” ነው ያሉት ሚኒሥትሩ።

ችግሮችን በሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ለመፍታት እንደ ሀገር ከ75 በላይ የችግር መፍቻ ሥርዓቶች በሚኒሥቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ተለይተው እየተሠራባቸው ይገኛል። አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ እንዳስቻሉም አቶ መሐመድ አክለዋል። ሚኒሥትሩ እንዳብራሩት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ምክክሮች እየተካሄዱ ነው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የሽምግልና ሥርዓቱ የራሱ መዋቅር አለመኖር፣ የገንዘብ እጥረት እና የጠነከረ መሠረት አለመኖር እንደ ሀገር  ማነቆ ስለመሆናቸው በምክክሩ ተነስቷል፤ የሽምግልና ሥርዓቱ የጠነከረ መሠረት እንዲኖረው ታዲያ የሕግ ዕውቅና  እንዲያገኝ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ዋና አፈ ጉባዔዋ ገልጸዋል።

ወደ ፊት ሀገር በሰላም ፀንታ እንድትቀጥል፣ ዜጎች በቀያቸው ተረጋግተው እንዲኖሩ፣ ሕጻናት፣ ታዳጊዎች እና ወጣቶች  ተምረው ሥራ የሚፈጥሩባት ሀገር እንድትሆን ወላጆች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መንግሥት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የታህሣስ  20  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here