ግብርናዉ የጀርባ አጥንት

0
131

በግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት አፈጻጸሟ ብራዚል በዓለም ቀዳሚ  ናት፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምግብ አስመጪነት ወደ ዓለም ቀዳሚ የምግብ ላኪነት የተሸጋገረችው ብራዚል የስኬታማነቷ  መሠረት ጠንካራ የግብርና ኤክስቴንሽን እና የምርምር ሥርዓቷ እንደሆነም የብራዚል የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን /Brazilian Agricultural Research Corporation/ የተባለው ተቋም አስነብቧል። የግብርና ኤክስቴንሽን በምርምር ማዕከላት፣ በዩኒቨርሲቲዎች እና በግብርና ተቋማት የሚገኙ አዳዲስ የግብርና ግኝቶችን፣ ቴክኖሎጂዎችን እና እውቀቶችን ወደ ተጠቃሚው  አርሶ አደር የማድረስ ሂደት እንደሆነም መረጃው አመላክቷል።

የብራዚል የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን (Embrapa) በዓለም ላይ ካሉ ቀዳሚ የትሮፒካል ግብርና ምርምር ተቋማት አንዱ ነው። በፈረንጆቹ  በ1973 የተቋቋመው ይህ የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን ለሀገሪቱ የግብርና ዕድገት ዋነኛ ምሰሶ ነው።

ኮርፖሬሽኑ ብራዚልን ከምግብ አስመጪነት ወደ ዓለም ቁጥር አንድ የምግብ ላኪነት የቀየረ ቁልፍ ተቋም ሲሆን ትኩረቱም ሳይንስን መሰረት ያደረገ ነው። ይህ ተቋም በብራዚል የግብርና ሚኒሥቴር ስር ይተዳደራል፡፡  በዋናነት ደግሞ ምርምር በማድረግ  ለግብርናው ዘርፍ እድገት ጠንካራ ተግባራትን ያከናውናል። በተለይም በሽታን የሚቋቋሙ እና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን ያፈልቃል፣ ተባይን የሚቋቋሙ ሰብሎችን በላብራቶሪ ያዳብራል፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና አያያዝን ውጤታማ ያደርጋል፣ የእንስሳት ዝርያን ያሻሽላል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ያፈልቃል፣ የተቀናጀ ግብርና  (የሰብል ልማትን፣ የደን ልማትን እና የእንስሳት እርባታን) በአንድ ላይ አቀናጅቶ  እንዲሠራም ጉልህ ሚናን ይጫወታል።

በኢትዮጵያም ግብርና የኢኮኖሚው ምሰሶ እንደሆነ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ግብርናው ከባሕላዊ አሠራር ተላቆ ወደ ዘመናዊነት እንዲሸጋገር እና ምርታማነቱ እንዲጨምር ከተፈለገ የግብርና ኤክስቴንሽን (Agricultural Extension) አገልግሎት ወሳኝ ሚናን እንደሚጫዎት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሩ ማስተዋወቅ፣ ክህሎታቸውን ማሳደግ፣ ወቅታዊ መረጃን ማቀበል እና አርሶ አደሩ በሥራው ላይ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በመለየት ለመፍትሔው ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የግብርና ትራንስፎርሜሽንን  ለማሳካትም ይህን አገልግሎት ይበልጥ ማዘመን፣ በቴክኖሎጂ መደገፍ እና ተደራሽነቱን ማስፋት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባ ይታመናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በሀገር አቀፍ የተዘጋጀውን የባለብዙ ተዋናይ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ እና አሥተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ አስተያየት መድረክ ታኅሳስ 09/2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።

በውይይቱ የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ አዋጁ ይዘት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በውይይቱ የቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት የነበረው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ከ50 ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በመሆኑም የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ አካታችነት እንዲኖረው፣ በዘርፉ ላይ ባለሀብቶችም እንዲሳተፉበት እድል ለመስጠት፣ ቀጣይነት እንዲኖረው፣ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ለማድረግ እና ምርታማነትን ለማሳደግ ሕጉ መሻሻል ማስፈለጉን ገልጸዋል።

የውይይቱ ዓላማም የባለድርሻ አካላት እና የዘርፉን ሰዎች ሀሳብ ለማካተት እና በቀጣይም በባለቤትነት ስሜት እንዲተገብሩት ለማድረግ መሆኑን  ጠቅሰዋል። ይህም የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ዋና አፈ ጉባኤዋ አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ በመንግሥት ብቻ ሲሰጥ የቆየውን የግብርና ኤክስቴንሽን ወደ ባለብዙ ተዋናይ አገልግሎት እና አሥተዳደር ለመቀየር በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት መደረጉ መልካም ጅምር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  ዘመናዊ ግብርናን ለማሳካትም የግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎትን ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

የግብርና ቢሮ ከአማራ ክልል ምክር ቤት ጋር በመተባበር በረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ አስተያየት ለመሰብሰብ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የተደረገው ውይይት  ጠቃሚ ግብዓቶች እንደተገኙበትም ኃላፊው ገልፀዋል። በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ የጋራ ሐሳቦችን በማሰባሰብ የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ለማስቻል የታሰበ መሆኑንም አብራርተዋል። ከዚህ ባለፈ የኤክስቴንሽን አገልግሎቱን ጥራት እና ተደራሽነት ሊያሳድግ እንደሚችል አስገንዝበዋል።

ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ሆኖ ከመፅደቁ በፊት መታየት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዲታዩ እና ግብርናው ዘመኑ ከደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን እንዲሁም    የግልፀኝነት ችግር ያለባቸው  በቀጣይ  ተሻሽለው እንዲፀድቁ  የሚያስችል ውይይት መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው የግብርና ኤክስቴንሽን የአገልግሎት አሰጣጡ የተደራሽነት ችግር የነበረበት፣ አካታች አለመሆኑ፣ የጥራት ችግር፣ የተሟላ አገልግሎት አለመሰጠቱ የነበሩ ጉድለቶች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

የአገልግሎት አቅራቢዎች ምዝገባ እና ብቃት (የብቃት ማረጋገጫ)፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎት  (የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ፣ የቢዝነስ ማማከር፣ የሥልጠና አገልግሎት፣ የገበያ ትስስርን፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ስለማቀናጀት) የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን፣  የፋይናንስ ምንጭ እና ፈንድ፣ የክፍያ አሠራርን፣ አካታችነት እና ተጠያቂነት በረቂቅ አዋጁ በግልፅ የተመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግሥት ብቻ ሲሰጥ የነበረውን የግብርና የኤክስቴንሽን አገልግሎት በዚህ ረቂቅ አዋጅ በሌሎችም ባለድርሻ  አካላት እና በባለብዙ ተዋንያን ጭምር እንዲሰጥ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ይበልጥ ኢንቨስትመንት እና የመልማት አቅምን የሚያሳድግ ነው። አዋጁም የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ጀምሮ ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት የላቀ ሚና አለው ብለዋል።

አዲሱ የግብርና ኤክስቴንሸን አገልግሎት ሥርዓት የግል ዘርፉን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን እና የሙያ ማኅበራትን በማካተት እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ተጠያቂነት ያለው አሠራር በመዘርጋት የገጠር ሁለንተናዊ ለውጥን እውን የሚያደርግ መሆኑን አቶ ደረጀ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት በደቡብ ጎንደር ዞን በሊቦ ከምከም ወረዳ የጣራ ገዳም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር  ፈጠነች ጌጡ በግብርናው የሚሰጠው አገልግሎት በየጊዜው እየተሻሻለ መሆኑን ገልጸዋል። የምክር አገልግሎት የሚሰጡ አካላት መብዛታቸው ደግሞ አርሶ አደሮች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት እና ለምርታማነት እንደሚጠቅም ተናግረዋል። አዲሱ የግብርና ኤክስቴንሽን አዋጅ ፀድቆ ተግባራዊ ሲሆን የተሻሻለ የግብርና ዕውቀት ሽግግር እንደሚኖር እና ምርታማነትን ሊያሳድግ እንደሚችል ተስፋ አድርገዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈር እና ውኃ ምርምር ዳይሬክተር እና የአፈር ለምነት ተመራማሪ ተስፋዬ ኩምሳ (ዶ/ር) የግብርና አሠራሮች ወደ አርሶ አደሮች ደርሰው ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ባለድርሻ አካላት መብዛታቸው በሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

ብዝኃ ተሳትፎ ያለበት የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለኢትዮጵያ የግብርና ልማትም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የሚያምኑት። አዲሱ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት በትኩረት እና በቆራጥነት መከታተል እና መምራት እንደሚያስፈልገውም ዶክተር ተስፋዬ አስገንዝበዋል። ባለብዙ ተዋናይ የግብርና ኤክስቴንሽን ግብርናውን በማዘመን የገጠር ሽግግርን እንደሚያፋጥንም ገልጸዋል።

አካሉ ተሾመ (ዶ/ር) የመወያያ ፅሑፍ ያቀረቡ እና ረቂቅ አዋጁን ካዘጋጁት የኮሚቴ አባላት እና አማካሪ አንዱ ናቸው። የግብርና ኤክስቴንሽን የዕውቀት፣ የክህሎት እና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት አርሶ አደሩ የተሻለ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል። ረቂቅ አዋጁ በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በሆልቲ ካልቸር፣ በደን ልማት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ ከአነስተኛ አርሶ አደር እስከ ሰፋፊ እርሻ ላይ ለተሰማሩ የግል ባለሀብቶች  በአጠቃላይ ግብርና እና ግብርና ነክ በሆኑ ጉዳዮች ለተሰማሩት ሁሉ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

በቅርቡ አዋጁ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግም ጠቁመዋል። አዋጁ ሲፀድቅ እና ሲተገበር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አብራርተዋል። በበርካታ ባለድርሻ አካላት ሐሳቦች እየተሰጠበት፣ እየተብራራ እና እየዳበረ  የመጣ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም ጠንካራ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለሀገር እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ነው አማካሪው የተናገሩት።

ዜና

 

ከ226 ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል ተሰብስቧል

የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

በ2017/18 የምርት ዘመን 286 ሺህ 332 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች መሸፈኑን በዞኑ ግብርና መምሪያ የእፅዋት ጥበቃ እና የድህረ ምርት አያያዝ ባለሙያ አቶ አለነ ባዘዘው ለበኵር ተናግረዋል። ከዚህም 13 ሚሊዮን 675 ሺህ 614 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። አቶ አለነ በስልክ እንደተናገሩት 147 ሺህ 25 ሄክታር በኩታ ገጠም (በክላስተር) የለማ ነው። እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በቆሎ፣ ስንዴ እና ጤፍ በዋናነት የተመረቱ ሰብሎች ናቸው።

በዞኑ የምግብ እና የቢራ ገብስ፣ ዳጉሳ፣ ሩዝ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ አተር፣ አኩሪ አተር፣ ኑግ፣ ተልባ፣ ሰሊጥ፣ ቦሎቄ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ጤፍ እና ስንዴ   ተሰብስቧል። መረጃው እስከተጠናቀረበት ታኅሳስ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 196 ሺህ 609 ሄክታር ሰብል መሰብሰቡንም ባለሙያው ገልፀዋል።

አርሶ አደሮች በደረሱ ሰብሎች ላይ የምርት ብክነት እንዳይኖር በፍጥነት እና በጥንቃቄ የመሰብሰቡን ሥራ በትኩረት እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል። ።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የታህሣስ  20  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here